Friday, 17 November 2023

ነገረ ሥላሴን የምናጠናበት ምክንያት (ክፍል ፮)

Please read in PDF

ካለፈው ቀጠለ …

4.2. አካል

“አካል ማለት የሚታየውና የሚጨበጠው ቁስ አካል አይደለም። አካል ‘ፍጹም ምሉዕና ቀዋሚ እኔ ባይ ማለት ነው’”[1]

ብዙ ሰዎች አካል የሚለውን ፅንሰ ዐሳብ የሚረዱት፣ ከሚዳሰስ ቍሳዊ ነገር ጋር በማያያዝ ብቻ ነው። በርግጥ የሰው ኹለንተና አካል ተብሎ መጠራቱ እውን ቢኾን፣ የሰው አካላዊነት ከዚህ የዘለለ ነው፤ ማለትም አካላዊነት ማንነትንና እኔነትን የሚያካትት ነውና። ስለዚህ አካል ስንል፣ የሰውን ወይም የአንድን ነገር የሚታየውን ቍሳዊ ነገር ብቻ እንዳልኾነ ልናስተውል ይገባል።

በእግዚአብሔር ወይም በቅድስት ሥላሴ ዘንድ ስላለው ፍጹም አካል ስናወራ፣ ከሰው በተለየ መልኩ ቢኾንም፣ የሰው አካል ከእግዚአብሔር ጋር የሚያመሳስለውም ነገር እንዳለ ሳንዘነጋ ነው። ከእግዚአብሔር አምላክ ጋር ከተዛመድንባቸው ወይም እግዚአብሔርን ከመሰልንባቸው “መልክና አምሳል” (ዘፍ. 1፥26) አንዱ፣ አካል ነው ብለን መናገር እንችላለን።

“… ሰው በዕውቀቱ፣ በኃይሉና በአንድ ስፍራ በመገኘቱ ውሱንነት፣ ዝቅተኛነት፣ የበታችነት … ወዘተ የሚሰማው ቢኾንም፣ በእግዚአብሔር አካልነት ላይ ግን ምልአት እንጅ ጕድለት የለም፤ እርሱ በሰላምና በአግባብ ኹሉን አስቦ እንደ ፈቃዱ ይፈጽማል።

እንደዚሁም ሰው ኀጢአተኛ በመኾኑ በአካልነቱ የሚታዩበት ማናቸውም ዐይነት የክፋት ዐሳብ፣ የሞት ፍርሀት፣ የጠባይ ለውጥ፣ የበደል ስሜት፣ የከንቱነት አስተሳሰብ … ወዘተ በእግዚአብሔር አካልነት ፈጽሞ አይገኙም። በዚህ ፈንታ በእግዚአብሔር ዘንድ ጽድቅና ቅድስና ይሰፍናሉ።”[2]

አካል በዓለመ ግዘፍ ብቻ ያይደለ፣ በዓለመ መንፈስም ጭምር የሚገኝ መኾኑን አለቃ መሠረት ያብራራሉ።[3]

“በሥሉስ ቅዱስ የሚገኙ ሦስት አካላት በዐለመ መንፈስ ያሉ ቢኾኑም፣ አስማተ አቃኒም ማለት በጽንዕ የሚገኙ ስሞች ናቸው። እነርሱም አብ፣ ወልድ፣ መንፈስ ቅዱስ ሲባሉ በዘለዓለም ሲኖሩ የነበሩ አስማት ተብለው ይጠራሉ። በዓለመ መንፈስ የሚገኙ ፍጡራን አካላት የሰው ነፍስና መልአክ ግን እያንዳንዱ አካል በለባዊነት በነባቢነት በእስትንፋስነት ክዋኔ ፍጹም አካል እንዳላቸው ያስታውቃሉ።”[4]

ስለዚህም እያንዳንዱ አካል ፍጹም አምላክ፤ ፍጹም ኅላዌ፣ እግዚአብሔር ባሕርያት ያሉት ነው። ይህን ስንል ሦስት አማልክት አንልም፤ አንድ አምላክ እንጂ። ስለዚህም ሥላሴ በማይከፋፈል ኅላዌ፤ በማይጠፋፋ አካላት ውስጥ በአንድ መለኮትነት ለዘለዓለም ጸንቶ ይኖራል። አሜን!

ይቀጥላል …

 



[1] አበራ በቀለ(ሊቀ ጉባኤ)፤ ትምህርተ ሃይማኖትና ክርስቲያናዊ ሕይወት፤ ገጽ 75

[2] ኮሊን ማንሰል (ቄስ)፤ ትምህርተ እግዚአብሔር፤ ገጽ 217-18

[3] መሠረት ስብሐት ለአብ(አለቃ) ሥላሴ በተዋሕዶ፤ ገጽ 84

[4] ዝኒ ከማኹ

4 comments:

  1. አሜንንን ክብር ሁሉ ለኢየሱሰ ክርስቶስ ይሁን

    ReplyDelete
  2. የሰው ዘር ሁሉ በሕይወት የመኖር ትርጉም የሚኖረው፣ ጌታውንና መድሃኒቱን ኢየሱስን ዝቅ ብሎ በማወደስና በማምለክ ነው።

    ReplyDelete
  3. ንፁህ የወንጌል መልዕክት የያዘ

    ReplyDelete