Friday 18 June 2021

መድሎተ ስሑት ወይስ “መድሎተ ጽድቅ”?! (ክፍል ፱)

 Please read in PDF

ካለፈው የቀጠለ …

ቅድስና ከመጽሐፍ ቅዱስ፣ ቊልፍ ቃላት መካከል አንዱ ቅድስና የሚለው ነው። በተቃራኒው ደግሞ፣ “የመድሎተ ጽድቅ ጸሐፊ”፣ ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጭ ትርጕም ከሰጣቸው ቃላት አንዱ ቅድስና ነው። ቅድስና የእግዚአብሔር የባሕርይ ገንዘቡ ነው፣ “እንደ እግዚአብሔር ቅዱስ የለምና፥ እንደ አምላካችንም ጻድቅ የለምና፤ ከአንተ በቀር ቅዱስ የለም።” (1ሳሙ. 2፥2)፤ “እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝና፤ ሰውነታችሁን ቀድሱ፥ ቅዱሳንም ሁኑ፥ እኔ ቅዱስ ነኝና፤” (ዘሌ. 11፥44)፤“ ጌታ ሆይ፥ የማይፈራህና ስምህን የማያከብር ማን ነው? አንተ ብቻ ቅዱስ ነህና፥” (ራእ. 15፥3) ተብሎ እንደ ተጻፈ፣ እግዚአብሔር አምላክ ብቻ ቅዱስ ነው። በዕብራይስጥ (godesh), በግሪክ (hagiosune) ተብሎ የተጠራው ቅድስና ትርጉሙ፣ መለየት ወይም እግዚአብሔርን መምሰል የሚል ነው። ቃሉ በተለይ በዘሌዋውያን መጽሐፍ ላይ እጅግ ተደጋግሞ የተጠቀሰ ነው።

በአዲስ ኪዳን ምንባባት ውስጥ፣ “ስለ ክፉ ምኞት በዓለም ካለው ጥፋት አምልጠን ከመለኮት ባሕርይ ተካፋዮች በተስፋ ቃል እንድንኾን፥ … ራስንም በመግዛት መጽናትን፥ በመጽናትም እግዚአብሔርን እንመስል ዘንድ” (2ጴጥ. 1፥4-6)፣ “ከኃጢአት አርነት ወጥታችሁ ለእግዚአብሔርም ተገዝታችሁ፥ ልትቀደሱ ፍሬ አላችሁ፤” (ሮሜ 6፥22)፣ እንዲሁም፣ “የልጁን መልክ እንዲመስሉ” (ሮሜ 8፥29) ተብሎ እንደ ተነገረው፣ ቅድስና እግዚአብሔርን ከመምሰልና በኹለንተናዊ መንገድ በእግዚአብሔር ቊጥጥር ሥር ከመኾን ጋር ተያይዞ ተጠቅሶአል። እንዲሁም መቀደስን እንሻ ዘንድ መፈለግ እንዳለብን ተነግሮናል (ዕብ. 12፥14)።

ከዚህ የምንረዳው ቅድስና ወይም ለጌታ መለየት የሚኾነው፣

1.      ክርስቶስ በመስቀል ላይ የተቀበለውን ዘላለማዊ የቤዝወት ሥራና የመስቀሉን መንገድ አማኞች በሕይወታቸው አምነው ሲቀበሉ ነው። ይህ በእምነት ኀይል የሚኾነው ወዲያውኑ ነው። አማኞች፣ ክርስቶስ በመስቀል ላይ የሠራውን ሥራ ወዲያውኑ አለ ነውር በቅድስና ይኾናሉ።

