Sunday 7 April 2019

በጎና ክፉ ባሪያ (ሉቃ. 19፥11-27)

Please read in PDF

   የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ዋቢ ያደረገው ዓቢይ ጾም፣ የጾሙ ሳምንታት በየራሳቸው ስያሜ አላቸው፤ ስያሜዎቹን የሰየመው “የዜማ ደራሲው” ያሬድ ሲኾን፣ የጌታ ኢየሱስን ሕይወቱንና ትምህርቱን ከወንጌላት በመውሰድ የሰየማቸው ነው። በኢትዮጵያ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ኢ መጽሐፍ ቅዱሳዊ የኾኑ ብዙ ትምህርቶች ያሉትን ያህል፣ ከጅማሬአቸው መልካም የነበሩና አኹንም ድረስ በመልካም ምሳሌነት የተያዙን አንጥሮ፣ በመጽሐፉ ቃል መዝኖ መቀበል ደግሞ ለእኛ ለአማንያን የተተወ ነው። ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የተገኘውን ኹሉ እንድንቀበል ሳይኾን በመጽሐፍ መዝነን እንድንቀበል ቃሉም መንፈሱም ይመክሩናልና።
   የዚህኛው ሳምንት ስያሜ ገብር ኄር ይባላል፤ ትርጉሙም መልካም ወይም ትጉህ ባርያ ማለት ነው፤ ይህ ስያሜ ደግሞ የተወሰደው ከማቴ. 25፥14-30 ወይም ከሉቃ. 19፥12-27 ካለው የወንጌል ክፍል ነው፤ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይህን ክፍል የተናገረው ለሞቱ ወደ ኢየሩሳሌም እየወጣ በነበረበት ወራት ነው፤ በተናቁትና በተገፉት፣ በኢየሩሳሌማውያን ፈጽመው በማይወደዱት ገሊላውያንና መንደሮቿ መካከል የቆየውና የነበረው ጌታችን ኢየሱስ፣ አሁን ለሞቱ ወደ ኢየሩሳሌም መጥቷል። በገሊላ የነበሩት እጅግ የተናቁ ብዙ ሰዎች ነበሩ፤ ኃጢአተኞችና በኢኮኖሚም ደረጃ እጅግ ዝቅ ያሉ፣ ከፍተኛ የሥነ ልቡና ጫናም የነበረባቸው ሰዎች ጭምር፤ ኢየሩሳሌም ደግሞ በሕጉ የሚመኩና የሚመጻደቁ፣ አግላይና ናቂ፣ ትእቢተኞችና ራሳቸው ብቻ የመሲሑ ተቆርቋሪ እንደ ነበሩ አድርገው የሚያስቡ ፈሪሳውያንና ሰዱቃውን የበዙባት ከተማ ነበረች።

