Wednesday 4 October 2023

ነገረ ሥላሴን የምናጠናበት ምክንያት (ክፍል ፫)

 Please read in PDF

ካለፈው ቀጠለ …

3.3. የፍጥረት ዐላማን መረዳት

እግዚአብሔር፣ በማይቀየረውና ሊለወጥ በማይችለው (ሐ.ሥ. 2፥23)፣ በዘላለም ዕቅዱ (ኤፌ. 3፥10-11)፣ ፍጥረትን የፈጠረው ለራሱ ክብርና ዓላማ ነው። ለራሱ ዓላማ ስለ ፈጠረውም፣ ፍጥረት ክብሩን ያውጃል፤ (ኢሳ. 43፥6-7)። ለዚህም ነው፣ መጽሐፍ ቅዱስ፣ የእግዚአብሔርን ኅልውና ሲያስረዳ፣ “በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን ፈጠረ።” በማለት ስለ እግዚአብሔር ማብራሪያ ባለመስጠት፣ የፍጥረትን መፈጠር አስደናቂ ተግባር በመተረክ የሚጀምረው። ፍጥረትም የተፈጠረበትን ዓላማ ስለሚያውቅ፣ እግዚአብሔርን ገልጦ ያሳያል፤ ለፈቃዱም በግልጥ ይታዘዛል።



“ … አሁን ግን እንስሶችን ጠይቅ፥ ያስተምሩህማል፤ የሰማይንም ወፎች ጠይቅ፥ ይነግሩህማል። ወይም ለምድር ተናገር፥ እርስዋም ታስተምርሃለች፤ የባሕርም ዓሣዎች ይነግሩሃል። የእግዚአብሔር እጅ ይህን እንዳደረገ ከእነዚህ ሁሉ የማያውቅ ማን ነው?” (ኢዮ. 12፥7-9)

ሰማያት የእግዚአብሔርን ክብር ይናገራሉ፥ የሰማይም ጠፈር የእጁን ሥራ ያወራል። ቀን ለቀን ነገርን ታወጣለች፥ ሌሊትም ለሌሊት እውቀትን ትናገራለች። ነገር የለም መናገርም የለም፥ ድምፃቸውም አይሰማም።” (መዝ. 18፥1-3)

“… ዓለሙንና በእርሱ ያለውን ሁሉ የፈጠረ አምላክ እርሱ የሰማይና የምድር ጌታ ነውና እጅ በሠራው መቅደስ አይኖርም፤ እርሱም ሕይወትንና እስትንፋስን ሁሉንም ለሁሉ ይሰጣልና አንዳች እንደሚጎድለው በሰው እጅ አይገለገልም። ምናልባትም እየመረመሩ ያገኙት እንደ ሆነ፥ እግዚአብሔርን ይፈልጉ ዘንድ በምድር ሁሉ ላይ እንዲኖሩ የሰውን ወገኖች ሁሉ ከአንድ ፈጠረ፥ የተወሰኑትንም ዘመኖችና ለሚኖሩበት ስፍራ ዳርቻ መደበላቸው። …” (ሐ.ሥ. 17፥24-27)

እነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ፍጥረት፣ የእግዚአብሔርን ክብር አንጸባራቂና ዓላማውን በመረዳት ክብሩን የሚገልጡ መኾናቸውን በግልጥ ይናገራሉ። በሌላ ስፍራ ቅዱስ ጳውሎስ፣

“… ስለ እግዚአብሔር ሊታወቅ የሚቻለው ለእነርሱ ግልጥ ነው፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር ለእነርሱ ግልጥ አድርጐታል። ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ የማይታየው የእግዚአብሔር ባሕርይ ይኸውም ዘላለማዊ ኀይሉና መለኮትነቱ፣ ከፍጥረቱ በግልጽ ይታያል፤ …

