Friday 1 June 2018

ደቂቀ እስጢፋኖሳውያንና የ“ዲያቆን” ዳንኤል ክብረት የክፋት ሸፍጥ (ክፍል ፪)

Please read in PDF
   

   በየዘመናቱ ለቤተ ክርስቲያን እንቆረቆራለን፤ ለእርሷ ዘብ ቆመናል፤ ጠበቃዋ ነን … የሚሉ ሰዎች ቤተ ክርስቲያን በመጻሕፍቶቿ ያልሸገገችውን ሕያው የታሪክ እውነትና የጥቁአንን [የተጠቁትን] የወንጌል ምስክርነት፣ እውነተኛ ሕይወታቸውንም ሊሸፋፍኑ፤ ሊያድበሰብሱ፤ የክፋት ልባቸውን ያለ መከልከል ገልጠው ሲያሳዩና አኹንም ሲያደርጉት ዕያየን ነው። ዳንኤል ክብረት፣ እስጢፋኖሳውያንን “መናፍቅ” ናቸው ለማለት የሚተጋውን ያህል፣ የተፈጸመባቸው ሰቆቃና መከራ ቅንጣት ታህል እንደ ማይሰቀጥጠው ንግግሮቹ ያሳብቃሉ። ለነገሩ መሞት፣ መዋረድ፣ ክፉን በክፉ አለማሸነፍ፣ መነቀፍ ሳይኾን መግደል፣ መሳደብ፣ መደብደብ … እንደ ሃይማኖትና መንግሥተ ሰማያት እንደ ሚያስወርስ “ምግባር ወይም ጽድቅ” በሚቆጠርበት የበዛ ማኅበረሰብ ባለበት፣ ዳንኤል ተቃራኒውን ቢያስብ ወይም ቢያስተምር እንጂ የደረሰባቸው ግፍ ባይገደው ምንም የሚያስደንቅ ነገር አይደለም።

ደቂቀ እስጢፋኖስ ግድያ ከመጽሐፍ ቅዱስ አስተምኅሮ አንጻር እንዴት ይታያል?
    ይህን ርዕስ ማንሳት ቀላልና ምንም የማያደክም ሊኾን ይችላል፤ ምክንያቱም መግደል ግልጽ ኀጢአት ነውና፤ ነገር ግን ሰዎች መግደልን “ቅዱስና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ፍቅድ ሥልጣን እንዳለው” ለማድረግ የማይተረት ተረት፤ የማይደረት ድሪት የለም። “መጻሕፍትንና የእግዚአብሔርን ኃይል አታውቁምና ትስታላችሁ” (ማቴ. 22፥29) እንዲል፣ ከእግዚአብሔር ቃል ውጭ በመውጣት የምንወድቀውና የምንስተው እግዚአብሔር የተናገረንን በትክክል ሳናውቅ ስንቀር ነው። ሰውን መግደል ስህተት፣ ኀጢአት፣ ዓመጽ እንደ ኾነ እናውቃለን፤ ለሃይማኖታችን ክብር ወይም የሚቃወመንን ስንገድል እንኳን ሰው፣ እግዚአብሔር ራሱ እንዲቃወመንና ተዉ እንዲለን አንፈልግም፤ ለሃይማኖታችን በምናደርገው ማናቸውም ነገር እግዚአብሔር ራሱ የእኛ ሎሌ [የሃሳባችንና የድርጊታችን ተካፋይ] እንዲኾን እንፈልጋለን።

