ነገረ ሥላሴን ማጥናታችን ምን ያስተምረናል?
1. ሥሉሳዊ አንድነት፦ በሥላሴ ዘንድ ፍጹም አንድነት አለ፤ አንድነታቸውም ፍጹም የኾነና እንከን አልባ ነው። ቅዱስ ዮሐንስ፣ የጌታችን ኢየሱስን ንግግር ሲናገር እንዲህ አለ፤ “እኔና አብ አንድ ነን።” (ዮሐ. 10፥30)። ጌታችን ኢየሱስ ይህን ሲናገር፣ አብ በእርሱ፤ እርሱም በአብ በማይለያይ ዘላለማዊ መለኮታዊ አንድነት አብረው መኖራቸውን ማስተዋል ይቻላል።
ስለ ሥላሴ፣ በመለኮትና በባሕርይ የአንድነታቸውን አለመለወጥና ፍጽምና እንዲህ ብለን መናገር እንችላለን፤
አብ ያለ ወልድ፤ ወልድም ያለ አብ ፈጽሞ አይኖርም ወይም አልነበረም። እናም አብ በወልድ፤ ወልድም በአብ ይኖራል። ፍጹም አንድ
ስለ ኾኑም፣ መላለሙን እጅግ በሚያስደንቅ መግቦት ይመግቡታል፤ ያስተዳድሩታል፤ ይገዙታል፤ ለክብራቸው ያደርጉታል።
ጌታችን ኢየሱስ እንዲህ ብሎ ጸለየ፤ “ቅዱስ አባት ሆይ፥ እነዚህን የሰጠኸኝን እንደ እኛ አንድ እንዲኾኑ በስምህ
ጠብቃቸው። … እኛም አንድ እንደ ኾንን አንድ ይኾኑ ዘንድ፤ እኔም በእነርሱ አንተም በእኔ ስትኾን፥ በአንድ ፍጹማን እንዲኾኑ፥
የሰጠኸኝን ክብር እኔ ሰጥቻቸዋለሁ፤” (ዮሐ. 17፥11፡ 22-23)። ይህ እጅግ ይደንቃል!
ጌታ እግዚአብሔር ግርማና ሞገሱ እጅግ አስፈሪ የኾነ አምላክ ቢኾንም፣ ሰውን በመውደዱ ደግሞ አፍቃሪና ተወዳጅ አምላክ ነው።
“እንደ
እኛ አንድ እንዲሆኑ” የሚለው የጌታችን ኢየሱስ ንግግርም፣ መንፈሳዊው አንድነት
አስቀድሞ በሥላሴ ዘንድ የነበረና ከዚያም ወደ ሰዎች መምጣቱን ወይም ለሰዎች መሰጠቱን ያመለክታል። እናም ቀድሞ በሥላሴ ዘንድ
የነበረው አንድነት ለዘላለም ጸንቶ እንደሚኖረው እንዲኹ፣ በአማኞች መካከልም የመንፈስ አንድነታቸው ጸንቶ እንዲቀጥል ጌታችን
በጸሎቱ ከፍተኛ ትኵረትን ሲሰጥ እንመለከተዋለን።
ይህ የመንፈስ አንድነት ተቋማዊ ወይም ድርጅታዊ አንድነት አይደለም፤ የዚህ የመንፈስ አንድነት መገለጫውም፣
ለክርስቶስ መኖር (17፥23)፣ ፍቅሩ ለዘላለም በእኛ ጸንታ ትኖር ዘንድ (17፥26)፣ ለእውነት ዘወትር መቀደስ (17፥16)፣
ከዓለምና ከዓለማዊነት መለየት (17፥14-16)፣ ኹሉ አንድ ይኾኑ ዘንድ በተለይም የጠፉትም እንዲገኙ እጅግ በሚናፍቅ ማንነት
ውስጥ መኾን ነው፤ (17፥23)።
ዘወትር በመሰብሰብ ብቻ መንፈሳዊ አንድነት አይመጣም። የመንፈስ አንድነት ለክርስቶስ በመታዘዝና ለቃሎቹ
መታመንን ይጠይቃል፤ እንዲኹም የጠፉትን በመፈለግ ውስጥ ጽኑዕ የመንፈስ አንድነት አለ። የፈቃድና የልብ አንድነት በሌለበት፣
መንፈሳዊ አንድነት ፈጽሞ አይኖርም። ቅዱስ ጳውሎስ፣ “በሰላም ማሰሪያ የመንፈስን አንድነት ለመጠበቅ ትጉ።” (ኤፌ. 4፥3) ሲል፣ ይህ የመንፈስ አንድነት በሥላሴ ዘንድ በተደረገልን የማዳን ሥራ እንደ
ኾነና ይህም ክርስቲያን ባመኑት መካከል የሚገኝ መኾኑን አበክሮ የሚናገር ነው (ኤፌ. 4፥14-22)።
ቤተ ክርስቲያን አንድነቷ የሚናደውና መንፈሳዊ ኅብረትዋ የሚበረዘው፣ ከዚህ እውነት የተዘናጋችና ተንሸራትታ
የወረደች ጊዜ ነው። እናም ትምህርተ ሥላሴን በትክክል መማርና ማወቅ ፍጹም የኾነ መንፈሳዊ ኅብረትን ወይም ሥላሴያዊ አንድነትን
እንማርበታለን! አማኞች ከሌላው ጋር ትክክለኛና ጤናማ ኅብረት ሊኖራቸው የሚችለው፣ በሥላሴ ዘንድ ያለውን እውነተኛና ትክክለኛ ኅብረት
ወይም አንድነት ያስተዋሉ እንደ ኾነ ብቻ ነው! የሥላሴን ፍጹም ኅብረት በመመልከት፣ ወደ መንፈስ አንድነት መመለስ ይኹንልን፤
አሜን።
ይቀጥላል
…
ድንቅ ስለሆነው የጌታ መልዕክት እግዚአብሔር ይመስገን::
ReplyDeleteGata abzeto yebarekeh
ReplyDelete