Wednesday 4 September 2024

የቁባቱን በድን የቆራጠው ካህን! (መሳ. 19-20)

 Please read in PDF

በእስራኤል ልጆች ታሪክ ውስጥ አያሌ አስከፊ ተግባራት ተከናውነዋል፤ ዛሬ የምናየው ይህ አንዱ ነው፤ “በዚያም ዘመን በእስራኤል ዘንድ ንጉሥ በሌለበት ጊዜ በተራራማው በኤፍሬም አገር ማዶ የተቀመጠ ሌዋዊ ነበረ፤” (መሳ. 19፥1) ይላል፣ በመሳፍንት መጽሐፍ ውስጥ ከተቀመጡት የብንያም ሰዎችን የሥነ ምግባር ብልሹነትና በምላጭ ጫፍ ላይ መቆማቸውን ከሚያሳዩት ታሪኮች አንዱን ለመተረክ ሲነሳ።

በርግጥ ሌዋዊው ካህን ቁባቱን ፍለጋ ከኤፍሬም ወደ ቤተልሔም መሄዱ፣ ከአንድ ሚስት በላይ ማግባቱን ያሳያል፤ ይህ በእግዚአብሔር ፊት ተቀባይነት ያለው ተግባር አልነበረም፤ በተጨማሪም፣ እግዚአብሔር ለእስራኤል ልጆች መሳፍንትን የሰጠው፣ ርሱ ብቻውን በነርሱ ላይ ሊነግሥ ነበር። ነገር ግን ለጌታ ከመታዘዝ ይልቅ፣ የሃይማኖት መሪዎቿ ድካምና ኃጢአት እያየለባቸውና እየባሰባቸው ሲሄድ በተደጋጋሚ እንመለከታለን።

ካህኑ ቁባቱን አጊኝቶአት ይዞ፣ ከቤተልሔም ወደ ኤፍሬም በሚመለስበት ጊዜ እግረ መንገዱን ጊብዓ በምትባል በብንያማውያን ከተማ መሸበትና አደረ።

የከተማዪቱ ሰዎች ግን ልክ እንደ ሰዶምና ገሞራ ሰዎች፥ እጅግ አስጸያፊ ተግባር የሚፈጸሙ ነበሩ። በእንግድነት ወደ ነርሱ የመጡትን ካህንና ቁባቱን ከማስተናገድ ይልቅ፣ በካህኑ ላይ የሰዶማዊነት ነውር ሊፈጽሙበት ፈልገው አሳዳሪውን ሽማግሌ፣ እደ ሰዶም ሰዎች ግድ አሉት። ሽማግሌው፦ “ወንድሞቼ ሆይ፥ ይህን ክፉ ነገር፥ እባካችሁ፥ አታድርጉ፤ ይህ ሰው ወደ ቤቴ ገብቶአልና እንደዚህ ያለ ኃጢአት አትሥሩ። ድንግል ልጄና የእርሱም ቁባት፥ እነሆ፥ አሉ፥ አሁንም አወጣቸዋለሁ፤ አዋርዱአቸው፤ እንደ ወደዳችሁም አድርጉባቸው፤ ነገር ግን በዚህ ሰው ላይ እንደዚህ ያለ ኃጢአት አታድርጉ” (19፥23-24) ብሎ ቢለምናቸውም፣ ሰዎቹ ግን ሊሰሙ ፈጽሞ አልወደዱም። በመጨረሻም ግን ሽማግሌው የገዛ ሴት ልጁንና የሌዋዊውን ቁባት አውጥቶ ሰጣቸው።

ሰዎቹ፣ የሌዋዊው ቁባት እስክትሞት ድረስ በመፈራረቅ ሌሊቱን ሙሉ አመነዘሩባት። ሽማግሌው እንደ ሎጥ፣ ራሱን ከማኅበረ ሰቡ ርኩሰት የጠበቀና ያገለለ መኾኑ እጅግ ያስደንቃል፤ ተግባራቸውንም “ክፉ ነገር” ብሎ መጥራቱ ይኸንኑ ያሳያል፤ ሌዋዊው ግን ያሳየው ግዴለሽነትና ደንታ ቢስነት ያሳዝናል።