   በክርስትና ትምህርት እንመራለን ካልን፣ ሊመራንና ሊዳኘን የሚችለው ቅዱስ መጽሐፍ፤ መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ነው። ሃሳባችን፣ ንግግራችን፣ ድርጊታችን፣ የሥራችን ኹለንተና ሊዳኝ የሚገባው፤ ትክክል አይደለም ወይም ነው ተብሎ ሊመዘን፣ ሊጸድቅና ሊኰነን የሚቻለው በመጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ነው። በሰው ፊትና ሃሳብ እጅግ መልካም የኾነው ነገር በእግዚአብሔር ፊት አጸያፊና አስነዋሪ ነገር ሊኾን ይችላል፤ እጅግ ብዙ ጊዜ ነውም። በእርግጥም፣ ያለ እግዚአብሔር ሰዎች እግዚአብሔር አምላክን ሊያስደስቱ የጣሩበት ኹሉም ዘመን እጅግ አስቀያሚና ርኩሰት የተመላበት ነበር። ሁል ጊዜም የሰው መልካምነት ፍጻሜው መራራና ሞት ነው፤ “ለሰው ቅን የምትመስል መንገድ አለች፤ ፍጻሜዋ ግን የሞት መንገድ ነው።” (ምሳ. 5፥5፤ 14፥12፤ 16፥25)።
     መጽሐፍ ቅዱስ “ስለ ሰው ግድያ ምን ይላል?” የሚለውን ከማየታችን በፊት፣ “መጽሐፍ ቅዱስ ሰውን ምን ያህል አክብሮታል?” የሚለውን ማየትና ማስተዋል እጅግ ጠቃሚና ወደ እግዚአብሔር የሚያቀርብ፣ በሰው ላይ አንዳች ክፋት ከማድረግ የሚጠብቅም ነው። አስተውሉ! ሰው ስንል ኀጥኡንም ጻድቁንም፣ የተማረውን ያልተማረውንም፣ ጤናማውንም በሽተኛውንም ወይም ከፍ ካለ ያበደውንም፣ የተወለደውንም ገና ያልተወለደ በማኅፀን ያለውንም፣ ኦርቶዶክሱንም እስላሙንም፣ ካቶሊኩንም ፕሮቴስታንቱንም፣ ቡሂዱንም ይሁዲውንም፣ ጥቁሩንም ነጩንም፣ ኢትዮጵያዊውንም ኤርትራዊውንም፣ አማኙንም መናፍቁንም … ማለታችን ነው። በዶግማና በቀኖና መለያየት ሌላ ጉዳይ ነው፤ ሰውን መግደል ደግሞ እጅግ እጅግ ሌላ ጉዳይ ነው። እኔ ኦርቶዶክሳዊ ነኝ፤ ነገር ግን አንድን ፕሮቴስታንት ወይም ካቶሊክ ወይም ሙስሊም ወይም ሻንቶ ወይም ሂንዱ … ከእኔ ጋር በዶግማና በቀኖና አንድ ስላልኾነ የመግደል ምንም መብት የለኝም፤ የለኝም ብቻ አይደለም ሲገደሉ በዐይኖቼ ባይ ዝም ማለት አልችልም፤ ምክንያቱም የእግዚአብሔር መልክ በኹሉም አለና።
   እግዚአብሔር ሰውን “በመልኩ እንደ ምሳሌው” ፈጥሮታል (ዘፍጥ. 1፥26)፤ ሰው እንደ እንሰሳት በየወገኑ ሳይኾን ወንድና ሴት ተደርጐ በእኩልነት በመፈጠሩ፣ ከሌሎች ፍጥረታት በላይ ክብርና ሞገስ አለው (ዘፍጥ. 1፥25፤ 17)፤ እግዚአብሔር ሕዋን የሚያህል ግዙፍ ዓለምና ይህንንም ምድር የፈጠረው፣ ስለ ሰውና ሰውም ለእግዚአብሔር ክብርና አምልኮን እንዲያመጣ በማድረግ ነው። ሰው እጅግ ክቡር ፍጡር ነውና የእግዚአብሔር ዓይኖች ዘወትር በእርሱ ላይ ናቸው። ስለዚህም እግዚአብሔር  በመልኩ እንደ ምሳሌው አክብሮና እጅግ አልቆ፣ አግንኖ፣ እጅግ መልካም የፍጥረት አክሊልና ዘውድ አድርጐ፣ በመልካምና በቅዱስ ፈቃዱ ፈጥሮታል (ዘፍጥ. 1፥31)፤ ስለዚህም ሰውን፦
V  ንቆጣው አንችልም፦ ቁጣ ወደ ነፍሰ ገዳይነት የሚያንደረድር የዓመጽ መሣርያ ነው። የያዕቆብ ልጆች ስምኦንና ሌዊ፣ ሴኬም እህታቸውን ስለደፈረ ሴኬምና መላ ቤተሰቡ እንዲገረዙ ካደረጉ በኋላ፣ በቁጣቸው ተነሣስተው በሰይፍ አረዷቸው። አስተውሉ! የይሁዲነት እምነት እንዲቀበሉና የኦሪትን ሕግ እንዲጠብቁ በሚል አስባብ አስገርዘው፣ የግርዘቱ ቁስል በጸናባቸውና ራሳቸውን መከላከል በማይችሉበት ሰዓት ላይ ገብተው በሰይፍ አረዷቸው፤ (ዘፍጥ. 34፥25-27)፤ ይህን ድርጊት ያዕቆብ ፈጽሞ በመጠየፍ እንዲህ አለ፦ “ስምዖንና ሌዊ ወንድማማች ናቸው፤ ሰይፎቻቸው የዓመፃ መሣሪያ ናቸው። በምክራቸው፥ ነፍሴ፥ አትግባ፤ ከጉባኤአቸውም ጋር፥ ክብሬ፥ አትተባበር፤ በቍጣቸው ሰውን ገድለዋልና፥ በገዛ ፈቃዳቸውም በሬን አስነክሰዋልና። ቍጣቸው ርጉም ይሁን፥ ጽኑ ነበርና፤ ኵርፍታቸውም፥ ብርቱ ነበርና፤ በያዕቆብ እከፋፍላቸዋለሁ፥ በእስራኤልም እበታትናቸዋለሁ፤ (ዘፍጥ. 49፥5-7)።
   የኹለቱ የያዕቆብ ልጆች ቁጣ፣ ብስጭት፣ ንዴት አንድ ዓይነት ነው፤ አንድ አይነት ብቻ ሳይኾን በአባታቸው ፊት እጅግ አጸያፊና ክፉ ነበር፤ በእግዚአብሔር ፊት ደግሞ እንዴት የተጠላ ይኾን? እግዚአብሔር በብሉይ ኪዳን እንኳ አስገድዶ ደፋሪው አሕዛቡ ሴኬምና ቤተሰቡ እንዲገደሉ ፈጽሞ ፈቃዱ አልነበረም፤ ይህንም ምንም ታላላቆች ቢኾኑም ከብኵርናቸው በመሰረዝ ወይም ብኩርናቸውን በመንሣት ድርጊታቸው ጸያፍ መኾኑን አሳይቷል፤ (2ዜና 5፥1)።
