Friday 12 April 2019

ራሴን ያየሁበት ምስል

Please read in PDF
  

ይህን ምስል ስመለከት ኹለት የተቃረኑ ሃሳቦች ወደ ውስጤ መጡ፤ አንደኛው የካቶሊኩ ፖፕ ስለምን እንዲህ ራሳቸውን አዋረዱ? ምን ይኾን ልቡናቸውን የነካው? ከአራት መቶ ሺህ በላይ በጦርነት የተፈጁትና ያለቁት የኑብያ ልጆች [ሱዳናውያን]  አንጀታቸውን አድብነው፣ ጉበታቸውን አፍርሰው፣ በመሪር እንባ በፊታቸው ድቅን ብለውባቸው ይኾንን? የዓለም መገናኛ ብዙሃን እንኳን ሊዘግበው ሊመለከተው ያልወደደውን የኑብያን ልጆች [የሱዳናውያንን] ሰቆቃ በአካል ሄደው ተመልክተውት ራሳቸውን ስተው ይኾንን? እንዲህ በማድረጋቸውስ “የሱዳኑ መሪ” ልቡ ይሰበር ይኾንን? የመቶ ሺህዎቹ የኑብያ ልጆች ኅሊናውን አልገደለው፣ ልቡን አላደነደነው ይኾንን? የፖፕ ፍራንሲስ “ውርደት” የራሱ “ውርደት” እንደ ኾነው ይሰማው ይኾንን?! በመላ ዘመኑ የኑብያዋ የሱዳን መሪ የእኒህን ፖፕ ድርጊት መዘንጋት ይቻለው ይኾን? ስል ...

