Friday 6 October 2023

በአጭሩ፣ ኢሬቻ የዋቄፈታ አማኞች አምልኮአዊ በአል ነው!

Please read in PDF

በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ውስጥ የሮማ ቄሳራውያን ያህል፣ ለባህላዊ ሃይማኖት መስፋፋት ታላቅ አስተዋጽዖ ያደረገ አካልን መጥቀስ አይቻልም። በተለይም እኒህ ነገሥታት ክርስቲያኖችን ለማጥፋት ከተጠቀሙበት መንገድ አንዱ፣ ራሳቸውን እንዲመለኩ በማቅረብና ጣዖታትን እንዲመለኩ አዋጆችን በማውጣት ነው፤ የሚቃወሙአቸውን ኹሉ ደግሞ ያለ አንዳች ርኅራኄ በመፍጀት ተካካይ የላቸውም።[1] የኢየሱስን ጌትነት አውጀው፣ የቄሳራውያንን አል ጌትነት መቃወምና ጣዖታትን ፍጹም መጠየፋቸው ለክርስቲያን ወገኖች ብርቱ የስደትና የሰማዕትነት ዋና ምክንያት ነበር።[2] በተለይም በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ውስጥ የቤተ ክርስቲያን የስደት ዘመን ወይም ዘመነ ሰማዕታት በመባል የተጠራበት አንዱ ምክንያት፣ የክርስቲያኖች ቄሳራዊ አምልኮን፣ ሮማዊና ሌሎችንም ባህላዊ ሃይማኖቶችን መጠየፋቸውና አለመቀበላቸው ነበር።[3]

ከፖለቲካውም ቅርጽ አንጻር፣ የሮም ባህላዊ ሃይማኖት ልክ እንደ መንግሥቱ ጠባይ፣ ሌሎችን ሃይማኖቶች አቃፊና ተቀባይ ነበር። ጌታችን ኢየሱስ በነበረበት ዘመን፣ አይሁድ በሮማውያን ቀንበር ሥር ቢኾኑም፣ ያህዌን ከማምለክ አልተከለከሉም ነበር። አንድ ሰው የሮማውያንን ባህላዊ ሃይማኖት ከተቀበለና ከተገበረ፣ የራሱንም ምስል እስከ ማምለክ መድረስ ይችላል። ምክንያቱም ባህላዊው ሃይማኖት ልክ እንደ ሕዝብ አንድነት መጠበቂያ ያገለግል ነበርና።[4] ኹሉንም ሃይማኖቶች ከባህል ጋር ማዳበል ይቻል ነበር።[5]

ለምሳሌ፦ በኢትዮጵያ ውስጥ በታላቅ ድምቀት የሚከበሩት የመስቀል ደመራና ዕንቁጣጣሽ፣ ጥንተ በአላቸው መንፈሳዊ እንዳልነበረ ይታመናል።[6] ነገር ግን ከክርስትና ወደ ኢትዮጵያ መግባት ጋር በተያያዘ መስቀል ደመራ ከመስቀል በኣል ጋር፣ ዕንቁጣጣሽ ደግሞ ከቅዱስ ዮሐንስ ጋር እንደ ተያያዘ ይተረካል። እስከ ዛሬም ድረስ ግን የመስቀል ደመራ እሳት አወዳደቅና ከቃጠሎው በኋላ ዓመዱን መቀባት፤ ወደ ቤት ይዞ መሄድ እንዳለና ይህም ከጥንት አምልኮ ጣዖት ጋር ተያያዥነት አለው የሚሉ አሉ።[7]

በአገራችን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ፣ ባሕላዊ እምነቶች ከቀደሙት ጊዜያት ይልቅ፣ ፖለቲካዊና ሕጋዊ ሽፋን በግልጥ ተሰጥቶአቸዋል፤ ከዚህም የተነሣ ቃልቻና ጥንቍልና ሳይቀር፣ በሕግ ተመዝግበው “እምነታቸውንና ልምምዶቻቸውን” በአደባባይ መስበክና ማከናወን ከጀመሩ ሰንበትበት ብለዋል። የዋቄፈናው ኢሬቻም የዚህ አንዱ ነጸብራቅ ነው፡፡

እውነተኛዪቱ የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ተግዳሮቶቿ በመልክና በይዘት በርክተውባት ከፊት ለፊትዋ ተደቅነዋል። እናም ወደፊት እንደ ቄሣር፣ “ወይ ክርስትናችሁን ወይ ኢሬቻችንን ምረጡ” የሚሉ ስለ መምጣታቸው ነቢይ መኾን አያሻም!

(“ዋቄስትና” ከሚለውና ካልታተመው መጽሐፍ ከገጽ 24-27 የተወሰደ)



[1] Frend WHC. Martyrdom and Persecution in the Early Church, 6. extension of power, 41

[3] አባ ጐርጐርዮስ (ሊቀ ጳጳስ)፤ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ በዓለም መድረክ፤ ገጽ 35-46

[4] Frend WHC. Martyrdom and Persecution in the Early Church, 9

[5] በታሪክ ጌታ ኢየሱስ ራሱ ከሚመለኩ አማልክት መካከል እንደ አንዱ እንዲቈጠር፣ በጢባርዮስ ቄሳር ጥረት ተደርጎ ነበር፤ አልተሳካም እንጂ። https://www.newadvent.org/fathers/250102.htm Eusebius’ Church History 2.2.1-3። አንዳንዶች ደግሞ በተቃራኒው የክርስትና ትምህርት እየበረታ፤ እየወረሰ ሲመጣና ባህላዊውን አምልኮ ሲቃረን ተመልክተው፣ ክርስቶስንም ለማጥላላት ብለው፣ በዘመኑ ከነበረው ታላቁ ፈላስፋና መናኒ ከነበረው ግሪካዊው ቲያና አፖሎኒየስ ጋር ሊያወዳድሩትና ዝቅ ሊያደርጉት አስበው ነበር። Arthur James Mason; The Persecution of Diocletian: A Historical essay, pp. 58-60

[6] ጸጋዬ ገብረ መድኅን(ሎሬት) (አሰናኝ ኤርሚያስ ሁሴን)፤ ኢትዮጵያ ታሪክ ወይስ ተረት፤ 2012 ዓ.ም፤ ገጽ 123-125

[7] ሀብተ ማርያም አሰፋ(ዶ/ር)፤ 1985 ዓ.ም፤ የኢትዮጵያ ታሪክ ጥያቄዎችና ባህሎች፤ ገጽ 230 እና 232 

No comments:

Post a Comment