Wednesday 18 September 2019

ሾላኮቹ (ክፍል ፫)

Please read in PDF

   በባለፉት ኹለት ክፍሎች የመናፍቃንን የሾላካነት ጠባይ መመልከታችን አይዘነጋም፤ ከዚያ በመቀጠል ዛሬም እንመለከታለን፤ የጌታ ጸጋና ሰላም ከኹላችሁ ጋር ይኹን፣ አሜን፡፡
4.      ዩነትን ወይም እንግዳ ዘርን ለመዝራት፦ ጌታችን ኢየሱስ እንክርዳድ ዘሪው ክፉ፣ ማንም ሳያየው በሌሊት ወይም ጨለማን ለብሶ በመሹለክ ተግባር እንዳደረገው ነግሮናል፤ ጠላት እንክርዳድ የዘራው በዚያው መልካሙ ዘር በተዘራበት እርሻ ላይ ነው፤ አበቃቀሉም ኹለቱም በአንድነት በቀሉ፤ የስንዴውም የእንክርዳዱም አበቃቀላቸው ተመሳሳይና አንዱን ከሌላው ለመለየት እጅግ አዳጋች እንደ ኾነ፣ “እንክርዳዱን ስትለቅሙ ስንዴውን ከእርሱ ጋር እንዳትነቅሉት አይሆንም” (ማቴ. 13፥29) ከሚለው ከጌታችን ኢየሱስ ንግግር እናስተውላለን።

