Friday 4 June 2021

ኹለቱ የእውነት ቃል አገልግሎት አገልጋዮች!

 Please read in PDF

በዚህ ወር “ያለ እውነት፣ የእውነት ቃል አገልግሎት!?” ከሚለው መጽሐፍ መታተም ጋር በተያያዘ፣ ኹለት የእቃአ(ከዚህ በኋላ፣ የእውነት ቃል አገልግሎት ለማለት የሚውል) አገልጋዮች ፊት ለፊት ተገናኝተውኝ አውርተውኝ ነበር። አንደኛው አገልጋይ መጽሐፍ ተርጓሚያቸው ሲኾን፣ ኹለተኛው ደግሞ ሰባኪያቸው ነበር። አንዱን በሰው መካከለኝነት[በወንድም ቴዎድሮስ ደመላሽ አማካይነት] ያገኘኹት ሲኾን፣ ሌላው ግን ያገኘኝ ራሱ ደውሎ ለብቻ ነበር። ኹለቱም በአካል አጊኝተው ሊያወሩኝ በመፈለጋቸው፣ እጅጉን ደስ ብሎኛል።



ከኹለቱም ጋር ከሦስት ሰዓት በላይ “ያወጋን” ሲኾን፣ የኹለቱንም ውይይት እጣሬ እንዲህ ማቅረብ እችላለሁ። ኹለቱም አገልጋዮች፣

·        እቃአ የሚመራበትና የራሱ የኾነውን የGBV መጽሐፍ ቅዱስ መኖሩንም አያውቁም። እንዲያውም ሌላ መጽሐፍ ቅዱስ የለንም ብሎ ተሟገተ፣

·        አንደኛው የGBV መጽሐፍ ቅዱስ ሳይኾን፣ የደርቢንን መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚቀበልና የደርቢንን ሙሉ ትምህርቶች እንደሚቀበል በሙሉ እምነት ሞገተ፣

·        ሌላኛው፣ ገና ወደፊት የሚሰበክና ቤተ ክርስቲያንን የማይመለከት ወንጌል እንዳለ አጽንቶ ሞገተ፣

·        ኹለቱም የጻፍኩትን አናምንም ለማለት አልደፈሩም፤ በተለይም አምልኮ የሚለውን ዐሳብ፣ “ከጌታ እራት በቀር” በሚለው አቋማቸው እንደ ፀኑ ነበር።

·        ኹለቱም [ስም ጠቅሰው] አብረሃቸው የምታገለግላቸው “አገልጋዮች” ጭምር እኛ ዘንድ መጥተው ይማራሉ፤ ስለ እነርሱ ምን አቋም አለህ? የሚል ጥያቄ ነበራቸው። የእነርሱ በድብቅ መሄድ ወይም መገናኘት፣የእቃአን ትምህርት እውነትነት እንደማይገልጥና ካመኑበትና ከተከተሉት ግን የጊዜ ጉዳይ እንጂ በትምህርትና በፍሬ እንደሚገለጥ ተናግሬአለሁ።

ኹለቱም ተወያዮች እኔ ለጻፍኹት መጽሐፍ ዐሳቦች እንግዶች ናቸው። አንዳንድ ትምህርቶችን ጭራሽ አልሰማንም አንዳንዴ ደግሞ አንልም ቢሉም፣ የተጻፈበትን ቦታ ስጠቁም ግን ዝምታን መርጠዋል። ከዚህም የተረዳኹት የተከተሉትን “እምነት” በቅጡ እንደማይረዱና በትክክል እንደማያውቁትም ነው። በእርግጥ መጽሐፉን ጽፌ፣ ወንድሞች እንዲተቹት በሰጠኹበት ጊዜ ከሰጡኝ አስተያየት አንዱ፣ “በዚህ ልክ ግን ትምህርቱ ስህተት ያለበት አይመስለንም” ብለውኝ ነበር። የእኔም ትልቁ ሥራ ድብቁ በግ መሳይ ካባቸውን ማውለቅና ማሳየት ነው!

የውይይታችን መደምደሚያ!

በሌላ ጊዜ ተቀጣጥረን፣ ተዘጋጅተው እንደሚመጡና እኔ በጻፍኩበት ልክ እንደማያስተምሩ በመሟገት ሲኾን፣ እንደሚያስተምሩ ለጠቀስኳቸውና ከእነርሱ መጻሕፍት ላሰፈርኳቸው ማስረጃዎች ግን ምላሽ ለመስጠት አልፈለጉም። በውስጤ የቀረው ጥያቄ፣

·        እውን የግል መጽሐፍ ቅዱስ እንዳላቸው አስተውለው አያውቁትም? አገልጋዮች ኾነው ካላወቁት እንዴት?

·        እውን የሚያምኑትን ይህን ሳያውቁት ቀርተው ነው ወይስ የሚያምኑበትን ያፍሩበታል?

·        የሚከተሏቸውን፣ ቀስ በቀስ እንጂ የሚያምኑትን ኹሉ እስከ መጨረሻ አያስተምሩአቸውም ማለት ነው? …

ነገር ግን ዛሬም፣ ራሳቸውን ሸሽገው ስተው ከሚያስቱ (2ጢሞ. 3፥13) የኑፋቄ መምህራንና ማኅበራት እንጠበቅ፤ እንርቅ፤ እንሸሽ ዘንድ ወንድማዊ ምክሬ ነው! “ጌታ ኢየሱስ፣ “የበግ ለምድ ለብሰው ከሚመጡባችሁ በውሥጣቸው ግን ነጣቂዎች ተኵላዎች ከሆኑ ከሐሰተኞች ነቢያት ተጠንቀቁ።” እንዲል (ማቴ. 7፥15)።

“ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን ባለመጥፋት ከሚወዱ ሁሉ ጋር ጸጋ ይሁን፤ አሜን።” (ኤፌ. 6፥24)

1 comment:

  1. የእነርሱ በድብቅ መሄድ ወይም መገናኘት፣የእቃአን ትምህርት እውነትነት እንደማይገልጥና ካመኑበትና ከተከተሉት ግን የጊዜ ጉዳይ እንጂ በትምህርትና በፍሬ እንደሚገለጥ ተናግሬአለሁ። yenem tiyake neber

    ReplyDelete