Tuesday, 24 October 2023

ነገረ ሥላሴን የምናጠናበት ምክንያት (ክፍል ፬)

 Please read in PDF

ካለፈው ቀጠለ …

3.4. ከሰውም ኾነ ከሌላው ፍጥረት ጋር ያለንን ግንኙነት የተሻለ ያደርገዋል

ሰው ከእግዚአብሔር ጋር በኤደን ገነት በቅድስና ይመላለስ ሳለ፣ ግንኙነቱ ፍጹምና እንከን አልባ ነበር፤ (ዘፍ. 2፥8፡ 15፡ 25)። ነገር ግን ሰው በኀጢአት በወደቀ ጊዜ፣ ኀጢአት የሰውንና የእግዚአብሔርን ግንኙነት አበላሸ። ከዚህም የተነሣ ሰው፣ ወደ ወደቀውና ወደ ተሰበረው ዓለም መጣ፤ እግዚአብሔር ግን ለዘላለም ጸንቶ በሚኖረውና በማይለወጠው የቅድስናና የፍቅር ባሕርይው ጸንቶ አለ፤ (ዘጸ. 3፥14፤ ሚል. 3፥6፤ ኢሳ. 48፥12)።

ስለዚህም መለወጥ በባሕርይው የሌለ እግዚአብሔር፣ ሰውን ፍለጋ ወደ ተሰበረው ምድር ፍለጋ “አዳምን ጠርቶ፦ ወዴት ነህ?” እያለ መጣ (ዘፍ. 3፥9)። በዚህም የሰው ፈጣሪና ወዳጁ መኾኑ ታወቀ፤ እናም በሥላሴ ዘንድ የማይለወጥና ሊቀየር የማይችለው የፍቅር ግንኙነት ወደ ሰው ፈሰሰ። ሰዎች ከወደቁ በኋላ እንኳ እግዚአብሔርን ሰውን በመውደድ ፍቅሩን ገለጠ (ዮሐ. 3፥16)፤ ከዚህ የተነሣ በእርሱና በእኛ መካከል የወዳጅነት ፍቅር እንዲኖር ወደደ፤ ሕዝቡን የሚወድ አባት ይባል ዘንድ ፈቀደ (ዕብ. 12፥5-10)።

ሰዎች በእስር ቤት ውስጥ በአንድነት[ፍቅር ሳይኖራቸው] ሊኖሩ ይችላሉ፤ ነገር ግን እንዲህ ባለ መንገድ ሳይኾን፣ በሥላሴ ዘንድ የነበረው እውነተኛ ፍቅር ወደ እኛ ተቈረሰ፤ “እኔንም የወደድህባት ፍቅር በእነርሱ እንድትሆን እኔም በእነርሱ፥ ስምህን አስታወቅኋቸው አስታውቃቸውማለሁ።” (ዮሐ. 17፥27) እንዲል፣ በሥላሴ መካከል የነበረው ፍቅር ወደ እኛ ፈሰሰ፤ ፍቅር በንግግር እንዲሰምርና እንዲያድግ እርሱም እኛን አናገረን፣ ፊት ለፊት ሊገናኘንም ሥጋን ለብሶ ወልድ በተለየ አካሉ ተገለጠ።

ሥላሴ ይዋደዳሉ፤ የእነርሱ ፍቅር ወደ እኛ ስለ ፈሰሰም፣ እኛም እንዋደዳለን፤ እግዚአብሔር ስለ ወደደን እንወደዋለን፤ ሌሎችንም ለመውደድ አቅም እናገኛለን፤ “ወዳጆች ሆይ፥ ፍቅር ከእግዚአብሔር ስለ ሆነ፥ የሚወደውም ሁሉ ከእግዚአብሔር ስለ ተወለደ እግዚአብሔርንም ስለሚያውቅ፥ እርስ በርሳችን እንዋደድ።” (1ዮሐ. 4፥7፡ 10) እንዲል።

እንግዲህ፣ “ሥላሴ አንድ ብቻ ነው ወይም አንድ ገጽ ነው” ማለት ፍቅርን ያጠፋል፤ ወይም በሥላሴ መካከል ያለን ፍጹም ፍቅርን የሚያጠፋ ነው። በሦስቱ አካላት መካከል ፍጹም መፈቃቀር አለ (ዮሐ. 3፥35፤ 14፥31፤ 17፥4)፤ እግዚአብሔር ይህን ፍቅሩን ልጁን በመስጠቱ ምን ያህል ታላቅ እንደ ኾነ አሳይቶአል፤ (ዮሐ. 3፥16፤ ሮሜ 8፥32፤ ኤፌ. 2፥4፤ 3፥19፤ 1ዮሐ. 4፥9-10)። ይህ ፍቅር ደግሞ በክርስቶስ ኢየሱስ የሚያምኑ ኹሉ፣ በአብ ፊት ክብሩን እንዲያዩ ጌታችን በመጸለዩና ተስፋን በመስጠቱ፣ የእግዚአብሔር ፍቅር በእያንዳንዱ አማኝ ላይ ማረፉ ሊስተባበል አይችልም (ዮሐ. 6፥37-40፤ 17፥20-21፡ 24፤ ገላ. 2፥20)።

እኛ በኀጢአት ስለ ወደቅንና ስለተዳደፍን፣ ፍቅር ለእኛ እንደ ትእዛዝ ነው፤ ለሥላሴ ግን ኀጢአት በእርሱ ዘንድ ስለሌለ፣ ፍቅር ባሕርይው ነው። በሥላሴ ዘንድ ለውን ፍጹም መፈቃቀር ያየ አማኝ ግን ከሌሎች ጋር ያለው ግንኙነቱ በፍቅር የተመላ ነው።

 

ይቀጥላል …

No comments:

Post a Comment