  ቁጣ ብኩርናን ብቻ የሚያስተው፣ የሚያስጥል አይደለም፤ ጌታችን ኢየሱስ ባስተማረው ትምህርቱም፦ “ለቀደሙት፦ አትግደል እንደ ተባለ ሰምታችኋል፤ የገደለም ሁሉ ፍርድ ይገባዋል። እኔ ግን እላችኋለሁ፥ በወንድሙ ላይ የሚቆጣ ሁሉ ፍርድ ይገባዋል፤ ወንድሙንም ጨርቃም የሚለው ሁሉ የሸንጎ ፍርድ ይገባዋል፤ ደንቆሮ የሚለውም ሁሉ የገሃነመ እሳት ፍርድ ይገባዋል።” (ማቴ. 5፥21-22) በማለት፣ ወንድምን መቈጣት እንደ ማይገባ ይነግረናል። ቁጣ የሰውን ሥጋና ነፍስ በመለያየት ገዳይ ብቻ አይደለም፤ ሰውን በቁሙ የሚገድልም ነው እንጂ፤ አይሁድ ይህን ስተው ነበር፤ ጌታችን ኢየሱስ ግን ይህን ታላቅ እውነት ከመሠረቱ ሊያብራራውና እውነቱን ሊነግራቸው ፈለገ። አትቆጡ በማለት!
    ሰውን ለመግደል ወይም በኀጢአት ማናቸውንም ሰው መቆጣት በደልና ዓመጽ ነው፤ ቃየል አቤልን ከመግደሉ በፊት የነበረውን ኹኔታ፣ “በሜዳም ሳሉ ቃየን በወንድሙ በአቤል ላይ ተነሣበት፥ ገደለውም።” (ዘፍጥ. 4፥8) በማለት ይናገራል። “ተነሣበት” ሲል የቁጣውን ብርታት የሚገልጥ ነው። በቁጣ መጽናት ለዲያብሎስ ፈንታ መስጠትና ለሌላ ኃጢአት ራስን ማዘጋጀት ነው፤ (ኤፌ. 4፥27)። ኹል ጊዜ ባይኾንም፣ አንዳንድ ቁጣዎች ሰዎችን ወደ ኀጢአት ይመራሉ፤ ብዙ ጊዜ ምንጩም የእኛ ክፉ ምኞት ነው፤ ዲያብሎስ ፈንታ የሚያገኘው ከእኛ ክፉ ምኞት መነሾነት ነው፤ ቁጣችን በሌሎች ላይ በጥላቻና በቅንአት እስክንነሣሣ ድረስ መዝለቅ [መቈየት] የለበትም፤ ስለዚህም በምንም መልኩ በቁጣ ኀጢአት ልንያዝ አይገባንም። ደግሞ፣ “የሰው ቍጣ የእግዚአብሔርን ጽድቅ አይሠራምና፤” (ያዕ. 1፥20) ቁጣን በብዙ ልንሸሸው ይገባናል።
V  ጠላ አይገባውም፦ “ሰውም [ሰውን] ... እስኪሞት ድረስ በጥላቻ ቢደፋው፥ ወይም ሸምቆ አንዳች ነገር ቢጥልበት፥ ወይም በጥላቻ እስኪሞት ድረስ በእጁ ቢመታው፥ የመታው ፈጽሞ ይገደል፤ ነፍሰ ገዳይ ነው፤” (ዘኍል. 35፥19-21)።
  ንቀት ሰዎችን በሰውነታቸው ብቻ ካለ መመልከት የሚመጣ ነው፤ ሰዎች ሰዎችን ከመጥላታቸው በፊት ይንቃሉ፤ ንቀት ወደ ጥላቻና ወደ ስድብ ያድጋል። “ኀጥእ በመጣ ጊዜ ንቀት ደግሞ ይመጣል፥ ነውርም ከስድብ ጋር” (ምሳ.18፥3) ሰውን የሚንቅ እርሱ ደግሞ የእግዚአብሔርን መልክ ንቋልና በእግዚአብሔር የተናቀ ነው።
  ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ሥጋዌው ካስተማረው ትልቁ ትምህርት አንዱ፣ “ባልንጀራህን ውደድ ጠላትህንም ጥላ እንደ ተባለ ሰምታችኋል። እኔ ግን እላችኋለሁ፥ በሰማያት ላለ አባታችሁ ልጆች ትሆኑ ዘንድ ጠላቶቻችሁን ውደዱ፥ የሚረግሙአችሁንም መርቁ፥ ለሚጠሉአችሁም መልካም አድርጉ፥ ስለሚያሳድዱአችሁም ጸልዩ፤ እርሱ በክፎዎችና በበጎዎች ላይ ፀሐይን ያወጣልና፥ በጻድቃንና በኃጢአተኞችም ላይ ዝናቡን ያዘንባልና” (ማቴ. 5፥43-44) የሚል ነው።
  ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሕዝብም ለአሕዛብም ታማኝ እረኛ ነው፡፡“… መልካም እረኛ እኔ ነኝ” (ዮሐ.10፥11) ያለው ጌታ፥ ሲጠራን የጠራን ለፍቅር ነው፤ ለፍቅር እንጂ ለጥላቻና ሰውን ፊታችንን በማጥቆር ለመመልከት አይደለም። እግዚአብሔር እንድንደርስበት የፈለገው ልኬትና እንድንኾን የፈለገው የእግዚአብሔር ልጆች ነው፤ ይህን ለመኾን የእርሱ ባሕርይ በእኛ መታየት አለበት። ሰውን የሚጠላ በእርሱ ላይ ያለውን የእግዚአብሔርን መልክና ዓላማ ፈጽሞ ይጠላል ማለት ነው፤ ይህ ደግሞ ጠባችን በቀጥታ ከምንጠላው ሰው ጋር ሳይኾን፣ ኹሉን ከሚችለው ኤልሻዳይ ያህዌ ጋር ነው። ከእርሱ ጋር የሚጣሉ ኹሉ ደግሞ ይጠፋሉ፤ ይደባያሉ። “አይበጃችሁምና ከአባቶቻችሁ አምላክ ከእግዚአብሔር ጋር አትዋጉ።” (2ዜና 13፥12) ምክንያቱም፣ “ከእግዚአብሔር ጋር የሚጣሉ ይደቅቃሉ፤ በሰማይም ያንጐደጕድባቸዋል፤ እግዚአብሔር እስከ ምድር ዳርቻ ይፈርዳል፤” (1ሳሙ.2፥10) ተብሏልና።
  እርሱ የፍጥረት ሁሉ አባት ነው። እግዚአብሔር ማንንም ከማንም አስበልጦ አያይም፤ አያይም ብቻ አይደለም እንዲህ ያለ ሃሳብ በእርሱ ዘንድ ከቶ የለም። የምድር ሁሉ ጌታና የምድርም ነገሥታት ሁሉ አምላክ የሆነው እግዚአብሔር (ኢያ.3፥11 ፤ 1ነገ.19፥15) እርሱ ፍጥረቱን በልዩነት ዐይን አያየንም። ለእግዚአብሔር ዓይኖች ምድር ሁሉ አንድ ናትና።
V  ረገም አይገባውም፦ በእግዚአብሔር መልክ ስለ ተፈጠረ ሊረገም ፈጽሞ አይገባም። “አንደበትን ሊገራ ማንም ሰው አይችልም፤ የሚገድል መርዝ የሞላበት ወላዋይ ክፋት ነው። በእርሱ ጌታንና አብን እንባርካለን፤ በእርሱም እንደ እግዚአብሔር ምሳሌ የተፈጠሩትን ሰዎች እንረግማለን፤ ከአንድ አፍ በረከትና መርገም ይወጣሉ። ወንድሞቼ ሆይ፥ ይህ እንዲህ ሊሆን አይገባም። (ያዕ. 3፥8-10)።
  የእግዚአብሔር አምላክና መልክና አምሳል አለበትና ሰውን መራገም፣ ራሱ እግዚአብሔርን የመራገም ያህል ነው። እግዚአብሔር አምላክን የሚራገም ማንም ደግሞ ከሕይወትና ከበረከት ኹሉ የወጣና ፈጽሞ የተለየም ነው። እግዚአብሔርን ብቻ ሳይኾን የእግዚአብሔር የኾኑትን የሚራገሙ ኹሉ ርጉማን ናቸው፤ (ዘፍጥ. 12፥3)።
  ከምንም በላይ ደግሞ በልጁ ሞት የተጠራን አማኝ ክርስቲያኖች፥ የእርሱን እረኝነት የምናምነው ያለ ስስት ለበጐቹ እኩል ነፍሱን በመስጠቱ ነው። ለጳጳስም፣ ለቄስም፣ ለፓትርያርክም፣ ለድኃውም፣ ለሃብታሙም፣ ለጤነኛውም ለእብዱም፣ ፊደል ለቆጠረውም ላልቆጠረውም … እኩል ስለ መዳናችን የፈሰሰው የክርስቶስ ደም አንድ ነው። በክርስቶስ ለምናምን እግዚአብሔር አንዱን ሰው ከሌላው አስበልጦ እንደ ሚያይ ማሰብ እጅግ አስነዋሪ ነገር፤ ርኩሰትም ነው።
   ሰው ላይ የሚኾነውም ነገር ሊቆጠቁጠን፣ ሊያገባን፣ ሊገደን፣ ሊያሳዝነን፣ ሊሰብረን፣ ሊያስለቅሰን… ይገባል፣ እንጂ ግድ ለማዘን ሰው የእኛ ሃይማኖት ተከታይ፣ አማኛችን፣ የእኛ ዘርና ጐሳ፣ ኢትዮጵያዊና የወንዛችን ልጅ መኾኑን እየመረመርን ወይም እየመረጥን ማዘን ግብዝነትና ከሰውነት የማነስ ምልክት ነው።
V  ገደል አይገባውም፦ “የሰውን ደም የሚያፈስስ ሁሉ ደሙ ይፈስሳል፤ ሰውን በእግዚአብሔር መልክ ፈጥሮታልና” (ዘፍጥ. 9፥6)። እግዚአብሔር የመጀመርያውን ነፍሰ ገዳይ ማንም እንዳይጐዳው፤ “እግዚአብሔርም ቃየንን ያገኘው ሁሉ እንዳይገድለው ምልክት አደረገለት” እንዲል (ዘፍጥ. 4፥15)፣ እግዚአብሔር አምላክ በግልጽ ኃጢአትን የሠራ ሰው እንኳ፣ ሰው የመግደል አንዳች ሥልጣን እንደ ሌለው አሳይቷል። በአዲስ ኪዳንም “ማንም የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ቢያፈርስ እግዚአብሔር እርሱን ያፈርሰዋል፤ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ቅዱስ ነውና፥ ያውም እናንተ ናችሁ” (1ቆሮ. 3፥17) ሲል፣ ያው እግዚአብሔር አኹንም ቅዱስ ከሃሳብ ያልተለወጠ መኾኑን ያሳየናል።
   ሰው ሰውን ሲገድል ሕግ ተላላፊ ብቻ አይደለም፤ እግዚአብሔርንም የሚንቅ ጭምር ነው እንጂ። ለዚህም ነው ጌታ እግዚአብሔር የሰውን ደም የሚያፈስሱ የእነርሱንም ደም ሰዎች እንደ ሚያፈስሱ የተናገረው። ይህ ነገር በምድር እንዳይኾን ጌታ እግዚአብሔር በጽኑ ተናገረ፤ (ዘፀ. 21፥12-14፤ ዘኍ. 35፥16-35፤ ሮሜ. 13፥3-4፤ 1ጴጥ. 2፥13-14)። እንኳን በጥላቻና አቅደን ሰውን ልንገድል፣ በቸልተኝነት እንኳ እንዳናደርገው ብርቱ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶናል።
   እግዚአብሔር አምላክ ከሰው ውድቀት በኋላ እንኳ ሰው ላይ የነበረውን መልኩና አምሳሉን አላነሣውም። ያ እግዚአብሔራዊ መልክ ተበላሸ፤ አደፈ፤ ቆሸሸ፤ ረከሰ እንጂ ፈጽሞ አልጠፋም። በዘላለም ዕቅዱ እግዚአብሔር ሊመልሰው፣ ሊቀድሰው፣ ሊያነጻው እስካሰበበት ድረስና ከዚያም በኋላ ባለው ጊዜ እንኳ ይህ ሰው የረከሰ ቢኾንም በሰው እጅግ እንዲሞት፣ እንዲገደል፣ እንዲንገላታ ፈጽሞ ፈቃዱ አልነበረም፤ አይደለምም።
ድያ የእስጢፋኖሳውያን መገደል እንዴት “መንፈሳዊ” ኾነ ተብሎ ሊነገረን በቃ?
  ይህን ጥያቄ ስናነሣ አንዳንዶች በግብዝነት “መናፍቅን ማረድና መግደል ኀጢአት አይደለም” የሚል አጋንንታዊ የደም ጥማት መልስን ይመልሳሉ። በማንኛውም መልኩ ግን ሰውን መግደል አይደለም መጥላትና መቈጣት እንደ ማይገባን ቅዱሳት መጻሕፍት ያስተምሩናል። የቤተ ክርስቲያኒቱ ፍትሐ ነገሥት እንኳን እውነተኞቹን አማኞች ይቅርና የተወገዘ መናፍቅን እንኳ እንድንራራለት፣ እንድንማልድለት እስኪመለስም ድረስ እንድንተጋለት እንጂ እንድንገድለው አይነግረንም፦
  “ኃጢአተኛውን ብታገኘው ጥቂት በጥቂት ምከረው ፈጥነህ አትለየው ዲያቆናትም በውጪ አጊኝተው አባብለው እንዲመልሱት ስለ እርሱም እንዲጸልዩ እዘዛቸው ያን ጊዜም በችሎታው መጠን ጾም ሥራለትአንድና ሁለት ሱባኤ ቢሆን ወይም ሦስት ወይም ፬ ወይም ፭ ወይም ፮ ሱባኤ ሥራለትኃጢአቱን ለማሥተሠረይ በሚገባ እንዲገስጽ አስተምረው፤ አክብረው በራሱ ትሑት የዋሕ እንዲሆን አስተምረው[1]

   “ኤጲስ ቆጶስ ሆይ የበደለውን አውግዘህ ብትለየው በውጭ አትተወው፤ ወደ ቤተ ክርስቲያን መልሰው እንጂ። የጠፋውንም ፈልግ። ስለኃጢአቱ ብዛት እድናለሁ ብሎ ተስፋ የማያደርገውን በሁሉ ጠፍቶ ይቀር ዘንድ አትተወው። እንዲህም ኤጲስ ቆጶስ የኃጥኡን ኃጢአት ሊሸከም ይገባዋል። እርሱም ፈጽሞ እንደበደለ ያድርግለት። የበደለውንም “አንተ ተመለስ እኔም ስለ እኔና ስለሁሉ በሞተው በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አምሳል ስለአንተ ሞትን እቀበላለሁ ይበለው።” [2]
  ቤተ ክርስቲያን በፍትሐ ነገሥቷ እንዲህ ብትልም፣ በዳንኤል አንደበትና በተአምረ ማርያም መጽሐፏ ግን የደቂቀ እስጢፋኖስን መገደል ግን ትክክልና እውነት እንደ ኾነ ትነግረናለች። ደቂቀ እስጢፋኖሳውያን የደረሰባቸው እልቂት ጆሮን ጭው የሚያደርግ ነው፤ ቤተ ክርስቲያን እንኳ በመጻሕፍቶቿ እንዳመነችው አፍንጫቸው ተፎንኗል፣ ምላሳቸው ተቆርጧል፣ በድንጋይ ተወግረው ሞተዋል፤ ገዳዩንም ተአምረ ማርያም “ንጉሣችን ዘርዓ ያዕቆብ” በማለት አንቆለጳጵሶና አሞካሽቶ ጠርቶታል። ከዚህ ባለፈ ደቂቀ እስጢፋኖሳውያን ላይ የጅማት ትልተላ፣ ለክርስቲያን ጠላት ለኾኑ አካላት በባርነት ተሸጠዋል፣ እጅግ በረዶአማና ቀዝቃዛ ስፍራ ላይ ለቀናት ታስረዋል፣ ሴቶች በብልቶቻቸው የጋለ ብረትና ፍህም ተጨምሮባቸዋል፣ በአንገቶቻቸው ገመድ ተደርጐ ተጐትተዋል፤ ለንባብና ለጆሮ የሚሰቀጥጥ፣ ሊታሰብ እንኳ የማይደፈር እጅግ አስጨናቂ ነገር ተፈጽሞባቸዋል።
   እንግዲያው ይህ ለኀጢአተኛና ለተወገዘ ሰው የተሰጠ ዕድል፣ ምነው በእስጢፋኖሳውያን ላይ ልምሾ ኾኖ አልሠራ አለ? ቤተ ክርስቲያን በገዛ ልጆቿ ላይ “ንጉሣችን ከምትለው ሰው ጋር” ለመግደልና ደም ለማፍሰስ ስለ ምን ተባበረች? ዛሬም ድረስ ይህ አሳፋሪ የጅምላ ጭፍጨፋ ታሪክ በመጻሕፍቶቿ ሲተረኩና ሲነበቡ ለምን ጆሮ ዳባ ልበስ ከመባል አልፎ የሚድያ ግብአት ኾኖ እንዲቀርብ ተፈቀደ? በውኑ ይህን ያህል ድንዛዜና አዚም ከወዴት መጣ?
   ዳንኤል ከተፈጸመው አስነዋሪ ነገር ይልቅ ድርጊቱ የተፈጸመበትን ሥረ ምክንያት ማልፈስፈስና ማድበስበስ ይፈልጋል፤ እንኳን በመንፈሳዊ፣ ከእግዚአብሔር ውጪ ለማንም ስግደትና አምልኮ አይገባም በሚባል ታላቅ መንፈሳዊ አቋም ይቅርና በምንስ ምክንያት ቢኾን፣ የሰው ስቃይና መከራ ምነው አልሰቀጥጥ አለው? ንጉሡ እንዲህ ለማድረግ ምክንያት አላቸው ቢባል እንኳ፣ ቤተ ክርስቲያን ግን ማን ፈቀደላት? ከማንስ ተማረችው? በእውኑ በክርስቶስ ወንጌል፣ በቅዱሳን ሐዋርያት አስተምኅሮ፣ በጥንት አባቶች ትምህርት፣ በትውፊትስ እንዲህ አስነዋሪና ጆሮ ጭው አድራጊ ተግባርን የሚደግፍ ምን አይነት ትምህርትና መንገድ አለ? 
  እንደ አንድ ኦርቶክሳዊ አማኝ ሳስበው በዚህ ጉዳይ አፍሬ እሸማቀቃለሁ እንጂ ሰው ማረድ፣ ሰውን በድንጋይ መውገር፣ የሰውን ምላስ መቁረጥ፣ የሰው አፍንጫ መፎነን፣ በሴት ልጅ ብልት የጋለ ብረትና ፍህም መጨመር፣ ጅማት መተልተል … እንኳን ላወራው፣ ልከራከርለት፣ ሳስበው እንኳ ራሴን እጠላለሁ፤ እጠየፈዋለኹ፤ አሳፋሪ ታሪክ ነውና አንገቴን ደፋለሁ። ለኀጢአተኞች፣ ለደካሞች፣ ለክፉዎችና ለጠላቶቹ … ሊሞት የመጣውን አምላክ በትክክል የማመልክ ከኾንኩኝ፣ በሰው መጠቃትና መንገላታት ፈጽሞ አልደሰትም፤ ይህም እንዲሸፋፈን፣ እንዲልኮሰኮስም ፈጽሞ አልሠራም። ሰው ከቅዱስ ወንጌል መንፈሳዊነት፣ ከሥነ ምግባርና ከሞራል ከወረደ ግን የወንዙና የጐሳው ሰው እንጂ የሌላው ሰው ሞት፣ ሞት ላይመስለው ይችላል።
   ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ሆይ! በእስጢፋኖሳውያን ጉዳይ ንስሐ መግባት እንደ ሚገባሽ አታስቢምን? ለአምላክሽ የምትሞቺ ኾነሽ ተጠራሽ እንጂ ትገድይ፣ ትቆርጪ፣ ትፎንኚ፣ ትተለትይ … ዘንድ ማን ሾመሽ? ዳንኤልና ባልንጀሮቹ ለጽድቅ ኖረው ሳይሞቱ፣ ገዳዮችን ቢያወድሱ፣ ነፍስ በላዎችን ቢያመሰግኑ ምን ይደንቅ ይኾን? ጌታ መንፈስ ቅዱስ ምድሪቱን በንስሐ እንድትመለስ በምሕረት ያስባት፤ አሜን።
ይቀጥላል …






[1] ፍትሐ ነገስት አን.5 ቁ.125
[2] ፍትሐ ነገስት አን.5 ቁ.122

23 comments:

  1. አቤኒ ጌታ ይባርክህ እነ ዳንኤል ለውሸት ቢቆሙም አንተ ለእውነት ቆመሀል እስጢፋኖስና ተከታዮቹ ሁሌም በልባችን ውስጥ አሉ ውሸታሟ ቤተ ክrstiያን ሳትሆን እውነተኛዋ የክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን ሁሌም ትዘክራቸዋለች

    ReplyDelete
  2. ሥለ እነሱ ካልተነገረክ ካልተማርክ በራስህ እንዴት ልታውቅ ትችላለህ ወንጌሉን አባቶቻችን ጽፈው ተርጉመው ባያቆዩልን ሲሰብኩት ባይኖሩ ኖሮ ዛሬ ላይ በምን እናውቀው ነበር ወንጌሉንም ገድሉንም መማር ግን ምሉዕ ያደርጋል የወንጌሉን ቃል መፈጸም ከበደኝ እንዳንል ወንጌሉን በህይወት የኖሩትን ቅዱሳን ገድል ተመልከት ይልሃል መጽሐፍ ቅዱስ እነርሱ ሲጋደሉ ጌታ በተዓምራትና በብዙ ድንቅ ሥራው ሲረዳቸው ታያለህ ለእምነትህ ኃይል እንድታገኝ የቅዱሣን ገድላት ይጠቅምሃል እንጂ በምንም ሒሳብ መጋረጃ አይሆንም ለምሳሌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ዘንዶ የሚያመልኩ ልጆቻቸውን ከሚገብሩለት ዘንዶ ጋር ይህ አምላክ አይደለም አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው ብሎ ዘንዶውን ወግቶ ገድሎ ነጻ አወጣቸው ሰብዓ ነገስታትም እኛ በምናመልከው ጣዖት እመን ሥልጣንን እንሰጥሃለን በሚል ሙግት እርሱ የእናንተን በዓል እና ሥልጣን አልፈልግም በሚል ጦርነት ሰባት ግዜ በመንኮራኩር ቢፈጩት የድንግል ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ሰባት ግዜ አስነስቶታል እንግዲህ ገድላት ለእኛ የእምነት ጥንካሬን እና የአምላካችንን ተዓምራት ያጎላሉ እንጂ ወንጌልን አይሸፍኑም በማንኛውም ጻድቅ ገድል ውስጥ ኢየሱስ አምላክነቱ ተስብኳል

    ReplyDelete
  3. አረ ተዉ ኘሮግራሞን ያየን ስለሆነ ታዘብኩህ ለዳንኤል ያለህን ጥላቻ ያላለውን አትበል እኔ ለእርሱ ጥብቅና ልቆምለት ሳይሆን የአባ እስጢፋኖስን መከራ መቀበል አልካደም ተናግሮታል የአባ እስጢፋኖስ ወይንም የአፄው ግጭታቸዉን እርሱ ብቻ ሳይሆን ብዙ የታሪክ ባለሞያዎቹ ገልጸዉታል።

    ReplyDelete
  4. በጣም ነው ሚገርመው ሁሌ አቤል እየሞት ቃይል እየገደለ መኖር ጽድቅ የሚቆጠርበት ዘመን አሁንም ቃይኖች ብክፋት እየገደሉ አቤሎች ደግሞ ንጹህ መስዋእት እያቀረብን እንኖራለን። ቃይይል ና የቃይል ልጆች። እነ ዳኒኤል ና መሰለቹ እንደ አባታቸው ቃይል ተቅበዝብዘይ ይኖራሉ

    ReplyDelete
  5. ሌባ በጓሮ በር ለምን ትገባለህ በፊት ለፊት ና! ደቂቀ እስጢፋ እንኳንም ጠፋ!

