የትምህርትም፤ የምግባርም ውድቀት፣ የቤተ ክርስቲያንን ኹለንተናዊ መልክ
ከሚያበላሹ መካከል ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛሉ። ትምህርቱ እንደ ኑፋቄ ያለ ሲኾን፣ ምግባራዊ ውድቀቱ ደግሞ እንደ ሰዶማዊነትና
ዓለማዊነት ያሉ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሲከሰቱ እጅግ ጆሮን ጭው ያደርጋሉ። እኒህን ተግባራት የሚፈጽሙ ሰዎች አንዳንድ[?] በ“ሃይማኖት”
ጥላ ሥር ያሉ ሰዎች ስለ መኾናቸው ብዙዎቻን እማኝ ነን።
ከዚህ ጋር በማይተናነስ መንገድ፣ ባህላዊ ሃይማኖቶች እጅግ አስፈሪ በኾነ
መንገድ እያቆጠቆጡ መኾናቸውን ስናይ ደግሞ፣ ቤተ ክርስቲያን ወደ ፊት ርቱዑን ወንጌል ለመመስከር ስላለመቸገሯ እፈራለኹ።
ጥቂቱን ልጥቀስ፣ የዋቄፈና እምነት ተከታዮች የሚያከብሩት ኢሬቻ፣ የሲዳማ ጨምበላላ፣ የጋሞ ብሔረ ሰብ ዮ ማስቃላ፣ የካፊቾ
ማሽቃሮ፣ የሐዲያ ያሆዴ፣ የወላይታ ጊፋታ፣ የጌዲዮ ባላ ካዳባ፣ የዘይሴ ቡዶ ኬሶ፣ የቦሮ ሺናሻ ጋሪ ዎሮ፣ የጎፋ ጋዜ ማስቀላ፣
የኦይዳ ዮኦ ማስቃላ፣ የየም ሄቦጋሽ፣ የጌዴኦ ዳራሮ፣ የከምባታና የጠምባሮ መሳላ፣ የዶንጋ ዶንጊ ፉልታ … ሌሎችም ባህላዊ
ሃይማኖታቸውን ፍለጋ ላይ ያሉ ይመስላል።
የባህላዊ እምነት ተከታዮቹ የክርስትናም ኾነ የሌላ ቤተ እምነት ተከታዮች ሊኾኑ
ይችላሉ፤ ቀለል አድርገው ግን፣ “ባህላችንን ማክበራችን ምን ችግር አለው? ይህ እኮ የአዲስ ዘመን መለወጫ ባህል ብቻ ነው፤
የምናመልከውም የፍጥረትን አምላክ ነው …” የሚሉ አያሌ ሰበቦች አሉአቸው። ሌሎች እንዲያውም ባህል ጠል እንደ ኾንን ጨምረው
ሲጠቅሱ እሰማለሁ። ነገር ግን አንድ እውነት መቃወም አንችልም፤ ርሱም ቋንቋ፣ አለባበስ፣ ቤት አሠራር፣ አመጋገብና ሌሎችም
የባህል አካላት ናቸው፤ እኛም ከዚህ ውጭ አይደለንም።
ጥያቄአችን ግን በባህል አስባብ ስለሚመጡ ባዕዳን አማልክትና አምልኮ እንጂ። ኹሉም
ባህላዊ ሃይማኖቶች መሥዋዕትን ከመሠዋት፣ የጸሎትና የዝማሬ አምልኮን፣ ሞራ ማንበብና ገላጭ፣ የደመራና የተለያዩ የእሳት መሥዋዕቶች
… ማቅረብን በሚገባ በውስጣቸው ይንጸባረቃል። እናም ወደፊት ከመናፍቅነት በማይተናነስ መንገድ ይህ ባህላዊ ሃይማኖት ለቤተ ክርስቲያን
እጅግ አደገኛ ተግዳሮት ነው ብዬ አምናለኹ።
መጽሐፍ ቅዱስ፣ “እግዚአብሔር ያለማወቅን ወራት አሳልፎ አሁን በየቦታቸው ንስሐ
ይገቡ ዘንድ ሰውን ሁሉ የሚያዝዘው” (ሐ.ሥ. 17፥30)፣ “ምናልባትም እየመረመሩ ያገኙት እንደ ሆነ፥ እግዚአብሔርን ይፈልጉ
ዘንድ” ነው፤ (ሐ.ሥ. 17፥26)፤ ነገር ግን ክርስትና ሞኝነት ኾኖብን የዚህ ምድር ባህልና ጥበብ ታላቅና ቅዱስ ከመሰለን፣ “እግዚአብሔር
ጥበበኞችን እንዲያሳፍር የዓለምን ሞኝ ነገር መረጠ፤ ብርቱንም ነገር እንዲያሳፍር እግዚአብሔር የዓለምን ደካማ ነገር መረጠ፤ እግዚአብሔርም
የሆነውን ነገር እንዲያጠፋ የዓለምን ምናምንቴ ነገር የተናቀውንም ነገር ያልሆነውንም ነገር መረጠ፥ ሥጋን የለበሰ ሁሉ
በእግዚአብሔር ፊት እንዳይመካ።” (1ቆሮ. 1፥27-29) የሚለውን ታላቅ ቃል ማስታወስ እንወዳለን።
የመስቀሉ ሥራ ጥንትም ባህላቸውንና ወጋቸውን፤ ቆሮንቶሳዊነታቸውን ለሚወድዱ ሞኝነት
ነበር፤ ነገር ግን የእግዚአብሔር ሞኝነት ከሰው ጥበብ ይልቅ እጅግ ይጠበባል፤ እናም፣ “ከእኔ ይልቅ አባቱን ወይም እናቱን
የሚወድ ለእኔ ሊሆን አይገባውም፤ ከእኔ ይልቅም ወንድ ልጁን ወይም ሴት ልጁን የሚወድ ለእኔ ሊሆን አይገባውም፤” (ማቴ. 10፥37)
ኢየሱስ እንደ ተናገረ፣ እኔም እላለሁ፣ ከኢየሱስ ይልቅ ባህላዊ ሃይማኖቱን የሚወድ ለኢየሱስ አይገባውም ብለን ለመናገር ከክርስቶስ
መንፈስ የተነሣ እንደፍራለን!
(ስለ ባህላዊ እምነቶች ከጻፍኹት መጽሐፍ ተቀንጭቦ የተወሰደ)
“ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን በማይጠፋ ፍቅር ለሚወድዱ ሁሉ ጸጋ ይሁን።”
(ኤፌ. 6:24) አሜን።
may God bless you in all your ways as you walk with him
ReplyDeleteGod bless you and keep you
ReplyDelete