Thursday, 28 November 2024

ወደ ኦርቶዶክስ መመለስ¡? – (የመጨረሻ ክፍል)

 Please read in Pdf

መጽሐፍ ቅዱስ ሥልጣኑ “ሲገሰስ”!

መጽሐፍ ቅዱስ የክርስትና ዋና ማዕከልና የትምህርቶቹም ኾነ የልምምዶቹ መሠረት ነው። ይህ እንዲኾን ያደረገው ዋናው ምክንያት ደግሞ የመጽሐፍ ቅዱስ ሥልጣን ነው። መጽሐፍ ቅዱሳዊው ሥልጣን ራሱ እግዚአብሔር ስለ ኾነ፣ መጽሐፍ ቅዱስ የትኛውንም ትምህርት ወይም መጽሐፍ ይዳኛል፤ ይመዝናል እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ ከርሱ ውጭ በኾነ ትምህርትም ኾነ መጽሐፍ ፈጽሞ አይመዘንም፤ አይመረመርም።

  

በቀረበው ዶክመንተሪ ላይ ግን ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጭ የኾኑ ትምህርቶችን ለማስረጽና እውነተኛ አድርጎ ለማቅረብ፣  የቤተክርስቲያን አባቶች የተባሉ ትምህርቶች ሲጠቀሱ ይስተዋላል። በዚህ ንግግራቸው የቅዱሳት መጻሕፍት ሥልጣን ተገስሶና ተድበስብሶ፣ ሐዋርያነ አበውና የቤተ ክርስቲያን አባቶች ከተባሉት ንግግሮችና ትምህርቶች ጋር በአንድነት ሲጠቀሱ ማስተዋል ይቻላል። ነገር ግን የሐዋርያውያነ አበውም ኾነ፤ የቤተ ክርስቲያን አባቶች የትኛውም ትምህርትና መጽሐፍ በቅዱሳት መጻሕፍት እውነት ይፈተሻል፤ ይመዘናል እንጂ ከመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ጋር እኩል ቅቡልነት የላቸውም።

ከዚህም የተነሣ ሐዋርያውያነ አበውም ኾኑ የቤተ ክርስቲያን አባቶች ከመጽሐፍ ቅዱስ የተለየ አስተምህሮ ቢኖራቸው፣ በዚህ ስም ስለ ተጠሩ ብቻ ተቀባይነት አይኖራቸውም።

ከዚህ ጋር መጽሐፍ ቅዱስ በግልጥ ሥልጣኑ ሲገሰስ የምናስተውልበት መንገድ አንዱ፣ አተረጓጎሙ አንድምታዊ በኾነና ከዐውዳቸውና ከተነገረባቸው ዓላማቸው ተለያይተውና ተፋትተው የቀረቡ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችን ማንሳት ይቻላል፤ ለምሳሌ፦

·        ሐዋዝ፣ 1ዮሐ. 1፥7ን ለካህን ኑዛዜ እንደሚገባ ሲጠቅስ ይህን ቃል ጠቅሶአል።

·        ዘካ. 1፥12 - ቅዱሳን መላእክት ያማልዳሉ ለማለት ተጠቅሶአል።

·        ራእ. 6 - ላይም ቅዱሳን ለእኛም ጭምር ይጸልያሉ ለማለት ተጠቅሶአል።

·        ዮሐ. 6 - የጌታችን ኢየሱስ ሥጋ ወደሙ ማለትም ለቅዱስ ቁርባን ሲጠቀስ እናስተውላለን።

ሐዋዝ ከዚህ በዘለለ፣ እጅግ አጸያፊ በኾነ መንገድ እንዲህ ሲልም እኛን በመክሰስ ይናገራል፤

“ስለ ማርያም ለመናገር ... መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጥቅስ ብቻ ይሻሉ? በዚህም ከበረከቷ ይጎድላሉ።”

ይህ ፍጹም መጽሐፍ ቅዱስን የማቃለል ንግግር ነው፤ ምክንያቱም እኛ የመጽሐፍ ቅዱስ አማኞች፣ መጽሐፍ ቅዱስ ዝም ሲል ዝም የምንል፤ ሲናገር ብቻ አብረን የምንናገር ነንና። ስለ ማርያም የምናስተምረው መጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተጠቀሰውን ብቻ እንጂ ከመጽሐፍ ቅዱስ ተቃራኒ የኾነውንና ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጭ የተነገረውን ኹሉ አይደለምና።

ሐዋዝ እጅግ ደፋር ከመኾኑ የተነሣ፣ “መዳን በእግዚአብሔር ጸጋ ብቻ” ብሎ ማስተማር መጽሐፍ ቅዱሳዊ እንዳልኾነ ለመተንተን ሲጣጣር መመልከቴም ነው። ወንጌላዊው ዮሐንስ፣ “እኛ ሁላችን ከሙላቱ ተቀብለን በጸጋ ላይ ጸጋ ተሰጥቶናልና ሕግ በሙሴ ተሰጥቶ ነበርና፤ ጸጋና እውነት ግን በኢየሱስ ክርስቶስ ሆነ።” (ዮሐ. 1፥16-17) ብሎ እንደ ተናገረው፣ ምሉዕ የኾነውና ያልተፈጠረው የእግዚአብሔር ጸጋ ክርስቶስ እንደ ኾነና መዳናችንና የዘላለም ጉዳያችን የተወሰነው በክርስቶስ ኢየሱስ ብቻ እንደ ኾነ እንደ አዲስ ወንጌልን “የምሥራች!” ብሎ ማን በነገረው?!

