Thursday 19 August 2021

ዕረፉ[አድቡ]! (መዝ. 46፥10) - ክፍል ፪

Please read in PDF

አንፈራም

የሚሰማው፣ የሚታየው፣ የሚነገረው፣ ጠላት በብሩ የሚጎስመውና የሚያጓራው ማጓራቱ እጅግ ጠንካራና አስፈሪ ነው፤ ነገር ግን እኛ አንፈራም፤ የማንፈራበት ምክንያት የማንፈራ ኾነን አይደለም፤ ነገር ግን ፍርሃትንና የፍርሃትን ምንጭ የሚሽር አምላክ ስላለን እንጂ። የማንፈራበት ምክንያት፦

1.   የሰራዊት አምላክ ከእኛ ጋር ነው፦ ይህ ቃል በዝማሬው ወስጥ እንደ አዝማጅ ተደጋግሞ ተጠቅሶአል (ቊ. 7፡ 11)፤ እርሱ “አምላካችን”፣ የሰራዊት አምላክ”፣ የያዕቆብ አምላክ” ነው። እርሱ በመግቦቱ ለያዕቆብ ወይም ለእስራኤል የተለየ ፍቅር አለው፤ በእርሱ ታምነዋልና። ስለዚህም የእርሱ ከእነርሱ ጋር መኖር ለእነርሱ ክብርና ሞገስ፤ መወደድም እነጂ የፍርሃት ምልክት አይደለም። እርሱ ከእነርሱ ጋር ስለኾነም ለዘላለም መጠጊያና ኀይላቸው፣ በመከራቸው ኹሉ የቅርብ ረዳታቸው (ቊ. 1)፣ መጠጊያቸው (ቊ. 7)፣ ከለላቸው ነው።

ስለዚህ ያለው ነገር እንደሌለ ቢኾን፣ መቅሰፍቶች ቢወርዱ፣ ጠላቶቻቸው ሽብር፣ ድንጋጤና ኹከትን ቢነዙም እስራኤል አምላኳ ከእርሷ ጋር ነውና ጨርሶ አትፈራም አትነዋወጥም፤ አትታወክም፤ አትንኮታኮትም! ይህ ለእስራኤል ብርቱ ተስፋ፤ የጸና እምነትም ነው!

2.   ብርቱዎችን ያቀልጣል (ቊ. 6)፦ ያህዌ ኤሎሂም ወደ ሕዝቡ ሲመጣና ሲቀርብ፣ ለሕዝቡ ከለላና መጠጊያ ሲኾን፣ እስራኤልን ያስጨነቁ ኹሉ ደግሞ በብርቱ ዐመጽ ቢነሳሱም ይወድቃሉ፤ ደግሞም ይቀልጣሉ። ችግሩና ንውጽውጽታው ምንም ያህል ብርቱ ቢኾን እግዚአብሔር ሲመጣ ይቀልጣል፤ ይወድቃል፤ ይንኮታኮታል።

3.   ከተማውን ያጸናል (ቊ. 4-5)፦ ብርቱዎች ጽዮንን ለማፍረስ ይቋምጣሉ፤ ይጎመጃሉ፤ ይከጅላሉ። እግዚአብሔር ግን በከተማይቱ ውስጥ ስላለ፣ ታላቅ ጥበቃውና ትድግናው አይለያትም። የሚፈልጓት አያገኟትም። ይህ ለጽዮን ከተማ ብርቱ ማጽናኛ ነው። እግዚአብሔር ከተማይቱን የማያስነካ ብቻ አይደለም፤ ደግሞም “ደስ እንደሚያሰኝ የውኃ ፍሳሽ(ወንዝ)” በማያቋርጥ በረከት፣ ጸጋን ክብር ለሕዝቡ ባርኮትን ይሰጣል።

