Wednesday 18 August 2021

የደብረ ታቦሩ የስንፍና ጸሎት

 please Read in PDF

በአዲስ ኪዳን ቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ፣ ለጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የቀረቡ አያሌ ጸሎቶችን እናነባለን። ለጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከቀረቡ አንድ መቶ ሰማንያ ሦስት የሚጠጉ ጸሎቶች መካከል አንዱ ጸሎት፣ “መምህር ሆይ፥ በዚህ መኾን ለእኛ መልካም ነውና አንድ ለአንተ አንድም ለሙሴ አንድም ለኤልያስ ሦስት ዳሶች እንሥራ” (ማር. 9፥5) በማለት ቅዱስ ጴጥሮስ ያቀረበው ጸሎት ነው።

ወደ ደብረ ታቦር (ወደ መለወጥ/ወደ ክብሩ ተራራ) ጌታችን ኢየሱስ ሦስቱን ደቀ መዛሙርት (ጴጥሮስን፣ ዮሐንስና ያዕቆብን) ይዞ ሲወጣ፣ ኢየሱስ በፍጹም ክብሩ “በፊታቸውም ተለወጠ፥ ልብሱም አንጸባረቀ፤ አጣቢም በምድር ላይ እንደዚያ ሊያነጣው እስከማይችል በጣም ነጭ ኾነ።” የዚያን ጊዜ “ሊቀ ነቢያት” ሙሴና “ርዕሰ ባሕታዊያን” ኤልያስ በተራራው ላይ ሲከሰቱ፣ ቅዱስ ጴጥሮስ ተመለከተ። እናም በልቡ ፍንድቅ-ፍንድቅድቅ አለ!

ወዲያውም ወደ ኢየሱስ፣ ለእያንዳንዳችን የሚኾን ዳስ እንሥራ የሚል ጸሎትን አቀረበ። ጸሎቱ ውብና ያማረ ይመስላል። በርግጥም ከኢየሱስ ጋር ቤት ሠርቶ እንደ መኖር ያለ ምንስ ነገር አለ?! ግን መልካም ጸሎቶች ኹሉ ትክክለኛ ጸሎቶች አይደሉም። እናም ጴጥሮስ ያቀረበው ጸሎት የስንፍና እንጂ መልስን የሚያስገኝ ጸሎት አልነበረም። በርግጥም ጴጥሮስ፣ ሙሴና ኤልያስን በማየቱ ተደንቆ ፈነደቀ እንጂ፣ ሙሴና ኤልያስ ከኢየሱስ ጋር ያወሩት ምን እንደ ኾነ ቢያውቅ፣ እንኳን በዚያ ጎጆ ሊቀልስ በድንጋጤ ክው ብሎ ከተራራው ቸኩሎ በወረደ ነበር።

ኹለቱ ነቢያት በተራራው ከኢየሱስ ጋር የተነጋገሩት፣ “በክብርም ታይተው በኢየሩሳሌም ሊፈጽም ስላለው ስለ መውጣቱ ይናገሩ ነበር።” እንዲል፣ መሲሑ የሰውን ልጅ ለማዳን በኢየሩሳሌም ስለሚገጥመው ውርደትና ሞት ነበር። በአንድ ወቅት ጌታችን ኢየሱስ፣ “የሰው ልጅ ብዙ መከራ ሊቀበል፥ ከሽማግሌዎችም ከካህናት አለቆችም ከጻፎችም ሊጣል፥ ሊገደልም ከሦስት ቀንም በኋላ ሊነሣ እንዲገባው ቃሉን ገልጦ ሲናገር”፣ ቅዱስ ጴጥሮስ፣ “ወደ እርሱ ወስዶ ይገሥጸው ጀመር።” ይላል ቅዱስ መጽሐፍ የሚገስጸውም ልትሞት አይገባህም፤ አብረኸን ልትኖር፣ በክብር ልትመላለስ ይገባሃል ማለቱ ነበር። ምክንያቱም ጴጥሮስ ኢየሱስን እንደ መሲሕ ቢቀበለውም፣ ነገር ግን ሞቱን ፈጽሞ አልወደደለትም።

እናም ቅዱስ ጴጥሮስ በደብረ ታቦር ያቀረበው ጸሎቱ ቢሰማና ጎጆ በዚያ ቀልሶ ቢኾን፣ አይሁድ በቀላሉ ኢየሱስን ባገኙና መሲሐዊ የአገልግሎት ጉዞውን ባጨናገፉበት ነበር። ኢየሱስ ግን የጴጥሮስን የደብረ ታቦር ጸሎት ችላ ብሎት አለፈ። በሌላ ስፍራ ግን በብርቱ ቊጣ፣ “ወደ ኋላዬ ሂድ፥ አንተ ሰይጣን፤ የሰውን እንጂ የእግዚአብሔርን ነገር አታስብምና” ብሎ ገሰጸው። ምክንያቱም መሻትና ዐሳቡ ሙሉ ለሙሉ የሰው ነበርና! የእግዚአብሔር ፈቃድ ግን መሲሑ ዳስ እንዲቀልስ፣ በክብር ያለ ሕይወት እንዲመላለስ ሳይኾን በመስቀል መንገድ በኩል እንዲያልፍ ነውና! ይህን መንገድ ደግሞ ሥጋ ለባሽ ይጠየፈዋል እንጂ ፈጽሞ አይወደውም!

ብዙ ጊዜ በፈንጠዝያና በፍንደቃ ውስጥ ኾነን፣ አልያ በብርቱ ስብራትና ሐዘን ውስጥ ኾነን ለጸለይናቸው ጸሎት ኹሉ እግዚአብሔር ስላልመለሰልን ስሙ ይባረክ፤ አሜን። ጌታ ሆይ ስላልተመለሱ የስንፍና ጸሎቶቼ እባርክሃለሁ፤ አመልክሃለሁ! ምክንያቱም ከእግዚአብሔር ትልልቅ በረከቶች አንዱ ጸሎትን አለመመለሱም ጭምር ነውና!

ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን ባለመጥፋት ከሚወዱ ሁሉ ጋር ጸጋ ይሁን፤ አሜን። (ኤፌ. 6፥24)

2 comments:

  1. ሁልጊዜ መልካሙንና የቀናውን መንገድ የሚመራን እግዚአብሔር ይመስገን የሚረባንን እሱ ያውቃልና🙏

    ReplyDelete