አየለ የተባለውም ሰው፣ እንዲህ ይላል፣ “ድንግል ማርያም አታማልድም ብለህ እንዴት ትድናለህ?” እኔ ደግሞ አየለን ጠይቀዋለኹ፤ “ድንግል ማርያም ራስዋ ‘መንፈሴም በአምላኬ በመድኃኒቴ ሐሴት ታደርጋለች፤’ (ሉቃ. 1፥47) ብላ እንደ ተናገረችና ርስዋም መድኀኒት እንደሚያስፈልጋት መጸለይዋን አላነበብህምን? መድኃኒት የሚያሻው ፍጡር እንዴት ለሌላው መድኀኒት መኾን ይቻለዋል? እኛን ኹላችንን ያዳነ አንድ መድኃኒት አለ፤ ርሱም መድኀኒ ዓለም ክርስቶስ ነው!

የሐዋዝ “አስፈራሩኝ” ውሸት

የዛሬ ሦስት ዓመት ገደማ ቃለ መጠይቁን በሠራ ማግስት፣ ከደወሉለትና ከሞገቱት ሰዎች መካከል “ብቸኛው” ሰው እኔ ሳልኾን አልቀርም፤ በዚህኛው ቃለ መጠይቁ ደግሞ “ዛቻና ማስፈራራት እንደ ደረሰበት” ሲጠቅስ አድምጫለኹ። ነገር ግን ለመወደድ በዚህ ልክ መዋሸትና ቀበሮአዊ ብልጣ ብልጥነትን መጠቀም እጅግ ያሳፍራል። አንባቢያንና አድማጮች ይፈርዱ ዘንድ ድምጽ ቅጂውን ከግማሽ በላይ ከዚኹ ጽሑፍ ጋር በቴሌግራም ላይ በአንድነት ላይ አያይዘዋለኹ።

ሐዋዝ በቃለ አዋዲ አገልግሎቱ ኹሉ ላይ ሲ-ዋ-ሽና ሲዘ-ብት የኖረ እንጂ፣ ሲያመልክና ሲያስመልክ የኖረ ሰው አይደለምና እጅግ ያሳዝነኛል፤ ነገር ግን በቂ መረጃ ባገኝበትም በመራራትና ሊመለስ ይችላል በማለት ታገሥሁት፤ ጠበቅሁት፤ ርሱ ግን በለየለት ዋ-ሾ-ነቱ ተገለጠ።

ሌላውና፣ የሐዋዝን ውሸት ከሚያጎሉት ነገሮች አንዱ የ”ዲያቆን” ሄኖክ፣ “መጀመሪያውኑ አልካድሁም እዚሁ ነበርኩ የሚሉ ሰዎች ትክክል አይደሉም” የሚለው ንግግሩ የሐዋዝን ውሸታምነት አፈር፤ ደቼ የሚያበላና ተሐድሶ ያልነበረ መኾኑንም ጭምር ያጐላ ንግግር ነው!

በመጨረሻም ሐዋዝ፣ መዝሙሮቹን ከልሶና አሻሽሎ ለተቋማዊው ኦርቶዶክስ በሚኾን መልኩ እንደገና እሠራዋለሁ በማለት ቃል ገብቶአል። ጌታ ኢየሱስ በመንፈስ ቅዱስ እንዲወቅሰውና እንዲገስጸው ትልቁ ጸሎቴ ነው።

ለምን ግን ከእኛ ተለዩ?

በግሌ ሦስት ምክንያቶች አሉኝ፤

1. በትክክል ተሳስተው፣ እውነትን ባለማወቅ በትምህርት ነፋስ የተወሰዱ ሊኖሩ ይችላሉ፤ እንዲህ ላሉት ልናዝንላቸው፣ ልንጸልይላቸው በትክክል በሰይጣን ወጥመድ ተይዘዋልና ልንማልድላቸው ይገባል።

2. አብዛኛዎቹ ደግሞ በሥነ ምግባር ዝቅጠት መዘፈቃቸውን ለመሸፈኛነት ሊጠቀሙበት የተመለሱ ናቸው። ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ለመደበቅ ከተፈለገ ዋሻና ሰፊ ሜዳ ነው። እናም ብዙ ጊዜ በእኛ ዘንድ ተመክረው፤ ተዘክረው ያስቸገሩ ብዙ ጊዜ ምርጫቸው ወደዚያው መመለስ ነው። እንዲህ ላሉት ብርቱ ተግሳጽ የሚያስፈልጋቸው ይመስለኛል።

