ኦርቶዶክሳዊው ተሐድሶ እያየለና በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነትን እያገኘ ሲመጣ፣ በቃላት በማባበል፣ በጥቅምና በክብር በማማለል፣ መልሰን አናወግዛችሁም በሚል የተስፋ ቃል በመስጠት … እየቀረበልን ያለው ጥያቄ፣ “ኑ! ወደ ኦርቶዶክስ ተመለሱ!” ሚል ነው። ከዚህ በታች የምናስቀምጣቸው ጠንካራ ምክንያቶች የመመለስና ያለ መመለስን ጥያቄ ትርጕም ይሰጡታል።
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ወደ ኋላ ስለ መመለስ በማስጠንቀቂያ አዘል ከተጻፉ
መልእክቶች አንዱ፣ የዕብራውያን መልእክት ነው። የሐዋርያት ሥራን መጽሐፍ ስናጠና እንደምናስተውለው፣ አስቀድሞ ክርስትናን
ለተቀበሉ አይሁድ የመጀመሪያዎቹ የቤተ ክርስቲያን ዓመታት እጅግ አስቸጋሪዎች ነበሩ። በእነዚህ ጊዜያት ክርስትና በአጭሩ
የአይሁድ ሃይማኖት ኾኖ ነበር። ከ120ው የጌታ ቤተ ሰቦች (ሐ.ሥ. 1፥15) ጀምሮ ኹሉም በአንድነት ያመልኩና ያገለግሉ
የነበረውም በአይሁድ ቤተ መቅደስ ውስጥ ነበርና፤ (ሐ.ሥ. 2፥46፤ 3፥1፤ 5፥42)።
በኋላ ላይ ክርስትናን የተቀበሉት አይሁድ (ሐ.ሥ. 2፥41፤ 4፥4)፣ በዋናነት
ክርስትናን ቢቀበሉም በአይሁድ የነበረውን የአምልኮ ሥርዓታቸውን ብዙም አልለወጡም ነበር። ምንም እንኳ ክርስቶስ ለኀጢአታቸው
የሞተ ሊቀ ካህናትና መሲሕ እንደ ኾነ ቢያምኑም፣ ነገር ግን የእንሰሳት መሥዋዕትን ማቅረብና የአይሁድን ባህላዊ ልምምድ
መተግበርን አልተዉም ነበር። የእስጢፋኖስ በአይሁድ እጅ መገደል፣ አሕዛባዊው ቆርነሌዎስ ወደ ክርስትና መመለስና በሐዋርያት ሥራ
ምዕ. 15 ላይ የተሰጡት ውሳኔዎች ግን ነገሮችን ፍጹም ለወጡአቸው፤ (ሐ.ሥ. 7፥51-60፤ 10፥1)።
በቤተ መቅደስ ተቀምጠው በነበሩ አይሁድ ክርስቲያች ላይ፣ የእስጢፋኖስ በአይሁድ
እጅ መገደል፣ ከመቅደስ ለመውጣታቸው አንድ ትልቅ ምክንያት ሲኾን፣ የአሕዛባዊው ቆርነሌዎስ አማኝ ኾኖ አይሁድ ወዳሉበት መሲሐዊ
ክርስቲያን ማኅበረ ሰብ መቀላቀል ጥያቄን አስነሣ። ነገሩ እየሰፋ ሲሄድና ክርስትና እያየለ ሲመጣ ኹለቱን ጽንፈኞች(አይሁድና
አሕዛብን) በአንድ ሜዳ ላይ የአንድ ርስት ተካፋይ ሊያደርግ ሰበሰባቸው። ይህ ግን ለአይሁድ ፈጽሞ አልተዋጠላቸውም።
እናም ከአሕዛብ የተመለሱ ክርስቲያኖችን ወደ ራሳቸው ወግና ሥርዓት፤ ልምምድና
ትምህርት እንዲመጡ አይድ ክርስቲያኖች ያላደረጉት ጥረት አልነበረም፤ እንደ ገላትያ ባሉ አብያተ ክርስቲያናት ላይ ጥቂትም ቢኾን
ተሳክቶላቸዋል፤ ቅዱስ ጳውሎስ ይህን የኋልዮሽ ጉዞ፣ “በጥንቆላ የተደረገ አዚም” ብሎ ይጠራዋል (ገላ. 3፥1)፤ የዕብራውያን
መልእክት ጸሐፊ ደግሞ እንዲህ ያሉ ተመላሾችን “ዳተኛ” ይላቸዋል (ዕብ. 6፥11)።
እኒህ ሰዎች ከክርስትና ይልቅ አይሁዳዊነትን ያስበለጡበት ኹለተኛው ምክንያት፣ እስራኤል ከሮም ቅኝ ግዛት እንድትወጣ የሚፈልጉ አማፂ