ይህ ብርቱ ፈሳሽ አለመቋረጡ ብቻ ሳይኾን፣ የሚፈልቀው ከእገዚአብሔር ለሚወዳቸው ሕዝቡ መኾኑ ነው። ይህም ሕይወትን የሚሰጥ ንጹሕ ውኃ ከአብ (ኤር. 2፥13)፣ ከወልድ (ዘካ. 13፥1፤ ዮሐ. 4፥14)፣ ከመንፈስ ቅዱስ (ዮሐ. 7፥38) የተሰጠና ፈጽሞ የማያስጠማ ነው፤ ከተማይቱ እግዚአብሔር በመካከልዋ ስላለ ደስታወና በረከትዋ ፈጽሞ የማይነጥፍና የሚበዛ፤ የሚትረፈረፍም ነው!

4.   ጦርነትን ከምድር ያስወግዳል፦ የአሕዛብ መንግሥታት ትልቁ አቅም ጦርና የጦር ወሬ ነው። በዚህም ነው ብዙውን ዓለም በማንበርከክ የሚታወቁት። አሕዛብ በሰረገላና በፈረሶቻቸው ብዛት እንደሚመኩና እንደሚታመኑ ዳዊት ተናግሮአል (መዝ. 20፥7)፣ ነገር ግን ፈረሶቻቸውና ሠረገሎቻቸው አያድኑአቸውም (መዝ. 33፥17)፤ እግዚአብሔር በሚያልፈውና ቋሚ ባልኾነው ነገር የሚመኩትን ፈጽሞ አይወድምና (ዘዳ. 17፥16፤ መዝ. 147፥10፤ ኢሳ. 36፥9)።

ከዚህም የተነሣ እግዚአብሔር በሕዝቡ ላይ ከዳር እስከ ዳር የተነሣውን ጦርነት ያስወግዳል፤ ቀስትንም ይሰብራል፤ ጦርን አንክቶ፣ ጋሻውንም በእሳት ያቃጥላል። ፍጻሜው ኹለንተናዊውን የያህዌን የመዋጀት ዕቅድ የሚያነሳ ሲኾን፣ ለአኹን ግን እስራኤል ከገጠማት ከበባ የሚታደግ አምላክ መኾኑን የሚያስረግጥ ነው። አሕዛብ ይህን አይተው እግዚአብሔርን የሚያከብሩበት ቀን ይመጣል(ቊ. 10)። እግዚአብሔር አዲስ ቀን ሊያመጣ ጦርነትን ኹሉ ከምድር ፊት እንዲቆም አዞአልና!

ኑ! ተመልከቱ!

እግዚአብሔር ምን እንዳደረገ ኑ ተመልከቱ! እርሱ አስደናቂ ነገሮችን አድርጎአልና! ሕዝቡ እንዲታመኑበት አስፈሪ ነገሮችን ኹሉ ሽሮአልና፣ አሸናፊነቱን አሳይቶአልና፣ አሕዛብን ድል ነሥቶአልና፣ ከእንግዲህ ወዲህ በእርሱ ከተማ ላይ አንዳች ጥቃት አይሰነዘርምና፣ ሥራውን ኑና ተመልከቱ! እግዚአብሔር ውድመትን፣ ሽብርን፣ ጥፋትን፣ ኹከትን፣ መፍረስን፣ መንኮታኮትን አስወግዶአልና! ከተማይቱንና ሕዝቡን እንዳይናወጡ በማለዳ እጅግ ረድቶአልና፤ ይህን ድንቅ ሥራውን ኑ ተመልከቱ!

እግዚአብሔር እዲህ ያለ ድንቅ ሥራውን በመሲሑ አገልጋይ አደረገ፤ የያዕቆብ አምላክ ከእኛ ጋር ይኾን ዘንድ ማደሪያውን በመካከላችን አደረገ፤ በመላ ዓለሙ በሰው ልጆች ላይ ጠላት ያኖረውን አስፈሪነትና ብርቱ የሽብር ዲስኩር ይሽር ዘንድ መሲሑ ተገለጠ! መላለሙ ሰላም ይጎናጸፍ ዘንድ መሲሑ መጠጊያና ረዳታችን ሊኾን መጣልን! ከእንግዲህ ጠላት በእግዚአብሔር መንግሥት ላይ የሚሰነዝረው ጥቃት አቅም እስኪያጣ ድረስ መሲሑ ወደ ምድር ለመግቦትና ለትድግና መጣልን!