2.     ጌታ መንፈስ ቅዱስ፣ በክርስቶስ ኢየሱስ የዳነውን አማኝ፣ በሕይወቱ ሳያቋርጥ በመሥራት ደግሞ በሂደት ይቀድሰዋል። የዳነው አማኝ ዘወትር በእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ቊጥጥር ሥር ነውና። ይህም የማያቋርጥና የኹልጊዜ አኗኗርን የሚያመለክት፣ በማናቸውም ኹኔታ ውስጥ እግዚአብሔርን መፍራት የሚያመለክት ነው። የዳነው አማኝ በወደቀው ዓለም ቢኖርም ራሱን ግን ከክፉው ዓለም መቀደስ ወይም መለየት አለበት። በዓለም ውስጥ ነው፣ ከዓለም ግን አይደለም፤ (ዮሐ. 17፥15)። መለየት ወይም መቀደስ በኃጢአት ፈጽሞ አለመተባበር ነውና፤ “ሕዝቤ ሆይ፥ በኃጢአትዋ እንዳትተባበሩ ከመቅሠፍትዋም እንዳትቀበሉ ከእርስዋ ዘንድ ውጡ፤” እንዲል (ራእ. 18፥4)።

ስለዚህ ቅድስና ከላይ በተጠቀሱት መንገዶች በአማኝ ሕይወት ውስጥ ይከናወናሉ። እግዚአብሔር ለራሱ ሲለየን፣ መጀመሪያ የሚያደርገው ነገር እኛን መቀደስ ነው። አንድ ጊዜ ብቻ የሚቀድሰን አይደለም፣ ሙሉ ለሙሉ ባልተዋጀው ዓለም ውስጥ ለምንመላለስ ኹላችን፣ ጌታችን በሊቀ ካህናትነት ጸሎቱ፣ “ከክፉ እንድትጠብቃቸው እንጂ ከዓለም እንድታወጣቸው አልለምንም።” (ዮሐ. 17፥15) ብሎ እንደ ጸለየው፣ መንፈስ ቅዱስ፣ በእውነት ይቀድሰን ዘንድ (ቊ. 17) “በምድርም ፊት ካለው ሕዝብ ሁሉ እኔና ሕዝብህ የተለየን እንሆን ዘንድ” (ዘጸ. 33፥16) ዘወትር አብሮን አለ። ማንኛውም የጸደቀ ሰው፣ መጽደቁ በሕይወቱ የሚገለጠው በቅድስና የተመላለሰ እንደ ኾን ነው።

“… ሰዎች በክርስቶስ በማዳን ሥራው አምነው እንዲድኑና እንዲጸድቁ እንዲቀደሱም በክርስቲያዊ ሕይወታቸውም እንዲጸኑ ካደረገ በኋላ መንፈስ ቅዱስ ሥራውን በመቀጠል የዳኑትንና የተቀደሱትን ደግሞ ለበለጠ ሥራና አገልግሎት ያዘጋጃቸዋል።”[1]

ይህ የእግዚአብሔር ፈቃድ እርሱም መቀደሳችሁ ነውና፤” (1ተሰ. 4፥3) እንዲል፣ ከሚረክሰው ዓለም ጋር እንረክስ ዘንድ አልተጠራንም ወይም አልጸደቅንም። የእግዚአብሔር ግልጽ ዐሳቡና ፈቃዱ ዘወትር በቅድስና እንኾን ዘንድ ነው፤ ልክ፣ “እግዚአብሔር በመንፈስ መቀደስ እውነትንም በማመን ለመዳን እንደ በኵራት መርጦአችኋልና፤” (2ተሰ. 2፥13) ተብሎ እንደ ተጻፈው ቅድስና፣ ከርኩሰት በመለየት የክብር ዕቃዎች እንኾን ዘንድ (2ጢሞ. 2፥21)፣ ለዳንን ኹሉ የተሰጠ እንጂ ለተወሰኑ ሰዎች ብቻ የተሰጠ አይደለም። ለዚህ ነው ቅዱስ ጳውሎስ፣ አማኞችን ኹሉ በታላቅ ልመና የሚለምነው፤ እንዲህ በማለት፦ “እንግዲህ፥ ወንድሞች ሆይ፥ ሰውነታችሁን እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝና ሕያው ቅዱስም መሥዋዕት አድርጋችሁ ታቀርቡ ዘንድ በእግዚአብሔር ርኅራኄ እለምናችኋለሁ፥” (ሮሜ 12፥1)።

