Monday 15 April 2019

ኒቆዲሞስ - ከዳግም መወለድ ይልቅ ኢየሱስ ይልቃል!

 Please read in PDF
 የሳምንቱ ስያሜ ኒቆዲሞስ ነው። የሚነበበው የወንጌል ንባብ ደግሞ ዮሐ. 3፥1-21 ነው። ክፍሉ በኢየሱስና በየአይሁድ መምህር በኾነው በኒቆዲሞስ ንግግር የደመቀ ኾኖ፣ የክፍሉ ዋና መልእክቱ ግን የኒቆዲሞስ መምህር መኾን ወይም የዳግም መወለድ ጉዳይ ብቻ አይደለም። እውነት ነው! በክፍሉ  የኒቆዲሞሰ ታሪክ ተመዝግቧል፤ የዳግም ልደት ትምህርትና ጥልቅ ማብራሪያም አለ፤ ዋናው የወንጌሉ መልእክት ግን ይህ አይደለም።

   ኒቆዲሞስ ስለ ኢየሱስ ከሰማው ነገር አንጻር፣ “መምህር ሆይ፥ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ከሆነ በቀር አንተ የምታደርጋቸውን እነዚህን ምልክቶች ሊያደርግ የሚችል የለምና መምህር ሆነህ ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደ መጣህ እናውቃለን” (ዮሐ. 3፥2) በማለት የተናገረው ትክክልና እውነት ነው። አዎን! ከእግዚአብሔር የተላከ መልእክት፣ የእግዚአብሔርም እውነተኛ ታዛዥ መልእክተኛ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፤ እንደ ጌታ ኢየሱስም የእግዚአብሔርን ሃሳብ በትክክል የፈጸመና ለአብ የታዘዘ ከቶ የለም። ይህ ግን ለኒቆዲሞስ ከእውቀት የዘለለ ምንም ነገር አልነበረም።
   ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ መልካም ለኾነው ለኒቆዲሞስ ንግግር፣ ምላሹ ጠንካራና በመንፈሳዊ ነገር አላዋቂነቱን በትክክል የሚያራቁት ነው። ጌታችን ኢየሱስን በትክክል ለማወቅ መንግሥቱ ልትገለጥልን ይገባል። የመጽሐፍ ቅዱስ ክርስትና ከዕውቀት በዘለለ መገለጥ ነው የሚባለው ለዚህ ነው። ልክ ቅዱስ ጴጥሮስን ጌታችን ኢየሱስ እንደ ተናገረው፣ “በሰማያት ያለው አባቴ እንጂ ሥጋና ደም ይህን አልገለጠልህምና ብፁዕ ነህ።” (ማቴ. 16፥17)፤ እንዳለው። ዛሬ ላይ ብዙዎች ኢየሱስን እናውቃለን ቢሉም፣ ዕውቀታቸው ከኒቆዲሞስ ዐይነት ዕውቀት የዘለለ እንዳይደለ ማስተዋል እንችላለን።
    በኢየሱስ ረክቶ ለመቅረትና በትክክል ለመናገር ዳግመኛ መወለድ ያስፈልጋል። ዳግመኛ በትክክል ሳይወለዱ ስለ ኢየሱስ መናገር ይቻላል፣ ንግግሩም “እውነት” ሊኾን ይችላል፤ ነገር ግን ኢየሱስ ስለ እርሱ ከሚነገረው እውነት ይልቅ የሚነገርበትን መንፈስ በትክክል ይመዝናል። ነፋስ ሲፈልግ አንድን ነገር ወደ ራሱ እንደሚወስድ ወይም እርሱ ራሱ ወደሚፈልገው ነገር እንደሚወስደው እንዲሁ፣ መንፈስ ቅዱስም የኢየሱስን ነገር ወደ ሰዎች ያመጣል ወይም ሰዎችን ወደ ኢየሱስ ይወስዳል። ጌታ ኢየሱስ ኒቆዲሞስን እንዲህ ልትኾን ይገባሃል አለው፣ መንፈሱ ሊያገኝህ ወይም መንግሥቱ ሊገለጥልህ ይገባሃል፣ አልያ ይህን መናገር አትችልም አለው።
   ከዚህ የሚልቀውና እጅግ የሚበልጠው ነገር ደግሞ ሌላ ነገር አለ አለው፤ “ከሰማይም ከወረደ በቀር ወደ ሰማይ የወጣ ማንም የለም፥ እርሱም በሰማይ የሚኖረው የሰው ልጅ ነው።” (ቁ. 13) ስለ መዳን ወይም ስለ ዳግመኛ መወለድ ከመረዳት የሚበልጠውና የሚልቀው ኢየሱስ ከሰማይ እንደ ወረደ ማመንና የክርስቶስን መሲሐዊነት በትክክል መቀበል ነው። ይህ ለኒቆዲሞስ፣ ለፈሪሳዊውው፣ ለአይሁድ አለቃ፣ ለእስራኤል መምህር … እጅግ ከባድ ትምህርት ነው። ምክንያቱም አይሁድ ኹሉ ለመቀበል እጅግ የተቸገሩት የኢየሱስን መሲሕነት ወይም ክርስቶስ መኾንን ነውና። ዋናው ነገር መወለድ አይደለም፣ ዋናው ነገር መሲሑን በመሲሕነቱ በትክክል መቀበል እጅግ ይበልጣል።