   የጌታ ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም መምጣት ለደቀ መዛሙርቱ የሰጣቸው ትርጉም ሌላ ነበር ፤ ይህንም ትርጉም፣ “ … ወደ ኢየሩሳሌም መቅረቡ ስለ ሆነ የእግዚአብሔርም መንግሥት ፈጥኖ ሊገለጥ እንዳለው ስለ መሰላቸው” (ሉቃ. 19፥11) ከሚለው ሃሳብ እናገኛለን፤ ደቀ መዛሙርቱ መሢሑ በኅይልና በታላቅ ሥልጣን መጥቶ ሮማውያንን በማሸነፍ ምድራዊ መንግሥትን የሚያቋቁም መሰላቸው፤ እናም የጌታ ኢየሱስን ወደ ኢየሩሳሌም መምጣት የተመለከቱት ምድራዊ መንግሥትን የሚያቋቁም መስሏቸው ነው።
   ጌታ ኢየሱስ ይህን ሃሳባቸውን ተመልክቶ ምሳሌ ነገራቸው፤ ምሳሌው በተለመደው መንገድ የተነገረ አይደለም፤ ባልለመዱትና ይኾናል ብለው ባላሰቡት መንገድ የተነገረ ነው፤ እንዲህ በማለት፣ አንድ ሰው የንጉሥ ማዕረግን ተቀብሎ ሊመለስ ውድዶ ወደ ሩቅ አገር ሄደ፤ ከአገልጋዮቹ መካከል አሥሩን ጠርቶ እስክመጣ ነግዱበት በማለት ምናን[1] ሰጥቷቸው ሄደ፤ ነገር ግን የሄደበት አገር ሰዎች ጠሉት፣ በላያችን እንድትነግሥ አንፈቅድም ብለው መልእክተኞችን ላኩበት፤ ዳሩ ይህ ሰው ንጉሥ ኾኖ ወደ አገሩ ተመለሰ፤ ከዚያም እንዲነግዱበት ምናን የሰጣቸውን አገልጋዮቹን ጠርቶ፣ በሰጣቸው ገንዘብ ነግደው ምን ያህል እንዳተረፉ ለማወቅ አስጠራቸው፤ አንዱ አሥር ምናን አተረፈበት፣ ሌላው አምስት ምናን አተረፈበት፣ አንዱ ግን “በጨርቅ ጠቅልዬ የጠበቅኋት ምናንህ እነሆ፤ ፈርቼሃለሁና፥ ጨካኝ ሰው ስለ ሆንህ፤ ያላኖርኸውን ትወስዳለህ ያልዘራኸውንም ታጭዳለህ አለው” ብሎ መለሰ።
   ኹለቱ ያተረፉትን ባተረፉበት ልክ የምናኑ ጌታ ሲሸልማቸው፣ ያላተረፈውን አንዱን ግን የምናኑ ጌታ፣ “አንተ ክፉ ባሪያ፥ አፍህ በተናገረው እፈርድብሃለሁ። እኔ ያላኖርሁትን የምወስድና ያልዘራሁትን የማጭድ ጨካኝ ሰው እንደ ሆንሁ አወቅህ፤ ምን ነው ገንዘቤን ለለዋጮች አደራ ያልሰጠኸው? እኔም መጥቼ ከትርፉ ጋር እወስደው ነበር” በማለት በጽኑ ወቀሰው።
  የምናኑ ጌታ ንጉሥ ለመኾን ወደ ሩቅ አገር መሄዱ ግልጽ አይደለም፤ ደግሞም የተለመደ አካሄድ አይደለም፣ ዳሩ ግን ሄሮድሳውያን አይሁድን ሊገዙ ወደ ሮም እንደ ሄዱ ከዚያም ለመግዛት እንደ መጡ እንዲሁ፣ ኢየሱስም ወደ አባቱ ከሄደ በኋላ፣ ወደ ፊት በክበበ ትስብእት በግርማ መለኮት ይመጣል፤ እስኪመጣ ግን አማኞቹና አገልጋዮቹ ምናን ወይም ኃላፊነት ተሰጥቷቸዋል፤ በሉቃስ ወንጌል በተጻፈው ምሳሌ ላይ ለአገልጋዮቹ የተሰጣቸው ምናን እኩል አሥር፤ አሥር ነው። የተሰጠን ጸጋ ወይም ኃላፊነት የአንዳችን ከሌላችን አይበልጥም፣ በግልጥ ምሳሌም በአማኝና በአማኝ መካከል አንዳችም መበላለጥና መቀዳደም የለበትም። ልክ ማስተማርም መስማትም፣ መስበክም ስብከት መስማትም … እንደማይበላለጠው ማለት ነው።
  ንጉሡ እንዲቀበሉት ቢፈለግም የአገሩ ሰዎች ግን ሊቀበሉት አልወደዱም፤ ይህ ክፍል ማስጠንቀቂያ አይሁድ የኢየሱስን ንጉሥነት እንዲቀበሉ ለማስጠንቀቅ የተነገረ መኾኑን ያስረዳል፤ ምንም እንኳ መሢሑ በውርደት መንገድ የመጣ ቢኾንም፣ ይህንኑ ኢየሱስ እንዲቀበሉ ጥሪው ለአይሁድ ቀርቧል። በምሳሌው ላይ እንደ ተነገረው ኹለቱ አገልጋዮች የጌታቸውን ትእዛዝ በትክክል ተቀብለዋል። ከተናገረው አንዲቱንም አላጎደሉም። የምናኑን ጌታ በትክክል ታዘውታል። ኢየሱስን በትክክል ካመንን፣ ማመናችንን የምንገልጥበት መንገድ በትክክል መታዘዛችን ነው። እንዲህ ያለውን አማኝና አገልጋይ በጎና መልካም አማኝ ነው ማለት ማለት ይቻላል። እንዲህ ላሉ አማኞችና አገልጋዮች ጸጋና ሽልማት አላቸው፤ ይጨመርላቸዋልም።

 አንዱ ግን በትክክል የታዘዘ አልነበረም፤ የተቀበለው ምናን ታዝዘው ካተረፉት የሚያንስ አልነበረም፤ የተቀበለው እኩል ምናን ነው። ነገር ግን የታዘዘ አልነበረም፣ አምኖ ምናኑን ከምናኑ ጌታ የተቀበለ ቢኾንም፣ ነገር ግን በተቀበለው ምናን ነግዶ፣ አገልግሎ፣ ታዝዞ ያተረፈበት፣ ለሌሎች ቆርሶ የሰጠው አልነበረም፤ ይልቁን ማንም እንዳያገኘው ሸሸገው፣ ቆፍሮ ቀበረው፤ ይባስ ብሎ የምናኑን ጌታ ንግግር ትክክል እንዳልነበረ ነቀፈ፤ ነገር ግን ለተናገረበት ነገር ጌታው መልሶ በጠየቀው ጊዜ አገልጋዩ መልስ መስጠት አልተቻለውም።
   በትክክል እንደ ቃሉ የማይታዘዝ አማኝ ኢየሱስን በትክክል አያምነውም። ተቀብለን እንዳልተቀበለ ሰው መኖር አንችልም፤ ድነን እንዳልዳነ ሰው መኾን አንችልም፣ ባለምናን ኾነን ምናን እንዳልተቀበለ ሰው ዘመናችንን መግፋት አንችልም፤ የሰጠን ከነትርፉ ሊቀበለን ይመጣል፣ ያዳነን የዳንበትን የኑሮ ፍሬ ማየት ይፈልጋል፤ ይህ ባይኾን ግን የተቀበልነውን የምንንቅ፣ የዳንበትን የምናቆሽሽ፣ ምናናችንን የምናባክን አማኝና አገልጋዮች ያለንንና የተሰጠንን በማጣት በፍጹም ድህነትና እጦት፣ ስቃይና መከራ እንደኸያለን፣ እንማቅቃለን፣ እንሳቀያለን።
   ኢየሩሳሌም መሢሑን ባለመቀበሏ በ70 ዓ.ም ባድማ እስክትኾን ድረስ በሮማውያን የደረሳብትን አስተውሉ! ኢየሱስን በትክክል የማይቀበሉና የማይታዘዙት ፍጻሜያቸው እጅግ መራራ ነው። በምናኑ ጌታ ላይ የሚያምጹ ኹል ጊዜ ከመቀጣት አያመልጡም፤ ይልቁን ችላ ካሉት በላይ መራራ ቅጣትን ይቀጣሉ።
   እንግዲያውስ፣ የመልካምነት መለኪያው የሰዎች ሃሳብ ወይም ሚዛን አይደለም፤ እውነተኛ አማኞች ወይም አገልጋዮች ከኾንን እኛን መልካም ኾነ ክፉ ማለት የሚቻለው ኢየሱስ ብቻ ነው፤ የእምነታችንም ኾነ የአገልግሎታችን ሚዛኑ ያለው በክርስቶስ ወይም በምናኑ ጌታ እጅ ብቻ ነው። የምንጨነቀው በምናኑ ጌታ በኢየሱስ ፊት ላለመወቀስና ላለመቀጣት እንጂ ሌሎች ስለሚሉን ነገር አይደለም፤ ካመንን መልካም ባርያ የሚለውን ሽልማት ለመቀበል ከፈለግን፣ ለኢየሱስ በትክክልና እንደሚገባ መታዘዝ ይኖርብናል፤ በአፍ ብቻ ማመናችንን በመግለጥ ግን እንደሚገባ ባንታዘዝ፣ ክፉ ባርያ ከመባል የምናመልጥ አይደለንም። መልካምና ታዛዥ ባርያዎች እንድንኾን ጌታ በመንፈሱ ያግዘን፤ አሜን።
 




[1] በጥንት የክብደት መለኪያ ሲኾን (ዕዝ. 2፥69)፣ በኋላ ገንዝብን አመለከተ፣ (ሉቃ. 19፥13)፤ አንድ ምናን የመቶ ዲናር ህል ዋጋ ነበረው። (የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት ገጽ 59 እና 241።

No comments:

Post a Comment