Sunday 19 May 2013

ለአማኑኤል አምጡ

የሲዖል ኃይሏ የሰይጣን ክንዱ
ስለደቀቀ የሞት ጉልበቱ
ስለተፈታ የኀጢአት ቤቷ
ግርግርና ከንቱው ድንፋታ

ክፋት ግሳንግስ
ያላባራው ክስ
የጸና ግዞት
የነፍስ ስደት
ዳር ስላገኘ
በክርስቶስ ደም ጽድቅ እየናኘ
በትንሣኤው ኀይል ድንቅ ምሥራች
ጥጋብ በረከት የደስታ ፍሳሽ
 
'ኛና 'ዳም ሳቅና ዜማ
ለዲያብሎስ ግን ድቅድቅ ጨለማ
ሆኖ ስላየን ዛሬ በጌታ
የበገና ቃል ለአማኑኤል ይምጣ፡፡
ተድሷል ቃሉ
ተሽሯል አቅሉ
የሞት ህልቅና ሞቶ ተረስቷል
ተቆርጦ እትብቱ መውጊያው ተሰብሯል
እኛን ተዛምዶ በእኛ ቦታ
የሞታችንን ትልቁን ዕዳ
ከፍሎ እንካችሁ እንዲሁ ያለዋጋ
ላለን ጌታችን አልፋና ኦሜጋ
ምስጋና አምጡ የጸናጽሉን
አዳኝ መድኃኒት ጌታ ለሆነን
ይምጣለት 'ርሱ ክራር ጭብጨባ
ምርኮን አብዝቶ ወደመቅደሱ በትንሳኤው ኃይል በደም ለገባ፡፡
ለምን ምስጋና እልልታ ብቻ
እኮ ስለምን ሽብሸባ ብቻ?
ጩኹ በደስታ ጩኹ ዘምሩ

በመስቀሉ ቃል በትንሣኤው በኩር አምናችሁም ዳኑ፡፡

No comments:

Post a Comment