እንግዲህ ቅድስናን ስናስብ፦

1.      ከእግዚአብሔር ከራሱ ዘንድ የምናገኘው ነው፤ እርሱን የሚመስል ቅዱስ በሰማይም በምድርም ከቶ የለም፤

2.     በክርስቶስ ያልጸደቀ ቅዱስ ይኾን ዘንድ አይችልም፤ ስለዚህም በክርስቶስ መሥዋዕታዊ የሥጋ ሞትና ትንሣኤ የሚያምኑ አማኞች ኹሉ ቅዱሳን ናቸው፤

3.     ቅድስና ወዲያውም፤ ሂደታዊም ነው፤

4.     ቅድስና በቀዳሹ እንጂ በተቀዳሹ ማንነትና ኹኔታ ላይ የተመሠረተ አይደለም።

5.     ያለ መንፈስ ቅዱስ ጸጋ፣ ሰው ከቶውንም በራሱ ችሎታና ብቃት ቅዱስ ይኾን ዘንድ አይችልም።

አቤቱ፥ በአማልክት መካከል እንደ አንተ ያለ ማን ነው? በምስጋና የተፈራህ፥ ድንቅንም የምታደርግ፥ በቅድስና የከበረ እንዳንተ ያለ ማን ነው?” (ዘጸ. 15፥11) እኔም እንደ ሙሴ ጥያቄውን ልመልስ፣ ማንም!

የ“መድሎተ ጽድቅ ጸሐፊ” የቅድስና ትርጕም ስህተቱ

“ቅድስና የሚገኝባቸው መንገዶች - ምስጢረ ጥምቀትን፣ ምስጢረ ሜሮንን፣ ምስጢረ ቁርባንን፣ ጾምን፣ ጸሎትን፣ መንፈሳዊ ተጋድሎን … አይቀበሉም”[2] በማለት፣ የቅድስና መገኛዎች ምስጢራትና መልካም ሥራዎች መኾናቸውን በመደጋገም ሌላውን በመኰነን ይናገራል። ምስጢራትን የማይቀበሉ ሰዎች ምስጢራትን የማይፈልጉበትን ምክንያትም ሲናገር፣ “በሰው መዳን ውስጥ ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያንን፣ የመጽናትንና የተጋድሎን አስፈላጊነት ኹሉ ከንቱ ለማድረግና እንዲሁ “ድኛለሁ” እያሉ በመፎከር እንዳሻቸው ኃጢአትን ለመሥራት ለራሳቸው ይለፍ ለመስጠት የፈጠሩት ሰፊ መንገድ ነው።”[3] ይላል።

“ጌታችን … ከመሠረቱ ጀምሮ(እምነት፣ ምስጢራት) ቀርተው በዚህ ብቻ ይዳናል ማለቱ እንዳልኾነ ግልጽ ነው። ለመዳን አስፈላጊ የኾኑት እምነት፣ ምስጢራትን መፈጸም እንዳሉ ኾነው …”[4] በማለት፣ ለቅድስና የግድ ምስጢራትን መፈጸም እንደሚገባ ደጋግሞ ሲናገርና እንዲያውም፣ ጌታችን “ምስጢራት ቀርተው ይዳናል አላለም!” ብሎ በድፍረት ሲናገር እንሰማዋለን። መጽሐፍ ቅዱስ ግን፣ “ከእናንተም አንዳንዶቹ እንደ እነዚህ ነበራችሁ፤ ነገር ግን በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም በአምላካችንም መንፈስ ታጥባችኋል፥ ተቀድሳችኋል፥ ጸድቃችኋል።” (1ቆሮ. 6፥12) በማለት ሲናገር፣ ቅድስና ከሰውም፤ በሰውም እንዳይደለ ይነግረናል።