    ReplyDelete
  6. አቤል እየሞት ቃይል እየገደለ

    ReplyDelete
  7. ወንድሜ እግዚአብሔር ይስጥልኝ ስለ ምስክርነጥ ምክንያቱ ሰው የገደለ በሚከበርበት ሃገር አስኪ ምከርልኝ ። ከክርስቶስ ቃል ይልቅ በስጋዊ ስሜት የሚመራ ትውልድ ከመጽሐፍ ቃል ይልቅ አሉባልታን ቁም ነገር ብሎ ጆሮን የሚሰጥ ትውልድ ነው። ክርስቶስማ << ሰማዕክሙ ዘተብህለ ለቀደምትክሙ ኢትቅትል ነፍሰ አንሰ እብለክሙ ወዘሰ አምዕዖ እኁኁ በከንቱ ይትኴነን ማቴ ፭፥ ፪፪ ለቅደምቶቻቹ ነፍስ አትግደል የሚል ሰምታቹ ይሆናል እኔ ግን ወንድሙን በከንቱ የትቆጣ ቢኖር ይፈረድበታል ይላል ሕዝቤ ግን ይህንን ወደ ጎን ተወት እያደረገች በ አሮጊቶች ተረት ታስራ ተይዛለች እውነታው ግን ሌላ ነው። በረከታቸው ይድረስብንና ሶስት ሞቶ ሊቃዉንት አባቶቻችን ኩፉውን መናፍቅ አርዮስን ( ወልድ ፍጡር በመለኮቱ) ያለዉን ሲረቱት ኮ ምኑን አልነኩትም ምክንያቱ ቅዱሳን ስለሆኑ ንጉሱ ቆስጠንጢኖስም ከ አባቶቹ ትእዛዝ አልወጣም ይመለሳል ብለው ለቀቁት እንጂ ምላሱን አልቆረጡትም። የ ዚህ ንጉስ ተብየ ሃይማኖተኛ ግን በጣም ያማል ደግሞ ቅዱስ ለማለት ይደፍራሉ አረ ምን ቀረ በተአምረ ማርያም መቅድምማ << በመዋዕሊሁ ለንጉስነ ዘርዐ ያዕቆብ ዘተሰምየ ቆስጠንጢኖስ>> ይባልልኛል ። ወይ አገሬ ከመቼ ወዲህ ይሆንን ነፍሰ ገዳይ ቅድስናን የምትሰጭ የሆንሺው። ብቻ መጻህፍትን ባላመመርመር እንዳንጠፋ መጻህፍትን እንመርምር ወገን።

    ReplyDelete
  8. ወንድሜ እግዚአብሔር ይስጥልኝ ስለ ምስክርነጥ ምክንያቱ ሰው የገደለ በሚከበርበት ሃገር አስኪ ምከርልኝ ። ከክርስቶስ ቃል ይልቅ በስጋዊ ስሜት የሚመራ ትውልድ ከመጽሐፍ ቃል ይልቅ አሉባልታን ቁም ነገር ብሎ ጆሮን የሚሰጥ ትውልድ ነው። ክርስቶስማ << ሰማዕክሙ ዘተብህለ ለቀደምትክሙ ኢትቅትል ነፍሰ አንሰ እብለክሙ ወዘሰ አምዕዖ እኁኁ በከንቱ ይትኴነን ማቴ ፭፥ ፪፪ ለቅደምቶቻቹ ነፍስ አትግደል የሚል ሰምታቹ ይሆናል እኔ ግን ወንድሙን በከንቱ የትቆጣ ቢኖር ይፈረድበታል ይላል ሕዝቤ ግን ይህንን ወደ ጎን ተወት እያደረገች በ አሮጊቶች ተረት ታስራ ተይዛለች እውነታው ግን ሌላ ነው። በረከታቸው ይድረስብንና ሶስት ሞቶ ሊቃዉንት አባቶቻችን ኩፉውን መናፍቅ አርዮስን ( ወልድ ፍጡር በመለኮቱ) ያለዉን ሲረቱት ኮ ምኑን አልነኩትም ምክንያቱ ቅዱሳን ስለሆኑ ንጉሱ ቆስጠንጢኖስም ከ አባቶቹ ትእዛዝ አልወጣም ይመለሳል ብለው ለቀቁት እንጂ ምላሱን አልቆረጡትም። የ ዚህ ንጉስ ተብየ ሃይማኖተኛ ግን በጣም ያማል ደግሞ ቅዱስ ለማለት ይደፍራሉ አረ ምን ቀረ በተአምረ ማርያም መቅድምማ << በመዋዕሊሁ ለንጉስነ ዘርዐ ያዕቆብ ዘተሰምየ ቆስጠንጢኖስ>> ይባልልኛል ። ወይ አገሬ ከመቼ ወዲህ ይሆንን ነፍሰ ገዳይ ቅድስናን የምትሰጭ የሆንሺው። ብቻ መጻህፍትን ባላመመርመር እንዳንጠፋ መጻህፍትን እንመርምር ወገን።

    ReplyDelete
  9. ቀንደኛ የተሀድሶ አቀንቃኝ ነው

    ReplyDelete
  10. ቀንደኛ የተሀድሶ አቀንቃኝ ነው

    ReplyDelete
  11. ሀራጥቃ የሚሰማህ የለም ይኸንን ለመጻፍ ያባከንከው ጊዜ ግን አሳዘነኝ ፣ ይኸን ስትጽፍ አይንህን ማጥፋትህ አሳዘነኝ ...... መናፍቅ