ሌዋዊው የቁባቱን ሬሳ 12 ቦታ ቆራረጠና ለእያንዳንዱ የእስራኤል ነገድ አንዳንዱን ቁራጭ ላከ። ይህም ነገር የ12ቱን ነገዶች ቁጣ ቀሰቀሰና ምን እንደ ተፈጸመ ለማየት መጡ። ታሪኩን በሰሙ ጊዜ፥ ይህን ኃጢአት የፈጸሙትን ሰዎች አሳልፈው እንዲሰጧቸው ብንያማውያንን ጠየቁ። ብንያማውያን ተቃወሙ፥ የርስ በርስ ጦርነት ተነሣ። በጦርነቱም 40000 እስራኤላውያንና 25100 ብንያማውያን ሞቱ። የብንያማውያን ሴቶችና ልጆች በሙሉ ተገደሉ። ከብንያም ነገድ በሙሉ የተረፉት 600 ሰዎች ብቻ ነበሩ።

ሌሎች እስራኤላውያን፥ ከእስራኤል ነገዶች አንዱ የኾነው የብንያም ነገድ ሊጠፉ እንደ ኾነ ተገነዘቡ፤ ስለዚህ ለእነዚህ 600 ብንያማውያን 600 ሚስቶች የሚገኙበትን ዘዴ ፈጠሩ። በዚህም የብንያምን ነገድ ጨርሶ ከመጥፋት አዳኑት።

ሰዎች ራሳቸው የሚፈልጉትን ነገር ብቻ ሲያደርጉ፥ ኃጢአታቸው አድጎ በርካታ ሰዎችን እንደሚነካና እንደሚያጠፋ አይገነዘቡም። ኀጢአትና ኀጢአተኝነት የመዛመትና ሌላውን የመውረስ ጠባይ አለው፤ የጊብዓ ሰዎች ኃጢአት በሺህ የሚቆጠሩ የበርካታ እስራኤላውያንን ሞትና የብንያም ነገድን ወደ ውድመት የሚያደርስ ጥፋት አስከትሎ ነበር። የአንድ ካህን ሕገ እግዚአብሔር መጣስና የብንያም ነገድ ሰዶማዊነት መኾን፣ ፍጻሜውን መራራ አድርጎታል። ኀጢአት በማናቸውም መንገድ የፍጻሜ መንገዱ ጣፋጭ አይኾንም!

እንግዶችን በማስተናገድ አንዳንዶች ራሱ እግዚአብሔርን ሌሎች ደግሞ መላእክትን ተቀብለው ነበር፤ የብንያም ሰዎች ግን እንግዶቻቸውን ለነውር ተግባር ፈለጉ፡፡ ወንዶቹ ኀፍረተ ቢስና ፍትሕ አልባ ነበሩ፡፡ ምናልባት ታሪኩ ሊረሳ እንጂ ሊተረክ የሚገባው አይመስልም፤ ግን እንድንተርከው ታዝዘናል፡፡ የሴቲቱ ታሪክ አሳዛኝና ልብ ሰባሪ ነው፤ የሚቆምላትና የሚከላከልላት አልነበረም፡፡ ሌዋዊው ሊንከባከብ ከአባትዋ ቤት ቢያወጣትም፣ ነገር ግን ለርኩሳንና ለማይራሩ ሰዎች አሳልፎ ሰጣት፡፡ በዚያ ሙሉ ሌሊት የተፈጸመባትን ርኩሰት ማስተዋልና ርኅራኄ ሊያሳያት ሲገባ ግን አላደረገም፤ ብሎም የቀብር ክብርዋን በመንፈግ ሰውነቷን ቆራረጠው!

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንዲህ ያሉ ታሪኮች መቀመጣቸው፣ ሰው ከእግዚአብሔር ፊትና ከአገዛዙ ሲለይ፤ በራሱም መንገድ መልካም መስሎ የታየውን የሚያደርግ ከኾነ ፍጻሜው ይኸው መኾኑን ያሳያል፡፡ ወዳጆቼ! ዛሬም በምድራችን ላይ የምንሰማቸው አያሌ ክፉ ተግባራት፣ ከዚህ እውነታ እምብዛም የራቁ አይደሉም! ከኀጢአታችን ለመታቀብና ለመተው፤ ብሎም ንስሐ ገብቶ ለመመለስ ፈቃደኞች ባልኾንን መጠን፣ የኀጢአት ፍሬና መከር መብላታችንና ማጨዳችን አይቀሬ ነው! “ኑ፥ ወደ እግዚአብሔር እንመለስ፤ እርሱ ሰብሮናልና፥ እርሱም ይፈውሰናል፤ እርሱ መትቶናል፥ እርሱም ይጠግነናል።” (ሆሴ. 6፥1) የሚለው የጌታ ቃል ዛሬም ሕያው ነውና እንመለስ!

No comments:

Post a Comment