ቅዱስ ጳውሎስ ይህን በሌላ ስፍራ፣ “ነገር ግን አሕዛብ በመንፈስ ቅዱስ ተቀድሰው የተወደደ መሥዋዕት ሊሆኑ፥ …” በማለት ገልጦታል (ሮሜ 15፥15-16 በተመሳሳይ አገላለጥ በ1ቆሮ. 1፥2፤ 1ቆሮ. 5፥23፤ ዕብ. 10፥10፡ 29፤ ዕብ. 13፥12፤ ይሁዳ 1 ተናግሮአል)። መንፈስ ቅዱስ የሚድኑትን ነፍሳት፣ በራሱ ያጠምቃል (ሮሜ 6፥3-8)፤ መንፈስ ቅዱስ ደግሞ ይህን የሚሠራው አማኙ፣ ክርስቶስ ለእርሱ እንደ ሞተና እንደ ተነሣ፣ ደሙንም ለእርሱ እንዳፈሰሰ ሲያምን ነው። ልክ አማኙ ሲያምን፣ መንፈስ ቅዱስ ወዲያውኑ ክርስቶስ ራስ ወደ ኾነባት አካሉ በማስገባት ያጠምቀዋል፤ ይቀድሰዋል፤ ፈጽሞም ያጠራዋል። አማኙም ከዚያች ቀን ጀምሮ እግዚአብሔርን መምሰልን፣ ወደ ልጁ ማደግን፣ ፍጹም በመቀደስ መመላለስን ከመንፈስ ቅዱስ የተነሣ ይለማመዳል።

የ“መድሎተ ጽድቅ” ጸሐፊ ግን፣ ይህን እውነት ፈጽሞ በመካድ፣ ከጌታ ጋር የተሰቀለውና በማመኑና በመቀደሱ በገነት ወዲያው የተገኘው ወንበዴ የዳነበትን መንገድ እንኳ ባለማስተዋል፣ መቀደስን ከግል ጥረትና በኹኔታዎች ክንውን ላይ ሲያንጠለጥለው እንመለከታለን። እውነተኛ አማኝ ግን እግዚአብሔርን ለመምሰል ኃይሉንም፤ ብቃቱንም የሚቀበለው ከእግዚአብሔር ነው። ከእግዚአብሔር በተቀበለው ኃይልና ብቃትም በመታመን ይተጋል፤ (2ጴጥ. 1፥3-7)፤ ከመንፈስ ቅዱስ የተነሣም እግዚአብሔርን በመምሰል በሕይወት ዘመኑ ኹሉ ይመላለሳል (2ጴጥ. 3፥11)። በጌታ የምናምን ኹላችንም ራሳችንን ለዚህ ታላቅ እውነት ማስገዛትና ማስለመድ አለብን፤ “ሰውነትን ለሥጋዊ ነገር ማስለመድ ለጥቂት ይጠቅማልና፤ እግዚአብሔርን መምሰል ግን የአሁንና የሚመጣው ሕይወት ተስፋ ስላለው፥ ለነገር ሁሉ ይጠቅማል።” (1ጢሞ. 4፥8) እንዲል።

ጸጋና ሰላም ክርስቶስን እጅግ ከሚወዱትና ከማይጠፉት ጋር ይኹን፤ አሜን።

ይቀጥላል …

 

 



[1] አበራ በቀለ (ሊቀ ጉባኤ)፤ ትምህርተ ሃይማኖትና ክርስቲያናዊ ሕይወት፤ 1996 ዓ.ም፤ ገጽ 176

[2] ገጽ 186

[3] ገጽ 188

[4] ገጽ 200-201

7 comments:

  1. የኔ ውድ ወንድም በብዙ ተባረክልኝ ፀጋ ይብዛልህ

    ReplyDelete
  2. Abeni,

    Thank you for all the hard work you have done in this article. As I am continuing to look into some of these same issues, it is becoming very complicated, particularly with all the apparent double speak out there. I am happy you did not shirk from saying the obvious.

    ReplyDelete
  3. Amazing Preaching!!

    ReplyDelete
  4. አንጀትህ ይቀደድ ምድረ መናፍቅ

    ReplyDelete
  5. አጭበርባሪ ፓስተር

    ReplyDelete
  6. እንዲሁ ቅናት እያሳበደህ ትኖራለህ መናፍቁ😃😃

    ReplyDelete
  7. ዳቆን ነህ እንጅ ዕውቀትህ የዲያቆን አይደለም። ቱልቱላ መናፍቅ

    ReplyDelete