Wednesday 29 May 2013

በደሙ ያልተጋረደ



ስልጣን ማዕረግ እውቀት
ዝና ክብርና ውበት
ለሐብት ማዕከለ ምድር
የጥበብ እንብርት ለፍጡር
የፊደል ገበታ ሰርተህ
ለስምህ ሐውልት አቁመህ

ደግነት ተትረፍርፎልህ
የቅኔ ቅኝት ሰምሮልህ
ዝማሬህ በስርቅርቅታ
የትውልድ ልብ ቢገዛ
ስብከትህ ከወዲያ ማዶ
ቢሰማ ቃናው ተወዶ….
አስተውል እንዳትዘነጋ
ሊቅነት አላጸደቀም
ማዕረጉም ሞት አልገሰጸም
ሥልጣኑም አላሻገረም
ሥራውም ከኩነኔ ፍርድ ትውልዱን አላላቀቀም
ጩኸቱም አለማመንን አስዶ አላባረረም
ቁንጅናም የኃጢአትን ጽልመት ሲያፈካ አልተስተዋለም

ይልቅስ ልንገርህ እውነት
ከሰማህ የሞኝ ስብከት
እግዚአብሔር አንድያ ልጁን
እንዲሁ ሰጥቶሀል አሁን
ይህንን በእምነት ተቀበል
አታርፍቅ ከዚያም አገልግል
በትጋት ይፍጠኑ እግሮችህ
ይዘርጉ ይባርኩ እጆችህ
አትቆጥብ ጩህ አሰምተህ
ተጋደል ትጋ በርትተህ

እንዲህ ነው የእውነት መንገዱ
እምነትን እያስቀደሙ
ከቃሉ እየተስማሙ
አልያ ግን
በደሙ ያልተጋረደ ምን ቢሆን ውብ አገልግሎት
ድምጽ እንጂ እንደጸናጽል መዓዛ የለውም ህይወት፡፡

No comments:

Post a Comment