Monday 23 September 2019

ሾላኮቹ (ክፍል ፬)

Please read in PDF
 ባለፈው በተመለከትነው ክፍል ሾላኮቹ ማንን ያስታሉ? ብለን በቀዳሚነት ከቅዱሳት መጻሕፍት ጠቅሰን  “ውነትን ማወቅ የማይወዱ ሞኞች ሴቶችን” እንደሚያስቱ ተመልክተናል፤ ዛሬ ደግሞ የዚኹን ቀጣይ ክፍል እንዲህ እንድታነቡት ጋብዛችኋለሁ፤ ጸጋና ሰላም ይብዛላችሁ፤ አሜን።
2.      ዳዲስ አማኞችን፦ አዳዲስ አማኞች ለቃለ እግዚአብሔር ጥማት የተጋለጡ ናቸው፤ ከቃለ እግዚአብሔር ጋር የተያያዘ ማናቸውንም ትምህርቶች ለመስማት ይቸኩላሉ። በተለይም ሾላካ መናፍቃን የሚጠቅሷቸውንና እውነተኛ መምህራን የሚጠቅሷቸውን እውነተኛ ትምህርት ከመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ጋር በማነጻጸር የትኛው እውነተኛና የትኛው ደግሞ ሾልኮ እንደ ገባ የመለየትና የማስተዋል እንከን አለባቸው።

