Wednesday 11 September 2024

ዘመን የተጨመረልን በመግቦቱ ነው!

 Please read in PDF

የእግዚአብሔር መግቦት እጅግ አስደናቂ ነው። ጌታ ፍጹም መጋቢ ስለ ኾነ በፍጥረት መካከል አድልዎ ሳያደርግ የሚተገብራቸው አያሌ መግቦቶች አሉ፤ ቅዱሳት መጻሕፍትን ዋቢ አድርገን ምሳሌ ብንጠቅስ፦ “ርሱ[እግዚአብሔር] በክፎዎችና በበጎዎች ላይ ፀሐይን ያወጣልና፥ በጻድቃንና በኃጢአተኞችም ላይ ዝናቡን ያዘንባልና።” (ማቴ. 5፥44)፣ እንዲኹም እግዚአብሔር አምላክ ጋብቻን ባርኮ ለመላለሙ በአምላካዊ መግቦቱ መስጠቱን እናስተውላለን፤ (ዘፍ. 2፥24፤ ማቴ. 19፥4-5)።

በተመሳሳይ መንገድ እግዚአብሔር ለሰዎች ዕድሜንና ዘመንን የሚሰጠውና የሚጨምረው ፍጹም ቅዱስ መጋቢ አምላክ ስለ ኾነ ነው። አስቀድሞ ጊዜንና ዘመንን ሲፈጥር፣ “ኹለት ታላላቆች ብርሃናትን አደረገ ትልቁ ብርሃን በቀን እንዲሠለጥን፥ ትንሹም ብርሃን በሌሊት እንዲሰለጥን ከዋክብትንም ደግሞ ያደረገ” (ዘፍ. 2፥16) እንዲል፣ እንደ ፈጠራቸው እንዲኹ ደግሞ፣ “ጊዜያትንና ዘመናትን የሚለውጣቸው” (ዳን. 2፥21) የዘመናት ባለቤትና ፈጣሪ ርሱ ብቻ ነው።

እግዚአብሔር ለመላለሙ ወይም ለሰው ልጅ ኹሉ ዘመናትና ጊዜያትን የሰጠበትን አንዱን ምክንያት ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ ይገልጠዋል፤ “ምናልባትም እየመረመሩ ያገኙት እንደ ሆነ፥ እግዚአብሔርን ይፈልጉ ዘንድ በምድር ኹሉ ላይ እንዲኖሩ የሰውን ወገኖች ኹሉ ከአንድ ፈጠረ፥ የተወሰኑትንም ዘመኖችና ለሚኖሩበት ስፍራ ዳርቻ መደበላቸው። ቢኾንም ከእያንዳንዳችን የራቀ አይደለም።” (ሐ.ሥ. 17፥26-27) ይለናል። በዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ውስጥ የእግዚአብሔርን አያሌ መግቦቶችን እንመለከታለን፤ ለምሳሌ፦ እግዚአብሔር ሰዎችን መፍጠር ብቻ ሳይኾን፣ ዝርያዎቻቸውን ኹሉ ከአንድ ወገን ወይም ነገድ ወይም ደም ፈጥሮ ቦታቸውንም ወይም መኖሪያ ስፍራቸውንም ጭምር ወስኖአል።

በተጨማሪም፣ “የተወሰኑትንም ዘመኖችና ለሚኖሩበት ስፍራ ዳርቻ መደበላቸው።” ይላል፤ በአምላከዊ መግቦቱ የምንኖርበትን ዳርቻ ብቻ ሳይኾን፣ ዘመናትንም ጭምር ወስኖ የሰጠን ርሱ ነው።  ስለዚህም ለምን እንደ ሰጠን በትክክል ማስተዋል ይገባናል፤ ሙሴ፣ “በልብ ጥበብን እንድንማር፥” (መዝ. 90፥12) ብሎ በአጭሩና እንደ ሸረሪት ድር በተመሰለው ዕድሜአችን ምን ማድረግ እንዳለብን በማስተዋል እንደ ጸለየው፣ ዘመን የመጨመሩን እውነት እጅግ ማስተዋል አለብን።

እግዚአብሔር በአምላካዊ መግቦቱ የሰጠን ዕድሜ ዋና ዓላማው፣ ሰዎች ኹሉ ርሱን እንዲፈልጉ ብዙ ዕድልን ለመስጠት ነው፤ ቅዱስ ጳውሎስ ለአቴና ጠቢባን፣ “እግዚአብሔርን ይፈልጉ ዘንድ በምድር ኹሉ ላይ እንዲኖሩ” ብሎ እንደ ተናገረው፣ የተሰጠን ዕድሜ ርሱን በመፈለግ እንተጋ ዘንድ ነው። የምንኖረው፣ የምንንቀሳቀሰውና ያለነው በመጋቢው አምላክ መግቦት ነውና። እናም እንደ ኤርምያስ እንዲህ እንጸልይ፤ “ያልጠፋነው ከእግዚአብሔር ምሕረት የተነሣ ነው፤ ርኅራኄው አያልቅምና።” (ሰቆ. 3፥22) እንዲል። እግዚብሔር ዘመንን የሰጠን፣ እንደ ኃጢአታችን ፍርድ የማይገባን ስለ ኾንን አይደለም፤ በመግቦቱ ለፍጥረቱ የሚራራ አምላክና ፈጣሪያችን ስለ ኾነ፤ ርሱን እንፈልገውም ዘንድ ነው። ርሱ ፍጻሜ ለሌለው ትውልድ መኖሪያ ቦታችን ይኾነን ዘንድ በድጋሚ ልለምናችሁ፣ እንደ ሙሴ እንጸልይ፣ እንዲህ ብለን፣ “ጥበብን የተሞላ ልብ ይኖረን ዘንድ፣ ዕድሜያችንን መቊጠር አስተምረን” (ዐመት)፤ አሜን!

“ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን በማይጠፋ ፍቅር ለሚወድዱ ሁሉ ጸጋ ይሁን።” (ኤፌ. 6:24) አሜን።

No comments:

Post a Comment