   የኒቆዲሞስ ትልቁ ስህተት የዳግመኛ ልደትን ነገር አለማመኑ አይደለም፣ ይልቁን የኢየሱስን ከሰማይ መውረድ አለመቀበሉና አለማመኑ እንጂ። ኢየሱስ ከልጅነት፣ ከዳግመኛ ልደት ወይም ዳግመኛ ከመወለድ፣ ከዘላለም ሕይወት እጅግ ይበልጣል። ከተሰጠን ልጅነት፣ ካገኘነው ከዘላለም ሕይወት፣ ከመንፈሳዊ ጸጋዎች ኹሉ ይልቅ ኢየሱስ ልዩና አቻ የሌለው ነው፤ ይበልጣል፣ ይልቃል፣ አይተካከልም!!! ኒቆዲሞስ ስለ ኢየሱስ እውነቱን ቢመሰክርም፣ የሚመሰክረው ግን የማያምነውንና ያላየውን ነው።
   ዛሬም ብዙ አማኞችና አገልጋዮች የሚመሰክሩትና የሚዘምሩት፣ ጮኸው የሚናገሩት የሰሙትን፣ ያነበቡትን፣ የተሰበኩትን … እንጂ ያዩትንና የቀመሱትን፣ የተገለጠላቸውንና በትክክል የሚያምኑትን አይደለም። ኒቆዲሞሳውያን በዘመናችን ፈልተዋል፣ ያልኖሩትን ለፋፊዎች፣ ያልቀመሱትን አዋጆች፣ ያልተገለጠላቸውን ሰባኪዎች፣ ያላዩትን ዘማሪዎች ቊጥራቸው ጥቂት አይደለም። በትክክል የእግዚአብሔር መንግሥት የተገለጠችለትና ኢየሱስን በክርስቶስነቱ የሚያውቀውና የሚያምነው አማኝና አገልጋይ ኢየሱስን ከምንምና ከማንም ጋር አያስተያየውም፤ ከምንም ነገር ይልቅ እጅግ ያልቀዋል፣ ያገንነዋል፣ አለልክ ከፍ ከፍ ያደርገዋል።
   የኢየሱስ መሲሕነትና ከሰማይ መውረድ በአይሁድ ዘንድ የተናቀና የተዋረደ ነው፤ ስለዚህ ኒቆዲሞስ ይህን እንዲያምን፣ ይህን ማመንም ከኹሉ እንደሚልቅና እንደሚበልጥ ከጌታ ተነገረው፤ ጌታና ኒቆዲሞስ ሃሳባቸው በምን እንደ ተቋጨ ወንጌላዊው አይነግረንም፤ የንግግራቸውን ማሰርያ ግን እንዲህ በማለት ይገልጠዋል፣ “ከሰማይም ከወረደ በቀር ወደ ሰማይ የወጣ ማንም የለም፥ እርሱም በሰማይ የሚኖረው የሰው ልጅ ነው።” በሚል ጠንካራ ሐረግ! አዎን! ኢየሱስን የሚመስል ማንም የለም! ተካካይም የለውም!
   በዛሬ ዘመን ክርስትና፣ ልጅነት አለልክ የተለጠጠውን ያህል ምንም ተለጥጦ የተተረጐመ ነገር ያለ አይመስልም። ልጅነት የእግዚአብሔር ስጦታ መኾኑ ተዘንግቶ ወደ እግዚአብሔርነት ማደጊያ ተደርጎ ከተወሰደ ሰነባበተ። በዘመናችን ያሉ ብዙ “ጣፋጭ” ትምህርቶች ልጅነትን አንቈለጳጳሽ፣ አወዳሽ፣ አሞጋሽ፣ አሟኳሽ … ናቸው። ነገር ግን ኢየሱስ ከኹሉም በላጭና ካሰበነው በላይ፣ ካለንም ነገር በላይ፣ የመጀመርያም የመጨረሻም ነው!!!
    በእርግጥ ስለ ኒቆዲሞስ ወደ ፊት ስናነብ፣ ስለ ኢየሱስ መልካም ነገር በመናገሩ ተነቅፏል፤ (ዮሐ. 7፥48-52)። አስቀድሞ ግን ኢየሱስን ማወቅና ማላቅ ለየቅል እንደ ኾነ አላስተዋለም። ኢየሱስን ማላቅ፣ ማግነን፣ ማተለቅ፣ ከፍ ከፍ ማድረግ … ከመዳናችን፣ ከዘላለም ሕይወታችንም ይበልጣል። በኢየሱስ ያልረካ ሰው፣ ባገኘው ነገር ኹሉ አይረካም፣ ሰዎች አማኝ ኾነው ወደ ፖለቲካ፣ ወደ ምድራዊ ነገር ሲያደሉ … የተረዳሁት እውነት፣ ኢየሱስን በዕውቀት ደረጃ እንዳወቁት እንጂ ከምንም በላይ አድርገው ብቻውን እንዳላላቁት፣ እንዳላላከበሩት ነው፤ መንፈስ ቅዱስ ብቻውን ኢየሱስን በሕይወታችን ያብራራው፣ ይግለጠው፣ ያተልቀው፣ ያግንነው፣ ከፍ ከፍ ያድርገው፤ አሜን።  



No comments:

Post a Comment