እንግዲያስ ዕረፉ!

እግዚአብሔር፣ ለእስራኤል በኹለመናዋ ሊታደጋት፣ ሊጠብቃት፣ ለመንግሥታት ሲናገር በሚያስተጋባ ድምጹ ሊጠነቀቅላት ኪዳን ሰጥቶአታል። አሕዛብ አስደናቂውን ሥራ እስኪመለከቱ ድረስ እግዚአብሔር ለእስራኤል ታላቅ ነገርን አድርጎአል። በዚህም የእርሱን ኹሉን ቻይነት በመታመን አርፈው ይቀመጡ ዘንድና ዐምባቸው እርሱ እንደ ኾነ በመተማመን ከራሳቸው ዝግጅት፣ ከአሕዛባዊ ትምክህት፣ በፈረስና በሰረገላ ከመታመን ዕረፉ! ተዉ! በቃ! ይላቸዋል!

እግዚአብሔርን ከፍ ከፍ እንዳታደርጉትና በመላ ዘመናችሁ ልዩ ስፍራ፣ ትክክለኛ ቦታ እንዳትሰጡ ካደረጋችሁ ወይም ከሚያደርጋችሁ ማናቸውም ተግባር ከእንግዲህ ዕረፉ፣ ከእንግዲህ ይበቃችኋል ሲል እናደምጠዋለን። እርሱ ሊረዳቸው ኹል ጊዜ የታመነ ነው፤ ከቶ አይተዋቸውም፤ እናም ይህን ከሚያዘናጋቸው ነገር እንዲያርፉና እንዲቆጠቡ ነገር ግን እግዚአብሔርን በማወቅ እስከ መጨረሻም በመጽናት እንዲመላለሱ ያስታውሳቸዋል። በርግጥም የእምነት ሕይወት በሚነዋወጠው ዓለም ላይ የማይነዋወጠውን የእግዚአብሔር ሉዓላዊነትና ጌትነት፣ መግቦትና ጥበቃ በሕዝቦችም ኹሉ ላይ ከፍ ከፍ እንደሚል በማወቅ የምንኖረው የአማኝ ሕይወት ነው።

ፍጻሜ!

በሚደርስብን መከራ ኹሉ የቅርብ ረዳታችን እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ነው፤ እርሱ በአዲስ ኪዳን ላለን አማኞች አማኑኤል ኾኖአል። የዚህ መዝሙር ትንቢታዊ ቃል ፍጻሜው በክርስቶስ ኢየሱስ መምጣትና መሞት መነሣት፤ ደግሞም ዳግም መምጣት የሚጠናቀቅ ነው። እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ያለው የመጨረሻው ዕቅዱና ዐሳቡ በማይነዋወጥ ዓለም መኖር፣ ሰላም በሰፈነበትና ጦርነት በሌለበት ዓለም እንዲኖሩ ነው፤ እንዲህ ተብሎ እንደ ተዘመረ፤ “እነሆ፥ የእግዚአብሔር ድንኳን በሰዎች መካከል ነው ከእነርሱም ጋር ያድራል፥ እነርሱም ሕዝቡ ይሆናሉ እግዚአብሔርም እርሱ ራሱ ከእነርሱ ጋር ሆኖ አምላካቸው ይሆናል፤ እንባዎችንም ሁሉ ከዓይኖቻቸው ያብሳል፥ ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይኾንም፥ ኀዘንም ቢሆን ወይም ጩኸት ወይም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፥ የቀደመው ሥርዓት አልፎአልና” (ራእ. 21፥3-4)።

አሜን፤ በመከራ ጊዜ ረዳታችን ሆይ፤ ማራን አታ!

ተፈጸመ

 

No comments:

Post a Comment