በማለት እግዚአብሔር አምላክን በሥነ ፍጥረቱ ማወቅ፣ በዓለም ለሚገኙ ሕዝቦች[ለአሕዛብ ጭምር] ኹሉ የተሰጠ የተፈጥሮ ጸጋ እንደ ኾነ በግልጥ ተናግሮአል። ከዚህ የተነሣ ፍጥረት ለተራ ተግባር አልተፈጠረም። እንዲያውም እግዚአብሔር ለመኖሩና ኅልውናው ፍጹም ለመኾኑ ብርቱ ማስረጃ ነው።

አንድ እውነት አንስትም፤ ፍጥረት የቅዱሳት መጻሕፍት ያህል፣ የእግዚአብሔርን ጥልቅ ዕውቀት አልያዘም፤ ይኹንና የእግዚአብሔር ባሕርይ ማለትም፣ ዘላለማዊ ኀይሉና መለኮትነቱ በፍጥረቱ በኩል ተገልጦአል። ስለዚህም ፍጥረት የተፈጠረው ለክብሩ ነው፤ ሲድንም የሚድነው ለክብሩ ነው። የእኛ መኖር በራሱ ጥቅም አይደለም፤ ነገር ግን መኖራችንም፤ መሞታችንም መዳን የሚባለው ለክብሩ ስንኖር ብቻ ነው። “ሁሉ ከእርሱና በእርሱ ለእርሱም ነውና፤ ለእርሱ ለዘላለም ክብር ይሁን፤ አሜን።” እንዲል (ሮሜ 11፥36)። በሌላ ስፍራም፣ “… በሰማይና በምድር ከምድርም በታች ያሉት ሁሉ በኢየሱስ ስም ይንበረከኩ ዘንድ፥ መላስም ሁሉ ለእግዚአብሔር አብ ክብር ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ እንደ ሆነ ይመሰክር ዘንድ ነው።” (ፊል. 2፥10-11) ተብሎ እንደ ተነገረው፣ የፍጥረት የመዳኑና የመጨረሻውም ግብ ለእግዚአብሔር ክብርንና አምልኮን ማምጣት ነው።

“እግዚአብሔር ለእኛ ምንም ነገር ቢያደርግ፣ ለማንም ምንም ነገር የማድረግ ዕዳ ስላለበት ሳይኾን፣ ከጸጋው የተነሣ ብቻ ነው። እግዚአብሔር ለኹሉም ሕይወትን ስለሚሰጥ፣ ደግሞም ኹሉንም አጽንቶ ስለሚይዝና የኹሉንም ዐላማ ስለሚወስን ለዘላለም ክብር ሊሰጠው ይገባል። ለእንዲህ ያለው አምላክ የአማኞች የዘወትር ውዳሴ፣ “ለእግዚአብሔር ክብር ይኹን፣ ታላቅ ነገር አድርጓልና!” የሚል መኾን አለበት።”[1]

በሰማይም ያለው ምስጋና ይህ ነው፤

ሀያ አራቱ ሽማግሌዎች በዙፋን ላይ በተቀመጠው ፊት ወድቀው፥ ከዘላለም እስከ ዘላለም በሕይወት ለሚኖረው እየሰገዱ፦ ጌታችንና አምላካችን ሆይ፥ አንተ ሁሉን ፈጥረሃልና ስለ ፈቃድህም ሆነዋልና ተፈጥረውማልና ክብር ውዳሴ ኃይልም ልትቀበል ይገባሃል እያሉ በዙፋኑ ፊት አክሊላቸውን ያኖራሉ።” (ራእ. 4፥10-11)።

ፍጡር ኹሉ እግዚአብሔርን ሲያመሰግን፣ ሰው ብቻውን እንደሚያመሰግን ሊያስብ አይገባም። መላለሙ እግዚአብሔርን ያመሰግናል፤ ጌታችን ኢየሱስ፣ “እነዚህ ዝም ቢሉ ድንጋዮች ይጮኻሉ” ብሎ እንደ ተናገረው፤ (ሉቃ. 19፥40)

ይቀጥላል …



[1] የአፍሪካ መጽሐፍ ቅዱስ ማብራሪያ፤ ገጽ 1323

No comments:

Post a Comment