Sunday 9 June 2024

ሰኔ 16 ቃለ አዋዲ፤ ሰኔ 23 ማኅበረ አኀው አይቀርም!

 

“ዘወትር እየተገናኘን ርስ በርሳችን እንበረታታ እንጂ አንዳንዶች ማድረግ እንደ ለመዱት መሰብሰባችንን አንተው፤ ይልቁንም የጌታ መምጫ ቀን መቃረቡን እያስታወሳችሁ ይህን ነገር በይበልጥ አድርጉ።” (ዕብ. 10፥25)

የዕብራውያን አማኞች፣ መንፈሳዊ ኅብረትን ስደትን ከመፍራት የተነሣ ተወት አድርገው ነበር፤ እናም ብዙዎች ወደ መንፈሳዊ ኅብረቶች ከመሄድ ይልቅ፣ በየቤቶቻቸው ተቀምጠው ነበር። ሌሎች ደግሞ አይሁድና አሕዛብ በአንድነት ኅብረት ሊያደርጉ አይገባቸውም የሚለውን ትችትና ነቀፋ በመፍራት ኅብረት ከማድረግ አፈግፍገው ነበር። ነገር ግን እኒህና ሌሎች በቂ የሚመስሉ ምክንያቶች ቢኖሩም፣ ከመንፈሳዊ ኅብረት መታጎል ወይም መቅረት ፍጹም ትክክል አይደለም።



የክርስቶስ አማኞች ርስ በራሳቸው ሊተናነጹ፣ የክርስቶስ አካል ተባብሮ ይጸና ዘንድ፣ ዘወትር መገናኘት ይገባቸዋል። አንዱ ሌላውን ሊያንጽ፣ ኅብረት እጅግ ወሳኝ ነገር ነው፤ አንዱ ከሌላው ጋር ጸጋ ለመካፈል፣ ዘወትር በቅድስት ኅብረት መገናኘት ይገባል፤ እግዚአብሔር የሚያጸናውና እጅግ የሚወድደው መንፈሳዊ ኅብረትን ነው። ጌታችን ኢየሱስ እንደ ተናገረው፣ “ኹለት ወይም ሦስት በስሜ በሚሰበሰቡበት በዚያ በመካከላቸው እሆናለሁና።” (ማቴ. 18፥20)።

በመንፈሳዊ ኅብረት ውስጥ “የአንድ ብርቱ” የለም! ሕያዋን ብልቶች በጋራና በአንድነት እንዲሠሩ ነው የተባለላቸው፤ ከሰውነታችን አካላት የማያስፈልግ ብልት እንደ ሌለ እንዲኹ፣ በኅብረት ውስጥ የማያስፈልግ ሰው፤ ጸጋ አልባ አማኝም የለም! ስለዚህም አማኞች አንዳችን ለሌላችን እጅግ አስፈላጊዎች ነን። ከኅብረት ለመቅረት ከምናቀርባቸው ይልቅ፣ ወደ ኅብረት በናፍቆትና በደስታ ለመምጣት የሚረዱን አያሌ ምክንያቶች አሉን። እግዚአብሔር አንድነታችንንና የመንፈስ ኅብረታችንን ሲሻ፣ መለያየትና ለመለያየት ሰበብ መፈለግ ከመንፈስ ቅዱስ አይደለም!

ንጹህና እንከን አልባ ኅብረት በምድር ላይ የለም፤ ኹላችን ክርስቶስን በማመናችን በዚህ ምድር ያለው መከራና ፈተና የሚወገድልንም አይደለንም፤ ዳሩ ግን በመታገልና በመጋደል በመቃተትና በምጥ እናልፍ ዘንድ አለን። አማኞች ኹላችን በድካም፣ በመቃተት፣ በምጥ፣ በመከራና በስደት … ብናልፍም፣ በመንፈስ ቅዱስ ዕርዳታና ኃይል ተስፋችንን እወርሳለን። የምንናፍቃት ፍጽምት ኅብረት በጉ ባለበት በሰማይ አለችን፤ እስከዚያው ድረስ በብዙ እንተጋለን!

እናም ወንድሞችና እህቶች ሆይ፤ በተለያየ ምክንያት ያፈረሳችሁትን የኅብረቶቻችሁን “መሠዊያ” አድሱ፤ ታድሱም ዘንድም እኒህን ኹለቱን ኅብረቶች በፍቅር እንጋብዛችኋለን፤ ቃለ አዋዲ በሚሊኒየም አዳራሽ በሰኔ 16 በሚያዘጋጀውና ማኅበረ አኀው ደግሞ በሰኔ 23 በደብረ ዘይት አዋሽ ሕንጻ ላይ በሚያደርጉት ጉባኤ ወይም የመንፈስ አንድነት ላይ ትገኙ ዘንድ በጌታ ፍቅር ጋብዘናችኋል።

“በማያቋርጥ ፍቅር ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን ለሚወዱ ሁሉ ጸጋ ይሁንላቸው።” (ኤፌ. 6፥24)`

2 comments:

  1. አሜን አሜን

    ReplyDelete
  2. ተባርከሀል ወንድሜ! ፀጋው ይብዛልህ።

    ReplyDelete