   ለዚህም በዋናነት የገላትያ ቤተ ክርስቲያንን በምሳሌነት ማንሣት ይቻላል። በገላትያ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ጳውሎስ አስተምሮ እንደ ሄደ፣ ሾላኮቹ አዳዲሶቹን አማኞች ለማሳትና ወደ ራሳቸው የስህተት አሠራር ለመሳብ ሾልከው የገቡት ወዲያው ነበር፣ “ነገር ግን ባሪያዎች ሊያደርጉን በክርስቶስ ኢየሱስ ያለንን አርነታችንን ይሰልሉ ዘንድ ሾልከው በስውር ስለ ገቡ ስለ ሐሰተኞች ወንድሞች ነበረ። (ገላ. 2፥4)። አገባባቸው በስውር የኾነበት ምክንያቱ አዳዲሶቹን አማኞች ለማሳት ነው።
  በእርግጥም ሾላኮቹ እውነተኞች አይደሉም፣ ሐሰተኞች እንጂ። ሐሰተኞች ስለኾኑ የእውነትን ትምህርት በመያዝ ሳይኾን፣ መዳን የሚገኝበትን የክርስቶስን የጽድቅ ሕይወትና ትምህርት በመተው ሌላ የሰው ትምህርትና የመዳን በር በማዘጋጀት ይተጋሉ። ልክ የገላትያ አማኞችን ከክርስቶስ ፊት ዘወር በማድረግ በሙሴ ሕግ ፊት በማኖር፣ “መዳን የሙሴን ሕግ በመፈጸም ነው” እንዳሉት ማለት ነው። ሾላኮች ኹል ጊዜ አዳዲስ አማኞችን ያመኑበትንና የተቀበሉትን ጌታና መድኃኒት በሌላ እንዲተኩ በማድረግ ለማስተው ያላሰለሰ ጥረት ያደርጋሉ።
   የሾላኮቹ የዘወትር ተግባር ከሰይጣን እስራት ያመለጡትን አዳዲስ አማኞች፣ ፈጥነው በሌላ የሰው ወይም የሕግ እስራት ሥር እንዲወድቁ ማድረግ ነው። ከቀመስነውና ካጣጣምነው ሰማያዊ ደስታ ወዲያው በማውረድ እኛን መጣል፣ ጎምዛዛና እጅግ መራራ የኾነውን ኃጢአትና ክፋት እንድናጣጥም ያደርጋሉና እንዲህ ካሉት የክፋት አገልጋዮች ፈጽመን መራቅ ይገባናል። አዳዲስ አማኞች በተለይ በጥንቃቄ መስማትንና በጥንቃቄ ማስተዋልን ፈጽሞ መዘንጋት የለብንም! 
3.     ኖች የኾኑትን  እረኛን መምታት ወይም ማጥቃት ነፍሳትን ለመበተን እጅግ ዐይነተኛ የጠላት መንገድ ነው። የጠላት የክፋት ጥበብ ኹል ጊዜ እረኛ በመምታት ወይም ጠልፎ በመጣል የበጎች መንጋን መበተን እንደ ኾነ ጌታችን ኢየሱስ ተናግሮ ነበር፤ (ዘካ. 13፥7፤ ማቴ. 26፥31)። ኤልያስ በቀርሜሎስ ተራራ ለእግዚአብሔር ቀንቶ የሐሰት ነቢያትን ካሳረደ በኋላ፣ ወዲያው የኤልዛቤል ዛቻ ደርሶት ነበር። ያ ብርቱ የእግዚአብሔር ሰው በአንዲት ሴት ዛቻ በፍርሃት ተውጦ ነፍሱን ለማዳን ፈጥኖ ሸሸ።
   የሲዶናዊቷ ኤልዛቤል ዐላማ ነቢዩ ኤልያስን መግደል አልነበረም፤ ለመግደልማ በጣም ትችል ነበር፤ ምክንያቱም በእርሷ ግዛት ውስጥ ነበርና፣ ያለ አንዳች ማንገራገር ወታደሮችን ልካ ማስገደል እየቻለች ነገር ግን የጣዖት አገልጋይ ነቢያት በመታረዳቸውና እግዚአብሔር ታላቅ መግቦታዊ ተአምራቱን እንዲመለከቱ ባደረጋቸው በአዳዲሶቹ አማኞች ፊት ኤልያስ ተቀባይነት እንዲያጣና እስከ መጨረሻው በአሳችነቷ ጸንታ ለመኖር ያደረገችው የመረረ የክፋት መንገድ ነው።
   ዋኖችን በማሳደድ የሚገኘውን የነፍሳት ትርፍ አጋብሶ ለማፈስ እንዲመች፣ ሾላኮቹ ያለ መታከት እንደሚሠሩ መዘንጋት እጅግ ዋጋ ያስከፍላል። በገላትያ ቤተ ክርስቲያንም ቢኾን የተደረገው ተመሳሳይ ድርጊት ነው፤ ሾላኮቹ ያደረጉት ቅዱስ ጳውሎስ በኢየሱስ የተመረጠ ሐዋርያ እንዳልኾነ አበክረው ሞገቱ፤ ትምህርትም አድርገው አሰረፁ። እርሱን ሐሰተኛ ሐዋርያ አድርገው ራሳቸውን ግን እውነተኛና ዋና አድርገው አቀረቡ፤ ቅዱስ ጳውሎስ በብርቱ ውግዘት ሐሰተኝነታቸውን በማጋለጥ፣ የእርሱን ሐዋርያነት ደግሞ “በኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታንም ባነሣው በእግዚአብሔር አብ ሐዋርያ የሆነ እንጂ ከሰዎች ወይም በሰው ያልሆነ ጳውሎስ” (ገላ. 1፥1-2) በማለት በጽኑ ይሞግታል፤ ምክንያቱም ባይቃወም እርሱን ብቻ ሳይኾን በእርሱ የሚናገረውን መንፈስ ቅዱስን በመቃወም ተጠልፈው አማኞቹ ይወድቃሉና
   በተቃራኒው ደግሞ ብዙዎቻችን ከኢየሱስ ይልቅ የምናምናቸውና የምንከተላቸው “ዋኖች” ሰባኪዎች፣ ዘማሪያን፣ ነቢያት፣ መምህራን፣ የቲቪና የሲዲ፣ የመገናኛ ብዙሃን “አለቆች” … አሉን፤ እነርሱ ሲነኩብን እናኮርፋለን፤ ከኢየሱስ በማይተናነስ መንገድ ለረጅም ሰዓት “ብናወራ የማንጠግብላቸው”፣ ያዘዙንን ሳናነጥብ፣ አንዳች ሳናጎድል የምንፈጽምላቸው በራሳችን ላይ የሾምናቸው ዋኖች አሉን፤ ጠላትም ሾልኮ ለመግባትና ትኩረታችንን የምናደንቃቸውና የምንከተላቸው ዋኖቻችን ላይ በማድረግ ከኢየሱስ ሊነጥለን ያላሳለሰ ጥረትን ያደርጋል።
   ተወዳጆች ሆይ! “ከውሾች ተጠበቁ፥ ከክፉዎችም ሠራተኞች ተጠበቁ፥ ከሐሰተኛም መገረዝ ተጠበቁ።” (ፊልጵ. 3፥2)፣ ምክንያቱም ዘወትር እንዲህ ያሉት ሠራተኞች እኛን ማጥመድና መጣል ዋና ሥራቸው ነውና። ጌታ መንፈስ ቅዱስ ከሾላኮች ወጥመድ እያንዳንዳችንን ይጠብቅ፤ አሜን።
ይቀጥላል …

1 comment: