Monday 4 June 2018

ደቂቀ እስጢፋኖሳውያንና የ“ዲያቆን” ዳንኤል ክብረት የክፋት ሸፍጥ (ክፍል ፫)

Please read in PDF
ንጉሥ አለ መስገድ ከጥበብ መጉደል ነውን?

“ … የደረሰባቸው ነገር የደረሰባቸው በኹለት ምክንያት ነው፤ አንድ አባ እስጢፋኖስ ጥበበኛ ባለ መኾኑ ምክንያት ነው፤ ነገሥታቱ ላይ የነበረውን ስህተት ብቻ ከመንቀስና ጳጳሳቱ ላይ ብቻ የነበረውን ስህተት ከመንቀስ ይልቅ እነዚህ ዓይነት የሥነ መለኮት ክርክሮቹንና ነገሥታቱ ላይ ያሉ ተቃውሞዎች ኹለቱን አንድ ላይ ቀላቀላቸው፤ እነዚህ ኹለቱ ሲቀላቀሉ ጠላት አፈሩበት ማለት ነው …” (ዳንኤል ክብረት)

  ዳንኤል ክብረት፣ ለእውነተኞቹ ቅዱሳንና ሰማዕታት ያለውን ንቀትና የራሱን የታሪክ አልኰስኳሽነት በዚህ ንግግሩ ያለኃፍረት በአደባባይ ይገልጣል። ሰማዕታት፣ አላውያንና ጨካኝ ነገሥታትን፣ ገዢዎችን ፊት ለፊት መቃወማቸው የጥበብ መጉደል መንገድ እንደ ኾነ ሊሰብከን ይፈልጋል። “ስገዱልን” የሚሉ ፍጡራንን በመቃወም የሚመጣውን መከራና ከባድ ሰቆቃ ከነገረ መለኮት ጋር የሚቀላቀል “የአላዋቂ ጥበብ” አድርጐ ለማቅረብ ርምጥምጥ ሃሳቦችን ያቀርባል።
  ዳንኤልን፣ እስኪ እኒህን ጥያቄዎች እናንሳለት፤ ሦስቱ ሕጻናት ንጉሥ ናቡከደነጾር በዱራ ሜዳ ላይ ላሠራው ጣኦት፣ “… የምናመልከው አምላካችን ከሚነድደው ከእሳቱ እቶን … ባያድነን፥ አማልክትህን እንዳናመልክ ላቆምኸውም ለወርቁ ምስል እንዳንሰግድለት እወቅ” በማለት ፊት ለፊት በግልጥ መቃወማቸውና ከእሳት መጣላቸው ጥበበኛ ባለ መኾናቸው ነውን? (ዳን. 3፥17-18)፣ መርዶክዮስ ለአጋጋዊው ለሐመዳቱ ልጅ ሐማ አንገቱን ሰብሮ ባለ መስገዱ ምክንያት በሱሳ ግንብ ሥር ባሉ አይሁድ ኹሉ ላይ ሞት ማስፈረዱ ከጥበብ መጉደል ነውን? (አስ. 3፥2፤ 15)፣ ዮሐንስ ወንጌላዊ ለንጉሥ ድምጥያስ አልሰግድም በማለቱ በፈላ ዘይት ተቀቅሎ በፍጥሞ ደሴት መጣሉና በዚያ ለብዙ ዓመታት በእስር መቆየቱ ጥበበኛነት ባይታይበት ነውን? ቅዱስ ፓሊካርፐስ በትራጃን ዘመነ መንግሥት ንጉሡ ስገድልኝ ሲለው፣ “ሰማንያ ስድስት ዓመት ሳገለግለው አንድም ቀን ያልበደለኝን ጌታዬን ኢየሱስ ክርስቶስን አልበድልም” ብሎ በሕዝብ አደባባይ በእሳት ተቃጥሎ በሰማዕትነት መሞቱ ጥበበኛ አለ መኾንን፤ ከነገረ መለኮት ክርክር ጋር ቀላቅሎ [ተምታቶበት] ነውን? አግናጢዮስ ምጥው ለአንበሳ፣ አረመኔውን ንጉሥ ሊሠማ ባለመውደድ ለአንበሶች የምግብ ሲሳይ የኾነው በውኑ ጥበብ ጐድሎት ነውን? በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ከ286 [አንዳንዶች ከ96 ዓ.ም ጀምሮ ያደርጉታል] ዓ.ም እስከ 315 ዓ.ም ድረስ ዘመነ ሰማዕታት ወይም የቤተ ክርስቲያን የስደት ዘመን እየተባለ ይጠራ በነበረበት ዘመን እነዚያ ድንቅ የቤተ ክርስቲያን ከዋክብት የታረዱት፣ ሰም ተቀብተው በሮማ አደባባዮች እንደ ጧፍ ቀልጠው የነደዱት፣ ለአንበሳ የተጣሉት፣ ቆዳቸውን እንደ በግ የተገፈፉት፣ በመንኩራኩር የተፈጩት … አንደኛና ዋነኛው ምክንያታቸው እኮ ለአላውያን ነገሥታት አንሰግድም፣ አንንበረከክም፣ በፊታቸውም አንደፋም በማለታቸው እንደ ነበር የዳንኤል ዐይኖች ምነው ማስተዋል ተሳናቸው? … ነው ወይስ ይህን የታሪክ ክፍል አልመረመረም?! ብለን እንድንጠይቅ ያስገድደናል።

 ሰዎች የራሳቸውን ሃሳብ ወደ ቅዱሳት መጻሕፍት ሲያስገቡና አስገብተውም እንግዳ የኾነን ትምህርት ሲያስተምሩ፣ መጽሐፉ የማይለውንም ሲናገሩ ይህ ተግባራቸው ሰጊጐት (Eiesegesis) ይባላል። በሚስያገርም ኹኔታ የራስን ሃሳብ ወደ ታሪክ እውነታ በማስገባት፣ ታሪክ ከሚያዛቡ ሰዎች መካከል ዳንኤል ክብረትን የሚስተካከለው ያለ አይመስለኝም። በእስጢፋኖሳውያን ዙርያ የተናገረውን ማንሣት በቂና ለዚህ ዋና ማሣያ ነው፤ ለእስጢፋኖሳውያን ከፍ ያለ መከራ መቀበል ምክንያቱ፣ አንዴ የስግደት ጉዳይ ነው ይልና፣ መልሶ ደግሞ የእስጢፋኖስና እስጢፋኖሳውያን አሰቃቂ መከራ መቀበል የእነርሱ ጥበብ መጉደል ነው ይለናል፤ አኹንም ይመልስና “ … ነገሥታቱና ጳጳሳቱ ላይ የነበረውን ስህተት ብቻ መንቀሱ … እኒህን የሥነ መለኮት ክርክሮቹንና ነገሥታቱ ላይ ያሉ ተቃውሞዎች ኹለቱን አንድ ላይ በመቀላቀሉ ነው” በማለት የክፋት ሸፍጡን “ይሸፍጣል”
 “እስጢፋኖሳውያን ለአፄው ሰግደው ቢኾን ኖሮ ይህ ኹሉ የመከራ ዓይነት ባልደረሰባቸው ነበር” የሚለው ሃሳብ፣ ከአንድ “ሰባኪ” እንደ ኾነ ከሚናገር ሰው የሚጠበቅ አይደለም። ዳንኤል፣ “እስጢፋኖሳውያን ክብርን መስጠት አለባቸው” ሲል፣ ለንጉሡ መስገድ እንዳለባቸው ያምናል ማለት ነው፤ ምክንያቱም ከመጀመርያውም “አምልኮና ስግደት ናፋቂ ለነበረው አፄ” ፈጽሞ ሊሰግዱለት እንደ ማይገባ እስጢፋኖሳውያን በፍጹም ድፍረት መናገራቸውን ያውቃል፤ በተጨማሪም ተአምረ ማርያም ውስጥ፣ አፄው ለሠገሠጓቸው ክፋቶች፣ ምርቅና ፍትፍት ሃሳቦች መገዛት እንደ ማይፈልጉ ጨክነው ተናግረዋል፤ ዳንኤል “እስጢፋኖሳውያን ይህን ነገር መታገስ ነበረባቸው” በማለት፣ ከ“ሰባኪነቱ” አይፎርሹ ይፎርሻል።
 ለመኾኑ ዳንኤል ክብረት እንዲህ ብሎ ከተናገረ፣ መጽሐፈ አስቴርን ለማስተማር ምን ሞራልና ብቃት ይኖረው ይኾን? ምክንያቱም በእርሱ ዕይታ መርዶክዮስ ለሐማ አለ መስገዱ ከጥበብ መጉደል ይሆናላ? መርዶክዮስ ቢሰግድ ኖሮ፣ ሐማ በእስራኤል ላይ ሞትን አያሳውጅም ነበራ!!! ይህ ግን የልጅ ጨዋታ ነው! ዳንኤል ክብረት፣ በመንፈሳዊ ጉዳይ ምን ያህል “ልዝብና ኢ መጽሐፍ ቅዱሳዊ” አስተምኅሮ እንዳለው እናስተውላለን፤ ምናልባትም የአኹኑ ጠቅላይ ሚኒስቴር ድንገት፣ “ስግደት ይገባኛል አልያ ሰዎችን እፈጃለሁ” ቢሉ፣ ዳንኤል እስጢፋኖሳውያንን በተቸበት ጥበቡ ብዙዎችን ለጠቅላዩ “ከማለቅና ከመፈጀት እንስገድ” በማለት፣ አያሰግድም ማለት ዘበት ላይኾን ይችላል፤ ደርሶ ሰማዕት ልኹን ካላለ በቀር!!!
 አፄ ዘርዓ ያዕቆብ ልጆቹን የገደለው “ለአምላክ ክብር ቀንቶ እንደ ኾነ” ይነግረናል፤ የልብን ሃሳብ እንዳፈቀዱ እያደረጉ በቅዱሱ አምላክ ማሳበብ፣ ቅድስናውን መናቅ አልያም ባሕርዩውን አለማወቅ ነው። ለመኾኑ ”ያልታዘዘ ልጅህን ግደልልኝ የሚል አምላክ አለን? ካለስ ማን ነው? ይህ ጸያፍ አድራጐትን የሚደግፍ የትኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ምንባብ ነው? በእውኑ አፄ ዘርዓ ያዕቆብ የገዛ ልጆቹን የገደላቸው የመንግሥቱን ክብር ሊጠብቅ ወይስ “የእግዚአብሔርን ክብር” ሊጠብቅ? አፄው የወንጌል ልብ እንደ ሌላቸው አድራጐታቸው በትክክል ይመሰክርባቸዋል፤  “ከወንጌል ያፈነገጠ የቅዱሳት መጻሕፍን እውነት የረገጠ” እንደ መንገደ ሰማይና “የቅዱሳንን ብልት” እየጠራ የሚያሞካሽ፣ የሚያወድስ፣ የሚያንቆለጳጳስ ሥራዎቹ ደግሞ ለወንጌልና ለጌታ ኢየሱስ ትምህርቶች ምን ያህል ባዕድና እንግዳ እንደ ኾኑ ይመሰክርባቸዋል። እና ለዚህ ጨካኝ አፄ አለመስገድ “ከጥበብ መጉደል ነው” ያስብላልን?
 እንግዲህ እስጢፋኖሳውያን ፅህማቸው የተነጨው፣ ደማቸው እንደ ውኃ የፈሰሰው፣ በረሃብና በብዙ መከራ ውስጥ ያለፉት፣ የታሠሩት፣ የተገደሉት፣ ቆዳቸውን የተገፈፉት … ጥበበኞች ስላልኾኑ አይደለም፤ የወንጌል መንገድ፣ “ለፍጡር አልሰግድም! ስግደት ለአንድ አምላክ ብቻ ነው!” ማለትና የመጨረሻ ጥጉም ይህን በመመስከር የሚመጣውን መከራና ስቃይ በመቀበል ማለፍን የሚጠይቅ መንገድ ስለኾነ ነው። ሰማዕታት የዚህን ዓለም ጣዕም የናቁት፣ መከራውን ኹሉ በመታገስ በማስጨነቅ ፍርድ ከመንገድ ኹሉ የተወገዱት ያመኑትን አምላክ በሞታቸውም ጭምር ለማክበር እንጂ ከጥበብ ጐድለው ወይም መደራደር የማይችሉ ኾነው አይደለም። መደራደር ይችላሉ፤ ሲደራደሩ ግን የዘለዓለም ክብራቸውን ያጣሉ፤ ከዘላለም ክብር ይልቅ ደግሞ የጊዜውን መከራ ሞትንም ቢኾን እንኳ ይመርጣሉ።
  ለእግዚአብሔር ክብርና ቅንአት ሞት ከጥበብ መጉደል አይደለም፤ ለእግዚአብሔር ወንጌልና ለክርስቶስ የመስቀል ላይ ሥራ መናቅ፣ መሰደብ፣ መተቸት፣ መዋረድ፣ መንገላታት፣ መራብ፣ መጠማት፣ መታረዝ፣ መታሰር፣ በባርነት መሸጥ፣ መሰደድ፣ መሰየፍ፣ መፎነን፣ መቆረጥ፣ ደም ማፍሰስ፣ መገደል … ቅንጣት ታህል ከጥበብ መጉደል አይደለም፤ ይህን ማምለጥም አጉል ብልጠትና ከእግዚአብሔር ሃሳብ መውጣት እንጂ ፈጽሞ ክብርና ሞገስ የለበትም። ይልቁን ይህን መሸሽ ሞኝነት፣ ራስን መውደድ፣ ራስን አለ መካድ፣ መስቀሉን ለመሸከም ፈጽሞ አለ መፍቀድ ነው። “መስቀሉንም የማይዝ በኋላዬም የማይከተለኝ ለእኔ ሊሆን አይገባውም። ነፍሱን የሚያገኝ ያጠፋታል፥ ነፍሱንም ስለ እኔ የሚያጠፋ ያገኛታል።” (ማቴ. 10፥38-39) እንዲል ጌታችን ኢየሱስ።

ገረ መለኮታዊ ክርክር?

 ከእግዚአብሔር በቀር ለሌላ አልሰግድም ማለት፣ ነገረ መለኮታዊ ክርክር ነው ወይ? ለፍጡር ፈጽሞ አልሰግድም ማለት፣ ምን የተለየ ምልከታ(View) አለውና ነገረ መለኮታዊ ክርክር ሊኾን የሚችለው? ልዩ ልዩ ምልከታዎች የነገረ መለኮት ትምህርት ቤቶች ፅንሰ ምክንያቶች ናቸው፤ ለምሳሌ፦ የእስክንድርያና የአንጾኪያ ትምህርት ቤቶች በጥንት አባቶች ሲመሠረቱ፣ በመካከላቸው የተለያዩ ምልከታዎችን የያዙ ናቸው፤ ለምሳሌ፦ አንዱ “አንድምታዊ” ወይም ምስጢራዊ ትርጓሜን (Allegorical) ሲከተል፣ ሌላው ደግሞ ንባባዊ ትርጓሜን(Literal) ተከታይ ነበሩ፤ ኹለቱም ትምህርት ቤቶች ግን ከእግዚአብሔር ውጭ ላለው ፍጡራዊ ስግደት አንዳች ድጋፍ የላቸውም፤ ለምሳሌ ከእስክንድርያ ተርቱሊያንን [ሰሜን አፍሪካ]፣ አትናቴዎስን፣ ቄርሎስን፣ … ብንመለከት፣ ከአንጾኪያ ተማሪዎች መካከል ደግሞ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅን [ዘቍስጥንጥንያ]፣ ሳዊሮስንና ሌሎችንም ብንጠቅስ በዚህ ርእሰ ጉዳይ አንዳች ክርክር የለባቸውም። “ለሰው፣ ለአፄ፣ ለፍጡር መስገድ ወይስ ለእግዚአብሔር ብቻ መስገድ ይገባልን? የሚል ክርክር አንድም ዘመን በክርስቲያኖች መካከል “ነገረ መለኮታዊ” ክርክር ኾኖ አያውቅም።
  ነገር ግን በክርስቲያኖችና በአላውያን ወይም በማያምኑና በአንዳንድ እብሪተኛ ሃይማኖት የለሽ አፄዎችና ነገሥታት መካከል ይህ ነገር ሲነሣ፣ ክርስቲያኖች ፊት ለፊት ተቃውመዋል፤ ከመቃወምም አልፈው ባለ መስገድ የሚመጣውን መከራና ማናቸውንም ስቃይ ለመቀበል እጅግ ዝግጁዎች ነበሩ እንጂ። በአፄ ዘርዐ ያዕቆብና በእስጢፋኖሳውያን መካከል በወንጌል ጉዳይ ግልጥ አለመስማማት አለ፤ አፄው አምልኮን፤ ስግደትን ይሻል፤ እስጢፋኖሳውያን ደግሞ ለእግዚአብሔር እንጂ ለአፄውም ኾነ ለማናቸውም ፍጡር ስግደትንና ማናቸውም አንገትን የሚያሰብር ክብር እንደ መርዶክዮስ ላይሰጡ ጨክነዋል፤ ይህን ያደረጉት አይሁዳዊ ስለኾኑ ሳይሆኑ እውነተኛ ክርስቲያን አማኞች ስለኾኑ ነው። አፄው ነገሩን ከቅዱሳት መጻሕፍትና ከእስጢፋኖሳውያን ከመረዳት ይልቅ ቅዱሳኑን ልቡ በፈቀደው ዓይነት መከራ በማረድ አሸናፊነቱን ለማሳየት ጣረ።
  አስተውሉ! እግዚአብሔር አምላክ የእስራኤልን ልጆች ሲያዛቸው እንዲህ አላቸው፣ “ከግብፅ ምድር ከባርነት ቤት ያወጣሁህ እግዚአብሔር አምላክህ እኔ ነኝ። ከእኔ በቀር ሌሎች አማልክት አይሁኑልህ። በላይ በሰማይ ካለው፥ በታችም በምድር ካለው፥ ከምድርም በታች በውኃ ካለው ነገር የማናቸውንም ምሳሌ፥ የተቀረጸውንም ምስል ለአንተ አታድርግ። አትስገድላቸው፥ አታምልካቸውምም፤ በሚጠሉኝ እስከ ሦስተኛና እስከ አራተኛ ትውልድ ድረስ የአባቶችን ኃጢአት በልጆች ላይ የማመጣ፤ ለሚወድዱኝ፥ ትእዛዜንም ለሚጠብቁ እስከ ሺህ ትውልድ ድረስ ምሕረትን የማደርግ እኔ እግዚአብሔር አምላክህ ቀናተኛ አምላክ ነኝና” (ዘፀ. 20፥2-6)። ለመኾኑ እስራኤላውያን ከያህዌ ይህን ሕግ ሲቀበሉ ውስጣዊ የነገረ መለኮት ክርክሩ ምንድር ነበር? እግዚአብሔርን ብቻ ከማምለክና ለእርሱም ብቻ ከመስገድ ውጪ ምን ሌላ ትንታኔና ሐቲት ነበረው?
  ይህ ሕግ የተሰጠው ለመላው ሕዝብ ለእስራኤል፣ ብሉይና አዲስ ኪዳንን ለምናምን ለእኛም ጭምር ነው፤ ለታላቁም ለታናሹም፤ ለአገልጋዩም ለአማኙም። “ከያህዌ በቀር ማንም ማን ሊሰገድለት አይገባም” የሚለው ሃሳብ እግዚአብሔርን በማያውቁ፣ በማያምኑና ለእግዚአብሔር አምላክ ብቻ በሚሰግዱ መካከል እንጂ በክርስቲያኖችና በአማኞች መካከል ልዩነት ኾኖ ፈጽሞ አያውቅም። በግልጥ ቃል አፄው፣ ደራሲው [መንገደ ሰማይ፣ ውዳሴ መስቀልና ሌሎችንም ደርሰዋል ይባላል]፣ አስተርጓሚው [ተአምረ ማርያም፣ ፍትሐ ነገሥትንና ሌሎችንም አስተርጉመዋል ይባላል]፣ ሰይፍና ሥልጣን በእጁ የነበረው ዘርዐ ያዕቆብ ስግደትን ከእስጢፋኖሳውያን መፈለጉና ለሌሎች ፍጡራንም እንዲሰግዱ ማስገደዱ፣ እንቢ ባሉም ጊዜ በተለያየ አሰቃቂ መከራ ውስጥ እንዲያልፉ ማድረጉ ምን ያህል የወንጌል ልብ እንደ ሌለው በትክክል ያሳየናል።
 በቤተ ክርስቲያን ታሪክ፣ በአማኞች መካከል የነበረው ነገረ መለኮታዊ ምልከታዎች ይቅርና፣ በመናፍቃንና በአማኞች መካከል የተደረጉት ክርክሮች [በኒቂያ፣ በቁስጥንጥንያና በኤፌሶን] ሲደረጉ፣ በልበ ሰፊነትና በውይይት መንፈስ እንጂ በሰይፍና በቁጣ አልነበረም። ቤተ ክርስቲያን በጽድቅ ትመላለስ በነበረ ዘመኗ፣ በጽድቅ ከመመላለስና ወንጌልን ከመስበክ፣ ከማወጅ ውጪ አንድም ዘመን ሰይፍን ታጥቃ ተነሥታ አታውቅም፤ ስትስትና ከፈቃደ እግዚአብሔር ፈቀቅ ስትል ግን እንደ ኢ አማንያንና አላውያን ነገሥታት ሰይፍን ይዛ ቆማለች፤ ብዙዎችን አርዳለች፤ ገድላለችም፤ በምሳሌነትም በተደጋጋሚ የተደረገውን የመስቀል ጦረኞችን ጦርነት ማንሳት በቂ ነው። ቤተ ክርስቲያን [“አሕዛብን በመናቋ፣ በመግደሏ፣ በማረዷ … ያውም በአዲስ ኪዳን፤ በዓመተ እግዚእ”] ይህን በማድረጓ ማፈር፤ መሸማቀቅ፣ አንገት መድፋት፣ ንስሐ መግባት እንጂ በፍጹም በዚህ ነገር ልትመካበት፣ ማድረጓንም ትክክል እንደ ኾነ ልትናገር አይገባትም። ክፉ ያደረገ ማናቸውንም ሰው፣ “መንፈሱ በጌታ በኢየሱስ ቀን ትድን ዘንድ እንደዚህ ያለው ለሥጋው ጥፋት ለሰይጣን እንዲሰጥ መፍረድን ትችላለች” እንጂ መግደል አትችልም፤ (1ቆሮ. 5፥5)።
 አይሁድ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ሲከራከሩ ብዙ ጊዜ ግልጥ ነገሮችን ነገረ መለኮታዊ ክርክርና ለእነርሱ ብቻ የተገለጠ ለማስመሰል ታልሙድን ይጠቅሱ ነበር። ጌታችን ኢየሱስ ግን ከቶራህ ከዋናው ሕግ ጠቅሶ ይናገራቸው ነበር እንጂ ሃሳባቸውን ፈጽሞ አይደግፍም። ነገረ መለኮታዊ ክርክር ነውና በጓዲያ እንነጋገር ፈጽሞ አላላቸውም፤ እንዲያውም አምልኮን የሚጻረሩትን ጥቃቅን ነገሮች እንኳ ፊት ለፊት በማንሳት ተጋፈጣቸው። ለምሳሌ፦ የሰንበት አከባበርን (ማቴ. 12፥1-8)፣ የጋብቻ ኹኔታን (ማቴ. 19፥3-12)፣ ስለ ምጽዋት፣ ጸሎት አደራረግ፣ ስለ ጾም አጿጿም (ማቴ. 6፥1-17) እና ሌሎችንም ብናነሣ እነርሱ የታልሙድ ልማዳቸው እንዲነካ አይፈልጉም ነበር፤ ጌታችን ኢየሱስ ግን እንደ ቃሉ ያልኾነውን ኹሉንም ፊት ለፊት ይቃወም፤ እውነቱን ብቻም ይገልጥ ነበር። ዳንኤል አፄው በስመ አክብሩኝ፣ ስገዱልኝ ማለቱን ትክክል ነው ሊለን ይፈልጋል፤ ከዋናው ከእግዚአብሔር ሕግ ከ“ቶራሁ” ይልቅ የአፄው “ታልሙድ” እንዲከበር ይቀናል። እስጢፋኖሳውያን ለአፄው ባለ መስገድ ለሚበልጠው ጌታ ብቻ ታዘዙ፤ ነፍሳቸውንም በመስጠትም ታመኑ። አዎን! ዳንኤል ግን፣ ከጌታችን ኢየሱስ ስላልተማረ ነገረ መለኮታዊ የምትል ስልታዊ ማፈግፈግን እንጂ እንደ እስጢፋኖሳውን ፊት ለፊት መጋፈጥና ለእውነት ዋጋን መክፈል እውነተኛና ትክክል አይመስለውም።
 እምነት እንደ መብረቅ ነው፤ በአደባባይና በሰገነት እንጂ በጓዲያ አይገለጥም፤ “በጨለማ የምትናገሩት ሁሉ በብርሃን ይሰማል፥ በእልፍኝም ውስጥ በጆሮ የምትናገሩት በሰገነት ላይ ይሰበካል” እንዲል (ሉቃ.12፥3)። እውነት ብንነጋገር ቤተ ክርስቲያን በባለፉት ዘመናቷ እንደ ዳንኤል ባሉ ምልከታዎች ተታላ ኖራለች። ነገረ መለኮታዊ ምልከታዎች በሚል ፈሊጥ፣ “የድንግል ማርያም ዐይኖች ሰማያዊ ናቸው ወይስ አይደሉም?፣ በአንድ መርፌ ጫፍ ላይ ስንት መላእክት ይቆማሉ? … በሚሉና በሌሎችም ከንቱ ልፍለፋዎች ተጠምዳ፣ እልፍ አእላፍ የወንጌል መመስከሪያ ጊዜዎችን አቃጥላለች። እስጢፋኖሳውያን “ለእኔም፤ ለፍጡራንም” ስግደት ይገባል ወይም ልትሰግዱልን ይገባል” የሚለውን የአፄ ዘርዓ ያዕቆብ ትምህርት ሳይፈሩ መቃወማቸው፣ ትክክልና የተገባ ነው፤ ምክንያቱም እንዲህ ያለውን ሃሳብ ማፍረስ እንጂ ጥበባዊ በሚል ፈሊጥ እንደ ዳንኤል ክብረት ለድርድር ማቅረብ ፈጽሞ የሚገባ አይደለም፤ “የሰውንም አሳብ በእግዚአብሔርም እውቀት ላይ የሚነሣውን ከፍ ያለውን ነገር ሁሉ እናፈርሳለን ለክርስቶስም ለመታዘዝ አእምሮን ሁሉ እንማርካለን” (2ቆሮ. 10፥5) እንዲል።
  አዎን! ለሰው ትምህርትና ለዓለማዊነት ሥርዓት አለ መገዛት ወዳጅ የሚያበዛ አይደለም፤ ይልቁን እልፍ ጠላትን እንጂ። እውነትን ከያዝን ብዙ ጠላት ምናልባትም አለሙ ኹሉ ጠላት ኾኖ ሊነሣብን ይችላል፤ ይህ ደግሞ በነጳውሎስም ኾኗልና አይደንቅም፤ “እንኪያስ እውነቱን ስለ ነገርኋችሁ ጠላት ሆንሁባችሁን?” (ገላ. 4፥16) ሲል፣ ጠላቶቹ እውነትን በመናገሩ የጠሉት እንደ ኾነ ይናገራል፤ ጌታችን ኢየሱስም፣ “ዓለም ቢጠላችሁ ከእናንተ በፊት እኔን እንደ ጠላኝ እወቁ።” (ዮሐ. 15፥18) በማለቱ፣ ጌታችን ኢየሱስን የሚጠላ የተከታዮቹ ኹሉ ጠላት እንደ ኾነ ነግሮናል። ለዚህም ነው ከሐዋርያቱ አንዱ ቅዱስ ዮሐንስ፣ “ወንድሞች ሆይ፥ ዓለም ቢጠላችሁ አትደነቁ” (1ዮሐ. 3፥13) በማለት የተናገረው። እናም እስጢፋኖሳውያን ሳይደነቁ መከራውን ኹሉ በደስታ የተቀበሉት ወዳጅነታቸውን ከጌታችን ኢየሱስ ጋር ብቻ በማጽናታቸው ነው።
እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ጸጋውን ያብዛልን፤ አሜን


ይቀጥላል …

21 comments:

  1. ሥለ እነሱ ካልተነገረክ ካልተማርክ በራስህ እንዴት ልታውቅ ትችላለህ ወንጌሉን አባቶቻችን ጽፈው ተርጉመው ባያቆዩልን ሲሰብኩት ባይኖሩ ኖሮ ዛሬ ላይ በምን እናውቀው ነበር ወንጌሉንም ገድሉንም መማር ግን ምሉዕ ያደርጋል የወንጌሉን ቃል መፈጸም ከበደኝ እንዳንል ወንጌሉን በህይወት የኖሩትን ቅዱሳን ገድል ተመልከት ይልሃል መጽሐፍ ቅዱስ እነርሱ ሲጋደሉ ጌታ በተዓምራትና በብዙ ድንቅ ሥራው ሲረዳቸው ታያለህ ለእምነትህ ኃይል እንድታገኝ የቅዱሣን ገድላት ይጠቅምሃል እንጂ በምንም ሒሳብ መጋረጃ አይሆንም ለምሳሌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ዘንዶ የሚያመልኩ ልጆቻቸውን ከሚገብሩለት ዘንዶ ጋር ይህ አምላክ አይደለም አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው ብሎ ዘንዶውን ወግቶ ገድሎ ነጻ አወጣቸው ሰብዓ ነገስታትም እኛ በምናመልከው ጣዖት እመን ሥልጣንን እንሰጥሃለን በሚል ሙግት እርሱ የእናንተን በዓል እና ሥልጣን አልፈልግም በሚል ጦርነት ሰባት ግዜ በመንኮራኩር ቢፈጩት የድንግል ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ሰባት ግዜ አስነስቶታል እንግዲህ ገድላት ለእኛ የእምነት ጥንካሬን እና የአምላካችንን ተዓምራት ያጎላሉ እንጂ ወንጌልን አይሸፍኑም በማንኛውም ጻድቅ ገድል ውስጥ ኢየሱስ አምላክነቱ ተስብኳል

    ReplyDelete
  2. ክብር ለሚገባው ሁሉ ክብር ስጡ ይላል ክብር ለሚገባው ለእግዚአብሔር ብቻ አይልም ከሠይጣን እና ክብራቸውን ከጣሉ በስተቀር ሁሉም ክብር ይገባዋል ታናሽ ለታላቅ ክብር መስጠት አለበት
    በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ሰው ለሰውም ለመላዕክትም ሰግዷል ያን ግዜ አምላክ አልነበረም ወይስ ህጉ አይሰራም ነበር ይልቅ ከድንቁርና ውጡ ኦርቶዶክሳውያን ለአምላካችን ክሪያላይሶን ክርስቶስ እያልን እንሰግዳለን ለቅዱሳን በረከታችሁ ትድረሰን አምላክ በሚቀበለው በሚወደው ጸሎታችሁ አማልዱን የተከበሩ ሰዎችን ደግሞ በማክበር ጎንበስ እንላለን ይሔ እንግዲህ አምላካዊ ሥርዓት ነው ኢየሱስ እንዲህ ብሏል እኔና አንተ አንድ እንደሆንን እነርሱም አንድ ይሆኑ ዘንድ የሰጠኸኝን ክብሬን ሁሉ ሰጠኋቸው አለ ለቅዱሳን የክርስቶስ ክብር ተሰጥቷቸዋል እኔ ቅዱስ ነኝና ቅዱሳን ሁኑ ለዚህ ነው ቅዱሳንን የተቀበለ እኔን ተቀበለ እኔን የተቀበለ አባቴን ተቀበለ ያለው እናንተን የማይቀበል እኔን አይቀበልም በፊቱ ያለውን ወንድሙን የማያከብር እኔን ሳያየኝ ሊያከብረኝ አይችልም ይላል ብዙ አወራሁ መናፍቃን ሲጀመር መች ሰግዳችሁ ስታውቁ ነው ሥለስግደት የምትከራከሩት

    ReplyDelete
  3. ዳንኤልን ክብረት እውነተኛ የተዋህዶ ልጅ ነው እንጀ አንተ አይነቱ ጥራዝ ነጠቅ እሱን መተቸት አይችልም ፕሮቴስታንት ስለሆንክ ነው የጠላሀው እመነኝ በአንተ ንግግር ማንም አይታለልም

    ReplyDelete
  4. Shefxenyew daniel weyes tehadiso .

    ReplyDelete
  5. Betekirestiyan ledingil mariya sigdet yegebal sitel ke egzeabher tebelxalech eyalech sayhone yegeta enat bekidisena bedingilina benitsehena yekebersh kefixret hulu kef kef yalshe bemalet yetsega yekeber segdet yegebatal bemalet fixret hulu lekidiste kidusan leweladete amlak yetsega sigdet endiseged tastemeralech ye temehert yemenafrebet sayhone yemenekorabet mehonun tehadiso na telalakiwechchew maweq yexebeqebachewal , yedeqiqe estefanose yetezaba temertn teqebayenet yelewm tarikenem hone yebetkirsteyan astemhero satawqu atzebarqu .

    ReplyDelete
  6. ከእግዚአብሔር ክብርና ከወንጌል እውነት ይልቅ ለራሳቸው
    ዝናና ሆድ ያደሩ እንዲህ አይነት አሳፋሪ አይነደረቅ ተኩላዎችን በዚህ ዘመን ማየት ይገርማል
    ከሁሉም የሚደንቀው ልቡንና ጆሮውን ሰጥቶ የሚያደምጣቸው መኖሩ ነው

    ReplyDelete
  7. ዳኔል እግዛብሔር አይምሮ ውን ይመልስለት

    ReplyDelete
  8. በእውነቱ በቤተክርስቲያኗ መምህራኖች ስለ ደቂቀ አስጢፋኖስ የተፃፈውን በጥቂቱም ቢሆን አንብቤአለሁ እናም ዲ.ዳንኤል ተናገረ ከተባለው ሀሳብ ጋር አይገናኝም(እንደዛ ተናግሮ ከሆነ) እውነቱ አንተ እንደፃፍከው ነው፡፡

    ReplyDelete
  9. ሲጀመር እንኳን መናፍቃን የነበሩት ደቂቀ እስጢፋኖስን ይቅርና ለዳቢሎስ ምሕረትን የጠየቁ ልቡሰ ሥጋ አጋንንትን አስተምረው ያጠመቁ ለከሐዲዎች ምሕረትን ለማሰጠት እራሳቸውን የሚጎዱ ቅዱሳን የታጨቁባት ቤተ ክርስቲያናችን ለቤተ ክርስቲያናችን ታላቅ ሥራ የሰሩትንና እናንተን የመሰሉ መናፍቃንን ከቤተ ክርስቲያናችን ጠራርገው ያስወጡልንን ብዙ አቢያተ ክርስቲያናትን ያሳነጹ የጌታን ግማደ መስቀል አስመጥተው ጊሸን ያስቀመጡ ፤ብዙ መጽሐፍቶችን የጻፉ ያስጻፉ ፤በኢትዮጵያ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ወርቃማው ዘመንና ወርቃማው ነጉሥ እየተባሉ የሚጠሩት አጼ ዘርያዕቆብ በቤተ ክርስቲያናችን የቅድስና ማዕረግ ተሰጥቶዋቸው ታቦት ተቀርጾላቸው ቤተ ክርስቲያን ታንጾላቸው ከሚከብሩ ቅዱሳን ነገሥታት ያልተመደቡትና ቅዱስ የሚለውን ስያሜ ያላገኙት ለምን ይመሳልሐል የስም ዲያቆን?ሲጀመር አንተ ስለእነርሱ አዝነክ ሳይሆን የእነርሱ ምንፍቅና በአጭሩ ስለተቋጨ አንግብግቦክ እንደሆነ እንኳን እኛ አምላካቹ የሱስም ያውቃል ለማንኛውም እኔ እምመክርህ አንተም የእነርሱ እጣ ፈንታ ሳይገጥምሕ በጊዜው ጭንብልሕን አውልቀህ የውሸት ዲያቆን መሆንሕን ትተህ ከቻልክ ፓስተር ከፈለግክ ደግሞ ነብይ ሆነክ ወደ አዳራሽህ በትቀየስ ይሻልሃል በአሁን ሰዓት ሐራጥቃነት ስለተነቃበትና አክሳሪም ስለሆነ ወደሚያዋጣው ሽቀላ ብትሔድ ይሻልሀል

    ReplyDelete
  10. zereyakob be egeziabehear fit kebrewal beserachew enante zarea
    betatelualuachew menem yemetekensubachew neger yelem
    serachew yehew yemesekeral sadek endehonu sadeken yemitelu
    hulu yesesetalu

    ReplyDelete
  11. zereyakob be egeziabehear fit kebrewal beserachew enante zarea
    betatelualuachew menem yemetekensubachew neger yelem
    serachew yehew yemesekeral sadek endehonu sadeken yemitelu
    hulu yesesetalu

    ReplyDelete
  12. ተውት፡፡ እሱ የህርያቆስ ልጅ እንጂ እግዚኣብሔርን አያውቀውም፡፡ በረኛው ብዬዋለሁ፡፡ እራሱ አይገባም፡ ተከታዮቹንም እንዳይገቡ በሩን ይዘጋል፡፡

    ReplyDelete
  13. ዳንኤልን ለመተቸት አቅምም ሞራልም የለህም ምነልባትም አንተ መሰሎችህና በግዋሻው የዳንኤልን እድሜ ያህል ከዚህ በኋላ ብትማሩ በፍጹም ዳንኤልን አትሆኑም ደግሞም አትችሉም ምክንያቱም መመረጥ ያስፈልጋልና ሁሉም ሰው እንዳንተ አይምሰልህ አንተን ብሎ ዲያቆን ጭልጥ ያልክ መናፍቅ ነህ በተጨማሪም ሌባ ሊያውም የነፍስ ሌባ!

    ReplyDelete
  14. ለዛሬ አልተሳካልህም በሚቀጥለው ዙር ይህንኑ በተቃራኒው ፅፈህ አምጣው ከንቱ ድካም ነው እናዝናለን

    ReplyDelete
  15. ይህንን አዳራሽህ ውስጥ ሔደህ እንደለመድከው ክፍት አፍህን ክፈት ዲያቆን ዳንኤል ለሐይማኖቱና ለሐገሩ ከፍተኛ መስዋእትነትን እየከፈለ ያለ ምርጥ አና እንቁ ልጃችን ነው

    ReplyDelete
  16. inante gin lemindinw le deqiqe Isxifanosawuyan indih yeteqoreqorachihu........timirtachew inde ke inante ke Lutherian yileyayal!!!!

    ReplyDelete
  17. እውነት እውነት ሲናገሩት እንዲ ያምራል

    ReplyDelete
  18. ጥሩ ነው ግን አንተንም እንደነርሱ እንዳያድረጉህ ተጠንቀቅ

    ReplyDelete
  19. Its fake orthodox

    ReplyDelete
  20. አሜን ቃለ ሄወት ያሰማልን ጸጋወ ይብዛልህ

    ReplyDelete
  21. ሙድ እየያዘ ነው!!!

    ReplyDelete