3. ወንጌል እንሰብካለን፣ ሕዝብን በቅርበት እንደርሳለን በሚል የተሸፋፈነና ለቤተ ክርስቲያን ኅብረት ታማኝነትና አክብሮት በጎደለው መንገድ ሊሄዱ የሚችሉም አሉ። አንዳንድ አገልጋዮች ይህን መንገድ ተከትለው ሄደዋል፤ ምናልባትም ለመሄድ እያኮበኮቡ ያሉም ይኖራሉ። እንዲህ ያሉት በርግጥ ይህ ዓላማቸው ከኾነ፣ የቤተ ክርስቲያንን ሥልጣን ባከበረና በእውነተኛ ቅንአት ቢያደርጉት እጅግ ደስ ይለናል። ከዚህ በዘለለ ግን ተራ ሽፋን እንጂ እውነት እንዳልኾነ በተደጋጋሚ ተመልክተናል።

ለአማኞችና ለአገልጋዮች

 ሸክምን ሁሉ ቶሎም የሚከበንን ኃጢአት አስወግደን፥ የእምነታችንንም ራስና ፈጻሚውን ኢየሱስን ተመልክተን፥ በፊታችን ያለውን ሩጫ በትዕግሥት እንሩጥ፤ እርሱ ነውርን ንቆ በፊቱም ስላለው ደስታ በመስቀል ታግሦ በእግዚአብሔር ዙፋን ቀኝ ተቀምጦአልና። በነፍሳችሁ ዝላችሁ እንዳትደክሙ፥ ከኃጢአተኞች በደረሰበት እንዲህ ባለ መቃወም የጸናውን አስቡ።” (ዕብ. 12፥1-3)።

የተስፋ ጭላንጭል

እንዲህ እንደ ኾነ ይቀራል ብዬ አላምንም፤ ወንጌል እንዲህ ብዙዎች ዘንድ እንደ ተ-ሸ-ቀ-ጠበት አይቀርም፤ የሸ-ቀ-ጡት የሚያፍሩበት፤ የተሳሳቱ የሚመለሱበት፣ ምናልባትም ዛሬ ላይ በለየ-ለት ው-ሸ-ትና በማስመሰል እንዲህ የሚናገሩት እንደገና አዝነው ይጸጸቱና ይመለሱ ይኾናል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፤ ጌታ ጻድቅና መጋቢ አምላክ ነው።

ማጠቃለያ!

ወንጌል ያሸንፋል፤ ስለ ተዋሸበት ፈጽሞ አይደበዝዝም፤ ለወደቀውና ለተሰበረውም ዓለም እግዚአብሔር ያዘጋጀው ዕቅድ፣ በጸጋው ፍጥረትን እያደሰ ወደ መንግሥቱ ሙላት ማምጣት ነው። ተሐድሶ ለተበላሸውና ለወየበው፤ ለገረጀፈውና የእርጅና ንቃቃት ለከበበው ዓለም እጅግ አስፈላጊና አይቀሬ ነው። ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን፣ ወንጌል ገፍታ፤ እውነትን ተኳርፋ፤ የርሷ አንደበት ባልኾኑ አካላት ተሸብባ መኖርዋ ዋጋ ያስከፍላታል፤ ይህም እንኳ ቢኾን ወንጌል ስርጓጉጡን እያጠራ፣ ተራራውን እየናደ፤ ሸለቆውን እየሞላ፣ ዓመጸኛውን የሰው ልብ እየረታ፣ ደካሞችን በጌታ ጸጋ እያበረታ፤ ጽኑአንን ደግሞ ደፋርና ኃያል እንዲኾኑ እያደረገ በድል ነሺነቱ እስከ ጌታ ቀን ድረስ ይቀጥላል።

“ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን በማይጠፋ ፍቅር ለሚወድዱ ሁሉ ጸጋ ይሁን።” (ኤፌ. 6:24) አሜን።

3 comments:

  1. ክብር ለእግዚአብሔር ይሁን, እውነት ነው የሚያስፈልገንን ተናገርከን

    ReplyDelete
  2. እውቀት እንደሚርቅህ ተገንዝበናል early church history አንብብ የምስራቅ ክርስትና እንዲህ አይነቱን ቅይጥ አምልኮ አያውቀውም ተሐድሶ አንተ አእምሮው ውስጥ ያለ በሰዎች ድካምና ብርታት የሚለካ የተመለሰና የተቀላቀለ ድማሚት ጉሰማ አይደለም ያየኸው ሁሉ እውነት የሚመስልህ ከአንደበተ ርትዑ ግለሰብ የሰማሃት ሁሉ እውነት የምትመስልህ ሰነፍ እንደሆንክ ከፅሁፍህ ተረድተናል አንብብ ማንበብ አይገድልም እሺ...ከመጥቀስህ በፊት ልብህን መርምር የቆምክበትን እይ!😏

    ReplyDelete
  3. ጌታ ኢየሱስ ሆይ ልቤ በጣም አዝኖ አዝኖ አዝኖ ግን ደግሞ እኔንም ምህረትህ እንዳቆመኝ ሳስብ በረታሁ ። ይሄንን ወንድም እርዳው ።

    ReplyDelete