   በሌላ መልኩ ደግሞ ፖፕ ፍራንሲስ ከአራት መቶ ሺህ በላይ ኑብያውያንን ደምና አጥንት፣ ያፈሰሰውና ያረገፈውን ጨካኝ መሪ ያለ አንዳች ፍርሃት መውቀስና መገሰጽ ሲገባቸው ለምን በእግሩ ላይ ተደፉ? ይልቁን እንደ ቃለ እግዚአብሔር ፊት ለፊት ሊናገሩት፣ ያፈሰስከውን ደም እግዚአብሔር ከእጅህ ይቀበለዋል፤ ይበቀልሃልም፤ ይህ ደግሞ እጅግ አስፈሪ ፍርድ ነው፤ ንስሐ ልትገባ፣ ራስህን ልታዋርድ፣ የበደልካቸውን ይቅርታ ልትለምን፣ ዝቅ ብለህም ልትክስ ይገባሃል … ብለው በፍጹም መንፈሳዊ ጭካኔ ስለ ምን አልገሰጹትም? ለምን ያለ ፍርሃትስ አልተቈጡትም? ብዬ ቀኑን ሙሉ ከራሴ ጋር ስሟገት ነበር የዋልኹት?
   እግዚአብሔር ግን አዋቂ ነው!
  ከዚህ ኹሉ በላይ ምስሉ ራሴን እንድመለከተው ዓመታትን ወደ ኋላ ሳበኝ፤ በልጅነቴ ወራት ከብቶችን የማግድ እረኛ ነበርኩ፤ ከብቶቹን ከማስመስክበት አቅራቢያ “ከእኛ ብሔርና ሃይማኖት ያልኾነ [ፕሮቴስታንት የኾነ]” ማሳ ወይም እርሻ የነበረው አንድ አባት ነበር፤ እኔ ከብቶቻችንን ነድቼ የማልፈው የዚህን ሽማግሌ ማሳ ወይም እርሻ አልፌ ነው፤ የሽማግሌው እርሻ ከመንገድ ዳር ነበርና የምነዳቸውን ከብቶች ወደዚህ ሽማግሌ ማሳ ኾን ብዬ ከብቶቻችንን ነድቼ አስገባና ዝም ብዬ እመለከት ነበር፤ መመልከት ብቻ አይደለም ዘፈን እየዘፈንኩ፣ በዘፈኑ መካከል ደግሞ የሽማግሌውን ስምና ብሔር አስገብቼ እሳደብ፣ አንጓጥጥ፣ አሸሙር፣ አላግጥ፣ አፌዝ … ነበር፡፡
   አንድ ቀን ግን እጅግ አስደንጋጭ ነገር ተመለከትሁ፤ እኒህ ሽማግሌ አሥራ አምስት ዓመት ዕድሜ የማልሞላውን እኔን ተንበርክከው በእንባ ለመኑኝ፤ በሕይወቴ ደንግጬ የማላውቀውን ድንጋጤ ደነገጥሁ፤ ከዚያን ቀን ጀምሮ ወደ እርሳቸው ማሳ ከብቶችን ማስገባት ተውኩ፤ … ግን ይቅርታ ሳልጠይቃቸው ዓመታት አለፉ፣ ወንጌል ከተረዳሁ በኋላ አደርግ የነበረው ጥፋት፣ በደል መኾኑ ገብቶኝ ንስሐ ገብቼ ይቅርታ ልጠይቃቸው በአድራሻ ሳፈላልጋቸው ማረፋቸውን ሰማሁ፡፡
   ዛሬም ድረስ ግን በጉልበታቸው ተንበርክከው “ከውካዋውን ወጣት አቤንኤዘር” በእንባ የለመኑኝን ልመና ፈጽሞ አልረሳውም፤ ያነቡት እንባ እጅግ ደንዳና ልብ የሚሰብር እንባ ነበር፣ ልመናቸውን አልፌ መሄድ እንዳልቻልኩ ትዝታ አለኝ፤ እሳቸው ማሳ ዘንድ ስደርስ በጣም ተጠንቅቄ አሳልፍ ነበር፡፡ እኒያን አባት አጊኝቼ ይቅርታ ብጠይቃቸው እንዴት ይደሰቱ ይኾን? [የሱዳኑ መሪ የፖፑ ልመና ልቡን ብትንትኑን አውጥቶ ይሰባብረው ያደቅቀው ይኾን?] አዎን! ሰው በክፋቱ ሲጸና መራራ ነው፤ ፍጻሜውም ሞት ነው፤ ሲመለስ ግን እውነተኛ አባት እጅግ ደስ ይለዋል፤ አዎን! መመለስ ለተመላሹ[ለተነሣሂው] እረፍት፤ ሲመለስ ላየው ደግሞ እጅግ ደስታና እልልታ ነው፡፡
   በእኛ መመለስ እጅግ ደስ የሚሰኝ፣ መጥፋታችንን የማይወድ አንድ ውድ አባት አለን፤ እግዚአብሔር!!! የጠፋው ልጅ (ሉቃ. 15፥11-32) እንደ ጠፋ እንዳይቀር አባቱ ዘወትር ደጅ፤ ደጅ ማየቱን አልተወም ነበር፤ እግዚአብሔር ስንጠፋበት “ዱካውን” የፍቅር ድምጹን በገነት መካከል እያሰማ መጥቷል፤ (ዘፍ. 3፥8)፣ ቃየል ወንድሙን በገደለ ጊዜም እግዚአብሔር ወደ ቃየል ከመምጣት አላቆመም፤ (ዘፍ. 4፥9)፣ እግዚአብሔር የጠፋ ልጁን ካላገኘ በቀር ፈጽሞ “አያርፍም”፡፡ እግዚአብሔር እንድመለስና ፊታችንን ወደ እርሱ ዘወር እንድናደርግ ዘወትር ዕድልና የንስሐ በር፣ ጆሮአችንን እየኮረኮረ እንድንሰማው ጭምር በማድረግ ጸጋውን ያበዛልናል፤ ያትረፈርፋልም፡፡ መመለስ ግን የእኛ ድርሻ ነው!!!
    እግዚአብሔር ለእኛ ልዩ አባታዊ ርኅራኄ አለው፤ ርኅራኄውንም በአንድያ ልጁ ገልጦልናል፣ እንድንመለስም ዘወትር በመንፈሱ ይማልደናል፤ እንድንመለስ፣ ከኀጢአት ጋር እንቆራረጥ፣ የልጁን መስቀል ብቻ እንድንመለከት፣ በማዳኑ እረፍት እንዲኾንልን ይፈልጋል፤ ወዳጆቼ! በእውነተኛ ልብ ልጁ ኢየሱስን በመውደድ ንስሐ በመግባት እንድንመለስና እንድናርፍ ጸጋውና መንፈሱ ይርዳን፤ አሜን፡፡ የሱዳኑ መሪ ሆይ! ጌታ መንፈስ ቅዱስ ልብህን ያራራው! የወገኖችህን እንባ ማበስ እንድትችል ጸጋው ይደግፍህ! ፖፕ ሆይ! ጸጋ ይብዛልዎ! ጌታ ኢየሱስ ሞገስና መወደድን ያብዛልዎ! አሜን!!!

No comments:

Post a Comment