አይሁዳውያን፣ በጥላቻ በአሕዛብ ላይ በመነሣታቸው ምክንያት፣ የክርስትናን ወንድማማችነት በመጠበቅና አይሁዳዊና አሕዛብ የሚለውን
ከፋፍሎ በማየት መካከል ከፍተኛ የኾነ አጣብቂኝነትን ፈጠረ። እንግዲህ እውነተኛ አማኞች ላይ የደረሰው ተጽዕኖ ፈርጀ ብዙና
ሃይማኖታዊም፤ ፖለቲካዊም መልክ የነበረው መኾኑን ከቅዱሳት መጻሕፍት እናስተውላለን።
በአገራችን በኢትዮጵያ በአጼ ዘርዓ ያዕቆብ ዘመንም፣ አጼው ደቂቀ እስጢፋኖሳውያንን
ለመመለስ ብዙ ጥረት አድርጎ ነበር፤ አጼው እስጢፋኖሳውያን እንዲመለሱ ይፈልግ የነበረው የራሱን “አፍቃሬ ማርያምነት ለማስረጽና
አንድ ሃይማኖት ብቻ” የሚለውን ለማጽናት ነበር እንጂ እውነተኛውን ወንጌል ለመስበክና የእግዚአብሔርን መንግሥት ለማስፋት
አልነበረም። የአጼውን ዐሳብ የተረዱት እስጢፋኖሳውያን ግን፣ ላመኑበት እውነት ጸንተው ቆመው ፍጹም የኾነውን አሰቃቂ መከራ ተቀበሉ
እንጂ ለማባበያውም ኾነ ለመከራው ፈጽሞ አልተንበረከኩለትም።
በዘመናችንም
እውነተኛውን ክርስትና ወደ ኋላ የሚስቡ አያሌ ምክንያቶች አሉ። በተለይም ደግሞ በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ላይ
ሊደረግ ስለሚገባው “ቤተ ክርስቲያኒቱ ወደ ኢየሱስ ትምህርት፣ ሕይወትና ሥራ መመለስ አለባት” በሚለው እንቅስቃሴ ዙሪያ፣
ጠንከር ያሉ ሥራዎች ከመጀመራቸውና ብዙዎችም ፊታቸውን ወደ ወንጌል ከመመለሳቸው ጋር ተያይዞ ግልጽ ተግዳሮቶች እየተስተዋሉ ነው።
ከተግዳሮቶቹ መካከል፦
1. የተሐድሶ
መሪዎችን የማስኮብለል ሥራ፦ የቤተ ክርስቲያኒቱ መሪዎች፣ በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ ያለውን አደጋ ተመልክቶ በመጽሐፍ
ቅዱስ እውነት ከማስተካከልና ከማረም ይልቅ፣ መጽሐፍ ቅዱስ በግልጥ ቃል፣ “እረኛውን ምታ፥ በጎቹም ይበተናሉ፤” (ዘካ. 13፥7) ብሎ የተናገረውን መርህ
እየተከተሉ ይመስላል። ቀድሞ በኦርቶዶክሳዊ ተሐድሶ የሚደረገውን እንቅስቃሴ መቃወም፣ ማሳደድ፣ ስም ማጥፋት፣ በአካል ከተገኙ
ደግሞ መደብደብ፣ የአካል ጉዳት ማድረስ፣ ማሳሰር፣ ማፈናቀል፣ በሰዎች መካከል ማዋረድ፣ ቤት እንዳይከራዩ ማድረግ ወይማ
ከተከራዩ ደግሞ በግድ ማስለቀቅና ሌሎችም የተቃውሞ ሥራዎች ይሠሩ ነበር።
አኹን ግን ከመቃወምና ከማሳደድ ይልቅ፣ ተለሳልሶ መቅረብ፣ አገልግሎቱን
ማዳከምና ውስጥ ካለው አገልጋይና አገልግሎት ምንም ልዩነት የሌለው በማስመሰል ወይም “እዚያ የምታገለግሉትን እዚህም ማገልገል
ትችላላችሁ” በሚል የስልክ ማባበያ ማቅረብ፣ በዘመድና በሚቀርቧቸው ሰዎች ማስጠየቅና … አገልግሎቱ እንዲፈታ የማድረግ ሥራ
በየአኅጉራተ ስብከት ተጠናክረው ቀጥለውበታል።
2. እውነተኛውን
ወንጌል ያለ መፈለግ፦ በኦርቶዶክሳዊው ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንዲመጣ የምንፈልገው ተሐድሶ እውነተኛና