   በእርሻው ውስጥ በአንድነት ሲገኙ፣ ለመልካሙ ዘር ከሚመጣው በረከት ሲቋደሱ፣ ከመልካሙ ዘር ጋር እጅግ ተመሳስለው ሲበቅሉ … ኹለንተናቸው ድብቅና የመመሳሰል ባሕሪይ አለው። ነገር ግን ተመሳስለው በዚያ የሚኖሩት፣ በመካከል የሚሸምቁት በጎችን በመለያየትና እንግዳ ዘርን በመዝራት ተግባራቸው በበጎቹ ላይ ሊረብቡ ነው።
   መንፈስ ቅዱስ የሚገኘውና ኢየሱስን ለማክበር የሚመጣው በኢየሱስ ስም በአንድነት በተሰባበሱት አማኞች መካከል ነው፤ ነገር ግን ሰይጣን ዘወትር ተቀዳሚ ተግባሩ የራሱን አንድነት ለክፉ ተግባሩ ጠብቆ፣ የአማኞችን የመንፈስ አንድነት ግን በማናጋትና በማፍረስ እጅግ ተግቶ ይሠራል። ምክንያቱም እኛ ከእግዚአብሔር ጋር በክርስቶስ ኢየሱስ አንድ ከኾንን፣ መንግሥቱ ፈጽማ እንደምትፈርስና ዙፋኑ እንደሚሻር ያውቃልና። ስለዚህም መለያየትንና ክፉውን ዘረ ከሚዘሩት ራቁ!
“መከፋፈል የሚያመጣን ሰው አንድ ጊዜ ምከረው፤ ለሁለተኛ ጊዜ አስጠንቅቀው፤ ከዚያ ባለፈ ከእርሱ ጋር አንዳች ነገር አይኑርህ፡፡ እንዲህ ዐይነቱ ሰው የሳተና ኀጢአተኛ ነው፤ ራሱንም እንደሚኰንን ዕወቅ፡፡” (ቲቶ 3፥10-11 ዐመት)
ማንን ያስታሉ?
   ሾላካ መናፍቃን በባሕሪያቸው በማን ላይ መርበብ፣ ማንን ማጥመድና ማሳት እንዳለባቸው አስቀድመው የመለየት ሥራን በጥንቃቄ ይተገብራሉ። ልክ እውነተኛ መምህራን ባላደራ ሊኾኑ የሚችሉ ደቀ መዛሙርትን አስቀድመው እንደሚለዩትና በእነርሱ ላይ ሙሉ ነገራቸውን እንደሚያፈስሱት እንዲኹ (2ጢሞ. 2፥1-2)፣ የሐሰት መምህራንም በሾላካነት ጠባያቸው ደቀ መዛሙርትን በኋላቸው ለመሳብና ባላደራ ለማዘጋጀት፣ ስተው ለማሳት ዘወትር ይተጋሉ፤ (ሐዋ. 20፥29-30)።
   ሌባ የሌላውን ንብረት ለመስረቅ አስቀድሞ የሚሰርቀውን ንብረት በዓይነ ቍራኛ እንደሚከታተል፣ ለመስረቅም አሳቻና ምቹ ሰዓት እንደሚጠብቅ እንዲሁ፣ ሾላኮችም “የክርስቶስን ሐዋርያት እንዲመስሉ ራሳቸውን እየለወጡ፥” (2ቆሮ. 11፥13) “ነገር ግን እባብ በተንኮሉ ሔዋንን እንዳሳታት፥ አሳባችሁ ተበላሽቶ ለክርስቶስ ከሚሆን ቅንነትና ንጽሕና ምናልባት እንዳይለወጥ ብዬ እፈራለሁ” እንዲል፣ ከእባቡ እንደ ተማሩት በተንኮላቸው ያስታሉ፣ አማኞች ለክርስቶስ ያላቸውን ቅንነትና ንጽሕና ለማበላሸት ሳይታክቱ ይሠራሉ።
   ለመኾኑ ግን እኒህ ሾላኮች ሾልከው ከገቡ በኋላ የሚያስቱት ወይም የሚያታላልሉት እነማንን ነው?
1.    ውነትን ማወቅ የማይወዱ ሞኞች ሴቶችን፦ ቅዱስ ጳውሎስ ስለዚህ ነገር ሲናገር እንዲህ ይላል፣ “ወደ ቤቶች ሾልከው እየገቡ፥ ኃጢአታቸው የተከመረባቸውን በልዩ ልዩ ምኞትንም የሚወሰዱትን ሁልጊዜም እየተማሩ እውነትን ወደ ማወቅ ሊደርሱ ከቶ የማይችሉትን ሞኞችን ሴቶች የሚማርኩ፥ ከእነዚህ ዘንድ ናቸውና።” (2ጢሞ. 3፥7)።
   እውነትን ለማወቅ አለመውደድ ፍጻሜው ፍጹም ወደ ኾነ የስህተት መደላድልና ገደል መድረስ ነው፤ በሚያሰጥም አዘቅትም መያዝ ነው። ክርስትና በእምነት ብቻ የምንከተው ያይደለ፣ የምናምነውንም ማወቅ የሚገባን እውነተኛ የክርስቶስ መንገድ ነው። የወንጌልን እውነት፣ የሕይወትን እውነት፣ የሥነ ምግባርን እውነት በትክክል ማወቅ ይገባናል። የጠራ ወንጌል፣ ቅዱስ ሕይወት፣ ሰናይ ሥነ ምግባር የማይኖረን እውነትን ለማወቅ ባለ መውደድ ስለምንሞኝና በልዩ ልዩ ምኞት ስለምንወሰድ ነው።
   ሾላኮቹ ብዙ ሞኞች ሴቶችን ማታለል ይችላሉ። ቅዱሳት መጻሕፍትን ከማወቅና ከመታዘዝ ይልቅ፣ እንደሚገባ ባለመማር የሚኖሩ ደካማ ሰዎችን ያጠምዳሉ። ምክንያቱም ኃጢአታቸው ስለ ተከመረባቸው፣ ኅሊናቸው ስለ ቆሸሸ፣ በልዩ ልዩ ፍትወት በመቃጠል፣ ለምኞታቸው በመሸነፍና በመገዛት የደነዘዙትን፣ ወላዋይና አቋም የሌላቸውን፣ እየተማሩ ወደ እውነት ፈጽሞ መድረስ የማይችሉትን ሴቶች ሾላኮቹ በማናቸውም ጊዜ ያስቱአቸዋል። ይህ ለሴቶች ብቻ አይደለም ለወንዶችም ጭምር እንጂ። ኅሊናቸው የደነዘዘ፣ ከመከተል ውጪ ማስተዋልና መመርመር የማይወዱ ወንዶችም ጭምር ለስህተት ትምህርት ጎምርተው የተዘጋጁ ናቸው።
   ዛሬ ብዙ አማኞችና አገልጋዮች ቅዱሳት መጻሕፍትን በትጋት፣ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል፣ በጸሎት ከመመርመር ይልቅ፣ ከቅዱሳን መጻሕፍት ውጭ ባሉ ሌሎች ጽሑፎችና ትምህርቶች ዙርያ ተኮልኩለው እንመለከታቸዋለን። ቅዱሳት መጻሕፍትን መሠረት ያደረጉ መጻሕፍትን ማንበብ፣ መመልከት መልካም ነው፣ ነገር ግን እኒያ መጻሕፍት የቅዱሳት መጻሕፍትን ቦታ አይተኩም፤ በዚህ ጉዳይ ሞኞች መኾን የለብንም። ለስህተት አስተማሪዎችም ራሳችንን አመቻችተን መቀመጥ የለብንም።
    ከንቱ የኾነ ክርክርና የሞኝነት ምርመራ አይረባንም (ቲቶ 3፥9)፣ ደግሞም እንደ ፍጥረታዊ ሰው የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበትን ሕያው እውነት ባለ መቀበል፣ ለምድራዊ ስሑት መምህራን ራሳችንን አሳልፈን መስጠት አይገባንም፤ (1ቆሮ. 2፥14)፤ ሾላኮቹ እንዲህ በማድረግ ሞኞች እንድንኾንላቸው ዘወትር ይፈልጋሉ፤ ነገር ግን እኛ ዘወትር እንዲህ ካለ ሞኝነት ፈጽመን መራቅ ይገባናል፡፡ ቅዱሳት መጻሕፍትን በትክክልና በእውነት ባለ ማጥናት ሞኞች መኾን ትፈልጋላችሁን? የማትፈልጉ ከኾናችሁ እንዲህ ካሉ ሾላኮች ራሳችሁን ለመንፈስ ቅዱስ አደራ በመስጠትና ቅዱሳት መጻሕፍትን በመመርመርና በማወቅ ጠብቁት! ጸጋ ይብዛላችሁ፣ አሜን፡፡
ይቀጥላል …

4 comments:

  1. ልዩ ልዩ ምኞትንም የሚወሰዱትን ሁልጊዜም እየተማሩ እውነትን ወደ ማወቅ ሊደርሱ ከቶ የማይችሉትን ሞኞችን ሴቶች ... ይገርማል

    ReplyDelete
  2. ልዩ ልዩ ምኞትንም የሚወሰዱትን ሁልጊዜም እየተማሩ እውነትን ወደ ማወቅ ሊደርሱ ከቶ የማይችሉትን ሞኞችን ሴቶች ... ይገርማል

    ReplyDelete
  3. ልዩ ልዩ ምኞትንም የሚወሰዱትን ሁልጊዜም እየተማሩ እውነትን ወደ ማወቅ ሊደርሱ ከቶ የማይችሉትን ሞኞችን ሴቶች ... ይገርማል

    ReplyDelete
  4. ልዩ ልዩ ምኞትንም የሚወሰዱትን ሁልጊዜም እየተማሩ እውነትን ወደ ማወቅ ሊደርሱ ከቶ የማይችሉትን ሞኞችን ሴቶች ... ይገርማል

    ReplyDelete