Sunday 20 November 2022

ተሐድሶን ለማጥፋት መወሰድ ያለባቸው ርምጃዎች! (ክፍል 1)

በእግዚአብሔር ቃልና በእግዚአብሔር መንፈስ ተፈጥሮ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንደ ሰደድ እሳት እየተቀጣጠለ ያለውን ተሐድሶን ለማጥፋት እንዴት ይቻላል? የሚለው ጥያቄ፣ የብዙ ዓመታት ጥያቄ ነው፤ ከታሪክም ኾነ በዚህ ዘመን እየኾነ ካለው እውነታ እንደምንረዳው አንዳንድ አብያተ ክርስቲያናትና ግለሰቦች ተሐድሶ እንዲጠፋ ይፈልጋሉ፤ ነገር ግን እንዴት ሊያጠፉት እንደሚችሉ አያውቁም። ለምሳሌ፦ በአገራችን ታሪክ በአባ እስጢፋኖስና በተከታዮቹ ደቂቀ እስጢፋኖስ ላይ በኢትዮጵያውያን ነገሥታትና ጳጳሳት በተለይም በዐጼ ዘርዓ ያዕቆብ የተፈጸመውን ግፍ፣ ከአውሮፓ ታሪክም በአሥራ ስድስተኛው ክፍለ ዘመን በተነሣው የተሐድሶ እንቅስቃሴ ላይ ከካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የተደረገውን ተቃውሞ ማንሳት ይቻላል።

በአኹኑ ወቅት ደግሞ፣ በአገራችን የዐጼ ዘርዓ ያዕቆብ የመንፈስ ልጆች በመሠረቱት ማኅበር የቤተ ክርስቲያን አለኝታ ብሎ ራሱን የሰየመው ቡድን፣ ተሐድሶን ለማጥፋት እስከ አኹን ድረስ ብዙ ተግባራትን አከናውኖአል። በ2000 ዓ.ም የክስ ደብዳቤ ለቤተ ክህነት በማስገባትና በሂደቱ ላይ ከፍተኛ ጫና በማድረግ ያስወገዛቸውን የአገልግሎት ማኅበራትና አገልጋዮች ማስታወስ ለዚህ በቂ ማስረጃ ነው።

ቤተ ክህነትም ቢኾን፣ በአቋም ደረጃ ሳይቀር ተሐድሶ ምንፍቅና ነው ብሎ ያምናል። ከዚህም የተነሣ ቤተ ክርስቲያንን ይጎዳል ብሎ ስላሰበ፣ ብዙ የተሐድሶ እንቅስቃሴ አራማጆችና ደጋፊዎች የኾኑ አገልጋዮችን በማውገዝ፣ ከሥራና ከደመወዝ በማገድ፣ በማሳደድና ከሕዝብ በመለየት እንዲንገላቱ ብሎም የሚያምኑበትን ወንጌል እንዳይሰብኩ ለማድረግ ብዙ ሥራዎችን ተሠርተዋል። ኾኖም፣ ኹሉም ስደተኞች እየተራቡና እየተጠሙ አኹንም ወንጌልን ከመስበክ ወደ ኋላ አላሉም። እንዲኹም ወንጌልን በማመን የተሐድሶ ዓላማን የሚደግፉ ብዙ አገልጋዮችና ምእመናን በየጊዜው እየተጨመሩ ሄዱ እንጂ ሥራው መቆም አልቻለም።

ከዚህ በመነሣት ተሐድሶን ለማጥፋት ለሚፈልጉ ኹሉ ተሐድሶን ማጥፋት የሚችሉባቸውን ስልቶች ለማመልከት ወደድን። እነዚህ ስልቶችም የተረጋገጡ ስልቶች ስለኾኑ ማንኛውም የተሐድሶ ተቃዋሚ የኾነ ግለሰብ፣ ተቋምና እንቅስቃሴ ኹሉ ተቀብሎ በተግባር ቢያውላቸው ዓላማውን በእርግጠኝነት እንደሚያሳካ እንመሰክራለን።

1.  መጽሐፍ ቅዱን ከገጸ ምድር ማጥፋት

አንደኛው ስልት ተሐድሶ እንዳይስፋፋና ወደ ሰዎች እንዳይደርስ ካስፈለገ፣ መጽሐፍ ቅዱስን ከምድር ላይ ማስወገድ ነው። በማንኛውም ቦታ፤ በማናቸውም ቋንቋ የተጻፈውን መጽሐፍ ቅዱስ እንዳይሠራጭና እንዳይነበብ ማድረግ የተዋጣለት ተሐድሶን ማጥፊያ ስልት ነው። ይህን ማድረግ የሚችል አካል ካለ፣ ተሐድሶን ማጥፋት እንደሚችል በእርግጠኝነት መመስከር እንችላለን።

ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱስ በአኹኑ ወቅት በኹሉም ቋንቋዎች ተተርጕሞ እየታተመና እየተሠራጨ ነው። ከኹሉም የእምነት ተቋማት የኾኑ ብዙ ኢትዮጵያውያን መጽሐፍ ቅዱስን በራሳቸው ቋንቋ ማንበብ የሚችሉበትን ዕድል እግዚአብሔር ከፍቷል፤ ይህ ዕድል በሰው ልጅ እንዳልኾነና መጽሐፍ ቅዱስን ከማግኘትና ከማንበብ የሚከለክለን ማንም ግለሰብ ወይም ተቋም እንደማይመጣ እርግጠኞች መኾን እንችላለን። ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ እስካለና እስከ ተነበበ ድረስ ተሐድሶ አለና ተሐድሶን ማጥፋት አይቻልም ማለት ነው።

መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ቃል ነው፤ በማናቸውም ዘመን ማንም ያላስቆመውና ያልገታው ቃል ነው፤ በዘመናትም የሰዎችን ልጆች ሕይወት በመለወጥ አቻ ያልተገኘለት ቃል ነው፤ ለዚህም ነው ብዙዎች መጽሐፍ ቅዱስን በማንበብና ቃሉን በመስማት እየተለወጡ ያሉት። ለዚህም ነው ቅዱስ ቃሉ እንዲህ በማለት የሚናገረው፣

“ዘመኑ ቀርቦአልና የሚያነበው፥ የትንቢቱን ቃል የሚሰሙትና በውስጡ የተጻፈውን የሚጠብቁት ብፁዓን ናቸው።” (ራእ. 1፥3)

እናም መጽሐፍ ቅዱስ በሚነበብበትና በሚሰበክበት፤ እንዲሁም ሰምተው በሚታዘዙበት ቦታ ኹሉ ቅዱስ ቃሉ የቤተ ክርስቲያንን ሕይወት በመለወጥና የሰይጣንን መንግሥት በማፍረስ እያሸነፈና እያየለ ይሄዳል፤ አሜን።

የዛሬውን አያድርገውና አእመረ አሸብር እንዲህ ጽፎ ነበር!

ይቀጥላል …


No comments:

Post a Comment