    ReplyDelete
  12. ደቂቀ እስጢፋኖስ? ስይጣን ያደቀቃችሁ ተኩላዋች። የአቤኔዘር ገፅ እያልክ ትሸረከታለህ ተኩላነት ተባኖበታል ማሊያህን ቀይረህ ና።

    ReplyDelete
  13. ደቂቀ እስጢፋኖስ? ስይጣን ያደቀቃችሁ ተኩላዋች። የአቤኔዘር ገፅ እያልክ ትሸረከታለህ ተኩላነት ተባኖበታል ማሊያህን ቀይረህ ና።

    ReplyDelete
  14. ለነቀፌታ የጓጓህ ትመስላለህ!!!!! ከመጠንህ በላይ አስተያዬት አትስጥ፡፡ የዳንኤልን የነገረ መለኮት እውቀት አንተ ስምህን እንኳን ፌስቡክ ላይ ለመግለፅ ያልደፈርከው ይቅርና እነ አቡነ ኤልሳን ሳይቀር ያስደመመ የፌስ ቡክ ሳይሆን የሐገርና የቤተ ክርስቲያን ጀግና ነው፡፡ ቆይ አንተ ማን ነህ? እስኪ ዳንኤል የተሳሳተበትን የነገረ መለኮት ትምህርት ያስተማረበትን መፅሐፍ ወይም የድምፅ ቅጂ ንገረን፡፡ አስመሳይ!!!!! ቆይ ለንጉስ በንግስናው፣ ባለው ክብር ብትሰግድለት የቱ ላይ ነው ነገረ መለኮት ስህተቱ? ቆይ ግን ክርስትና አታክብሩ ትላለች እንዴ አታምልኩ እንጂ? ስግደት ዓይነት ዓይነት እንዳለው ልብ ይሏል፡፡ ስለዚህ ለነገስታት ባላቸው ዓለማዊ ስልጣን፣ በሰውነታቸው ለአክብሮት መሰገዱ ለምንድን ነው ከነገረ መለኮት ጋር የሚያያዘው? ሰውን በሰውነቱ ማክበር ምንድን ነው ስህተቱ? ያላመኑ ሰዎች ዘንድ ለስብከተ ወንጌል ስትሔድ በትዕቢት ነው የምትሔደው? ለመለኮት የሚሰጠውን ክብርና መገዛት ለሰዎች ሰጥተው ከሆነ ነው መነቀፍ ያለባቸው እንጂ አለመስገዳቸው (አለማክበራቸው) በምንም ዓይነት መመዘኛ ከነገረ መለኮት ጋር አይያያዝም፡፡ ስለዚህ ማን ነበር ስምህ ወንድም ያው ስምህን በወል ስለማናቀው ማለቴ ነው ለስድብ አፍህን አታስፋው ይልቅ የመረዳት ኮሮጆህን ሙላው፡፡ እሱ ነው የሚሻለው፡፡ ጉዳይህ ከሰውዬው ጋር ከሆነ በዛው ጨርስ፡፡ ነገር ግን የክርስትና ጭምብል ለብሰህ የምታደርገውን ማወናበድ ተወው ምንም አይጠቅምህም፡፡ ድሮም ሰራተኛ ነው የሚነቀፈው ሰነፍን ማን ይናገረዋል፡፡

    ReplyDelete
  15. ይህን ያለፈበት ተረትህን ትተህ ወንጌል ስበክ.....ዳንዔልን ካንተ በላይ እናውቀዋለን....አጭበርባሪ ...ተመሳስሎ መኖር ያለፈበት ፋሽን ነው....ለምድህን አውልቅ እና ስለ ወንጌል እንነጋገር

    ReplyDelete
  16. ባዶ ክስ ነው፡፡ ካጠፋ ያጠፋው ምንድን ነው? ከዚያ ውጭ ያለጥፋት መክሰስ መናፍቅነት እንጂ ሰማዕታትን ማክበር አይደለም

    ReplyDelete
  17. zim bilh atidkem lmin yesew Sem bamxfat tidkmsah zim bleh yeradhin sera atsram bemaxlalat ewket ayigegnim tawakim ayikonim lezare altsakam yene dedbe

    ReplyDelete
  18. zim bilh atidkem lmin yesew Sem bamxfat tidkmsah zim bleh yeradhin sera atsram bemaxlalat ewket ayigegnim tawakim ayikonim lezare altsakam yene dedbe

    ReplyDelete
  19. ante rasu yalgebah neger ale. Sew memot mn yidenkal? Snt sew motual ena atakabd

    ReplyDelete
  20. Kkkkk er endew atasiqegn..egna eco enawuqalen yawum kefireyachew

    ReplyDelete
  21. Kkkkk er endew atasiqegn..egna eco enawuqalen yawum kefireyachew

    ReplyDelete
  22. አወይ ጭካኔ ምን አይነት መነኮሳትና ንጉስ ነው፡፡ በጣም አስፈሪ ዘመን ነበር ማለት ነው፡፡ግን ለመንፈሳዊነት ከጨከኑ አይቀር እንዲህ ነው

    ReplyDelete
  23. ብከ ድህነ አለም። እስጢፋኖስ። ክርስትናን አያውቅም?እረ ባክህ ይህን ታሪክ። ከየት ተማርከው ?ኦርቶዶክስ ይህን ታሪክ። ትቀበለዋለች የዚህን እውነተኛ ታሪክ። እምና። የምትቀበለው ከሆነ አንተ ከወዴት ነህ?እውነትንና ታሪክን ያንተ ተራ የሀይማኖት። ቅናት አፍነው የሚያስቀሩት ይመስልሀል? በፍፁም። በፍፁም። እውነት ለትውልዱ። ሁሉ የሚገለጥበት ዘመን ሰለሆነ። አፍናችሁ አታስቀሩትም። አትልፉ የአባእስጢፋኖስና የተከታያቸው ታሪክ። በቅርቡ ለእግዚአብሔር። ክብር። ይፋ ይሆናል እድሜ ብቻ ይስጥህ

    ReplyDelete