መጽሐፍ ቅዱሳዊው ነው። ይም ማለት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በራስዋ ልጆች የተነቀፈው የተሰቀለው ክርስቶስ
ወንጌልን በትክክል እንድትሰብክ፣ ታላቁን ሐዋርያዊ ተልእኮ በመፈጸም መንግሥቱን የማስፋት ሥራ ከኢትዮጵያ ወጥቶ በጎረቤት
አገራትና በአኅጉራችን ብሎም በዓለም ኹሉ ማድረስ፣ እግዚአብሔርን የማያከብሩ ማናቸውም ትምህርቶች፣ ልምምዶች፣ ጽሑፎች፣
ትውፊቶች ኹሉ አስወግዳ ማየት ናፍቆታችን ነው።
በቤተ ክርስቲያቱ ውስጥ ይህ እውነት በግልጽ ተገፍቶ የሚታየው ትምህርቱን
በመቃወም ብቻ ሳይኾን፣ ለዚህ ትምህርት የተገባ ሕይወትና ቅድስና የሌላቸው ሰዎች ይህን ወንጌል ይዘናል በማለታቸውም ጭምር ነው፤
ይህ ሐቅ ደግሞ “ለኦርቶዶክስ ተመልሰናል” የሚሉ ሰዎችን ጭምር ያካትታል። እውነተኛው ወንጌል ተሸፍኖ፤ እውነተኛውን ወንጌል
“የያዙ” የነበሩ፤ እውነተኛውን ወንጌል እውነተኛ ባልኾነ ሕይወት ጭምር ለመሸፈንና ለማክፋፋት ሲነሱ፤ በቤተ ክርስቲያኒቱ
ያለውን ጨለማ ምን ያህል ሊያበረታ እንደሚችል ለሚያስተውል እጅግ የተገለጠ ነው።
ይቃወሙትና ይጠሉት የነበረውን ያንን መንገድ፣ ለመላመድና ትክክለኛ ባልኾነ
የተሐድሶ መንገድ “ከጨለማው ሥራና ሥርዓት ጋር ለማስማማት” መጣር፣ የእግዚአብሔርን ሥራ በሰው ሥርዓት የመተካት ያህል እጅግ
አስቀያሚ ነው፤ ቃሉ፣ “ጌታም፦
ይህ ሕዝብ በአፉ ወደ እኔ ይቀርባልና፥ በከንፈሮቹም ያከብረኛልና፥ ልቡ ግን ከእኔ የራቀ ነውና፥ በሰዎች ሥርዓትና ትምህርት
ብቻ ይፈራኛልና”
(ኢሳ. 29፥13) የሚለው በቤተ ክርስቲያቱ እንዲፈጸም አብዝተው እየተጉ ይመስላል።
ውድ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሆይ!
እኛ ቤተ ክርስቲያኒቱ በወንጌል ትታነጽ፣ የገረጀፈ መልኳ በቅዱስ ቃሉ ኩል
ይጌጥ፣ በሰው ትምህርትና ሥርዓት የደመቀው አምልኮና ልምምድ ፍጹም በኾነ በቅዱስ ቃሉ እውነት ይቁም የሚል ጠንካራ ጥሪና ናፍቆት
ብቻ ነው ያለን። ይህ ግን የሚፈጸመው፣ አገልጋዮችን በማስኮብለል፣ ለብ እንዲሉና ተመሳስለው እንዲኖሩ በማድረግ ፈጽሞ አይደለም።
ወንጌል ሕይወት ነው፤ ለዚህም ነው የታመኑለትም በነፍስ ተወራርደው (ፊል.
2፥30) የሚያለግሉት። ወንጌል ከሕይወት ያነሰ መሥዋዕትነት አይሻም፤ ከወንጌል ውጪ የትኛውም ሰዋዊ ብልሐትና ጥበብ ለጊዜው
የሚጠቅም ይምሰል እንጂ፣ ወደ ቅዱስ ወንጌል የመመለሱን መንገድ የበለጠ የድጥ ከማድረግ የዘለለ ምንም ፋይዳ የለውም።
እናም ለኦርቶዶክሰዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፣ ምሥራቃዊውን ትውፊት ባልለቀቀ
መንገድ፤ ፍጹም ለወንጌል እውነት በተሸነፈ ቁመናዋ ተስካክላ ትቆም ዘንድ እየናፈቅን፣ በወንጌል እውነት ጸንታችኹ በአንዳች
ማባበል ሳትታለሉ፣ በብዙ መከራና ማጣት ውስጥ ሳትናወጹ ወንጌልን በነፍስ ተወራርዳችሁ ለምታገለግሉ ኹሉ ደግሞ የጌታ ክርስቶስ
ጸጋና ሠላም እጅግ ይብዛላችሁ!
No comments:
Post a Comment