መላለሙን የፈጠረው አካላዊ
ቃል ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ድል ነሺና አሸናፊ፤ የነገሥታት ንጉሥ ነው። ኹሉ ከእርሱ በታች ያለና የተገዛለትም ነው። ያለ እርሱ
የኾነ ምንም እንደሌለ እንዲኹ፣ ያለ እርሱ ኹሉም ነገር ከንቱና እርባና ቢስ ነው። “የሚታዩትና
የማይታዩትም፥ ዙፋናት ቢኾኑ ወይም ጌትነት ወይም አለቅነት ወይም ሥልጣናት፥ በሰማይና በምድር ያሉት ሁሉ በእርሱ ተፈጥረዋል”።
እርሱ ከኹሉ በላይ አምላክና ገዥ ነው።
ይኹንና ይህ ኹሉን የፈጠረ
አምላክና ገዥ፣ የታመመና የተሰቀለ ደግሞም በሥጋ የሞተ ነው። የኢየሱስ ክርስቶስ ሕማማት ለክርስትና ልዩ ባህርይ ነው፤ ክርስትና
ከኹሉም ቤተ እምነቶች የሚለይበትና የሚታወቅበት አስተምኅሮው ሕማማትና መስቀሉ ነው። “አምላክ በለበሰው ሥጋ ሞተ” ብሎ
የሚያስተምር ክርስትና ብቻ ነው። ሌላው ኹሉ እንዲህ ብሎ መነገርን ለአምላክ የማይስማማ ባሕርይ አድርጎ ያቀርበዋል እንጂ ፈጽሞ
አይቀበለውም።
አምላክ ሰውን ከመውደዱ
የተነሳ፣ ሰውን ያድነው ዘንድ ከኀጢአት በቀር የሰውነትን ባሕርይ ከቅድስት ድንግል ማርያም ሥጋን በመንሳት ገንዘብ አደረገ፤
በጠባብ ደረት በአጭር ቁመት ተወስኖ ሰው ኾነ። ሉቃስ ወንጌላዊው እንደሚነግረን በሚያስደንቅ መንገድ፣ “በዚያም የበኲር ልጅዋን
ወለደች፤ በመታቀፊያ ጨርቅ ጠቀለለችው፤ በእንግዶች ማደሪያ ስፍራ ስላላገኙ በበረት በከብቶች መመገቢያ ግርግም ውስጥ
አስተኛችው።” ይለናል። መሲሑ የሰውን ሥጋ በመልበሱ የሕማማትን መንገድ ጀመረ!
ከነቢያት መካከል አንዱ፣ ይህን
እውነት ከዘመናት በፊት አስቀድሞ በመመልከት እንዲህ ብሎአል፤ “የሰማነውን ነገር ማን አምኖአል? የእግዚአብሔርስ
ክንድ ለማን ተገልጦአል?”።
በርግጥም የነቢዩ ጥያቄ ነገረ ድኅነትን ለመረመረ፣ እጅግ ለማመን የሚያዳግት ነው። “ … እግዚአብሔርን
በረጅምና ከፍ ባለ ዙፋን ላይ ተቀምጦ አየሁት፥ የልብሱም ዘርፍ መቅደሱን ሞልቶት ነበር።” ብሎ በሚያስፈራና በሚያስደነግጥ ግርማ ያየውን
ጌታና አምላክ፣ መከራ ተቀባይና ስቁይ ሎሌ ኾኖ ሲመለከተው፣ በመደነቅ ጠይቆአል።
አዎ! ማንም ሊቀርበው በማይችል
ብርሃን ውስጥ የሚኖረው ጌታ፣ ቀይ በአይሁድ እጅ ተያዞ ልብሱን ተገፎ ቀይ ልብስ ለበሰ፤ የእያንዳንዱን ዐሳብና የልብ ዝንባሌ
የሚያውቅ መሲሕ፣ “ሸፍነውም ፊቱን ይመቱት ነበርና፦ በጥፊ የመታህ ማን ነው? ትንቢት ተናገር እያሉ” ቀለዱበት፤ ኹሉን ማዳን የሚቻለውን ልዑል፣
“ከመስቀል
ወርደህ ራስህን አድን… ሌሎችን አዳነ፤ ራሱን ሊያድን አይችልም፤ አይተን እናምን ዘንድ የእስራኤል ንጉሥ ክርስቶስ አሁን
ከመስቀል ይውረድ” እያሉ
በነቀፋ ዘበቱበት።
በእውነት እጅግ አስደናቂ ተቃርኖ
ነው፤ አሸናፊው ስለ ፍቅር ተሸነፈ፤ ልዑሉ የሰውን ልጅ ለማዳን ተዋረደ፤ ንጉሡ ሰውን ለማክበር የንግሥና አክሊሉንና ዘውዱን በፈቃዱ
ተወ፤ የፍጥረተ ዓለሙ ፈጣሪ በፍጡራኑ እጅ ጸዋተወ መከራ ተቀበለ…። ቅዱስ ጳውሎስ ለዚህ ነው፤ “እኛ ግን
የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን፤ ይህም ለአይሁድ ማሰናከያ ለአሕዛብም ሞኝነት ነው፥” ብሎ በድፍረት የተናገረው። ድል ነሺው ክርስቶስ
ተሰቅሎአል፤ መዳንና ሥርየት በዚህ በተሰቀለው ጌታ ነው፤ መስቀሉንና ሕማሙን የሚጋርድ የቱም ትምህርት የክርስትና አይደለም!
“ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን በማይጠፋ ፍቅር ለሚወዱ ኹሉ ጸጋ ይኹን፤ አሜን”።
No comments:
Post a Comment