“ከበዓሉም በታላቁ በኋለኛው ቀን ኢየሱስ ቆሞ፦ ማንም የተጠማ ቢኖር ወደ እኔ
ይምጣና ይጠጣ። … ይህን ግን በእርሱ የሚያምኑ ሊቀበሉት ስላላቸው ስለ መንፈስ ተናገረ፤ …” (ዮሐ. 7፥37፡ 39)
በአይሁድ ባህል መምህራን የሚያስተምሩት ተቀምጠው ነው፤ ጌታችን ኢየሱስ ግን ከአይሁድ ባህልና ሥርዓት
ወጣ ባለ መንገድ፣ ስለ መንፈስ ቅዱስ ሲናገር፣ ኹሉም ሰው እንዲሰማውና ትኵረት እንዲሰጠው ለማድረግ ፈልጐ ቆሞ ደግሞም “ጮኾ”
(ቍ. 38) ተናገረ። ቆሞና ጮኾ በመናገሩ፣ ከበዓሉ በመጨረሻው ቀን የነበሩት ሕዝቦች ኹሉ እርሱን ለመስማት ችለዋል።
በዚህ ክፍል የተጠቀሰው በዓል በዘሌ. 23፥34 እና ዘዳግ. 16፥13 ላይ የተጠቀሰው በዓል ነው፤
በዓሉ ለተከታታይ ሰባት ቀናት የሚከበር በዓል ነው፤ በስምንተኛው ቀን ደግሞ ኹሉ ሕዝብ ባለበት በአደባባይ የሚከበር በዓል ነው።
በዓሉ በሚከበርበት ወቅት፣ ሊቀ ካህናቱ ከግዮን ምንጭ ውኃ ይቀዳል፤ ከዚያም በመሠዊያው ላይ እስኪፈስስ ድረስ ይሞላዋል፤
ጌታችን ኢየሱስ ይህን በምሳሌነት ተጠቀመበት።
ሕዝቡ የጌታችንን ቃል በሰሙ ጊዜ፣ በምድረ በዳ የተሰጠውን የዐለቱን ውኃና በመሠዊያው ላይ ተትረፍርፎ
የሚፈስሰውን ውኃ ያስታውሳሉ። በምድረ በዳው ጉዞ እስራኤል በብርቱ ጥም በነበሩበት ጊዜ የእስራኤል ቅዱስ ያህዌ ውኃን ከዐለት
አፈለቀላቸው፤ (ዘኊ. 20፥11)። ጌታችን ኢየሱስ ወደዚህ ታላቅ ትውስታ ሕዝቡን ወስዶአቸዋል፤ የተናገረውም በስምንተኛው ቀን
ማለትም ሕዝብ በአንድነት በዓሉን ለማክበር በተሰበሰበበት በዓል ላይ ነው። ይህም የሚያመለክተው መንፈስ ቅዱስ ለኹሉም ሰው
እንደሚያስፈልግ ነው።
ጌታችን ኢየሱስ ይህን ለሕዝቡ ያቀረበው እንደ ታላቅ ግብዣ ነው፤ ከዚህ ግብዣ ለመሳተፍ ደግሞ
የሚያስፈልገው፣ መጠማትና መፈለግ ብቻ ነው። ኢየሱስ ወደ እርሱ ለሚመጡ ኹሉ የሚሰጠው “የሕይወት ውኃ” አለው፤ እርሱም ራሱን
ወይም መንፈስ ቅዱስን ነው፤ (ዮሐ. 4፥10፤ 1ቆሮ. 10፥4)፤ እግዚአብሔርን የሚፈልግ ልብ በትክክል እግዚአብሔርን ያገኘዋል
(ኤር. 29፥13)፤ መንፈስ ቅዱስ እግዚአብሔርን በመፈለግ
ለሚራቡና ለሚጠሙ ኹሉ የተሰጠ፣ እውነተኛ ምግብና መጠጥ ነው።
ከክርስቶስ መካፈላችንን ከሚመሰክርልን አንዱና ቀዳሚው ምስክር መንፈስ ቅዱስ ነው። እርሱ ደግሞ ዘወትር
እንድንጠማው ይሻል፤ የማንጠማውና የማንፈልገው ከኾነ ፈጽሞ መርካት አንችልም። መዝሙረኛው በመዝሙሩ፣ “ዋላ ወደ ውኃ
ምንጭ እንደሚናፍቅ፥ አቤቱ፥ እንዲሁ ነፍሴ ወደ አንተ ትናፍቃለች።” (መዝ. 42፥1) ሲል፣
የፍለጋውና የመጠማቱ መጠን ምን ያህል ታላቅ እንደ ኾነ ያስተምረናል።
ከክርስቶስ መጠጣት የሚለው ዐሳብ ፍጹም በክርስቶስ ማመንንና እርሱን በማመንም አዲስ ሕይወት መቀበልን
ያመለክታል። በእርሱ የሚያምን ኹሉ እስኪፈስስ ድረስ በመንፈስ ቅዱስ ይሞላል፤ ኢዩኤል ይህን ነው ያለው፣ “መንፈሴን
በሥጋ ለባሽ ሁሉ ላይ አፈስሳለሁ፤” (2፥28)፤ ይህ የሕይወት ውኃ በእኛ ከሞላ፣ ቀጣዩ
ሥራው ወደ ሌሎች መፍሰስ ነው፤ ለሌሎች የምናካፍለው በረከት አለን፤ ብዙ የምንቀበለውና በመትረፍረፍ መንፈስ ቅዱስ ወደ እኛ
የሚመጣው ለሌሎች እንድንቆርስና እንድንሰጥ ነው። ይህ ሲኾን እጅግ ይበዛልናል፤ መጽሐፍ፣ “ያለውን
የሚበትን ሰው አለ፥ ይጨመርለታልም፤” (ምሳ. 11፥24) እንዲል።
በዙሪያችን ያለው ዓለም እጅግ ምድረ በዳ ነው፤ መንፈሳዊ ነገሩ የደረቀ ነው፤ ክው ብሎ የነቃቃ፤
የሞገገ፣ ከክሳቱ ብዛት የጠቆረ ብዙ ወገን በዙሪያችን አለ፤ እናም ለዚህ ዓለም የምሥራቻችን እንደ ክርስቶስ እንዲህ የሚል
ነው፤ “ማንም
የተጠማ ቢኖር ወደ እኔ ይምጣና ይጠጣ። በእኔ የሚያምን መጽሐፍ እንዳለ፥ የሕይወት ውኃ ወንዝ ከሆዱ ይፈልቃል” አሜን፤ በኢየሱስ ዘንድ የሚንፎለፎል፣ የሚፈልቅ፣ የማይደርቅ፣ የሕይወት ውኃ ምንጭ አለ፤ ምድረ በዳውን
እንደ ኤደን ገነት ማለምለም ይችላል፤ ለምድረ በዳው ተስፋችሁ፤ ለምድረ በዳው ኑሮአችሁ፤ ለምድረ በዳው መንፈሳዊ ነገራችሁ
እነሆ፤ መንፈስ ቅዱስን በመጠማት፣ አብዝታችሁ በመፈለግ ትረኩ ዘንድ በመስቀሉ ርኅራኄ እለምናችኋለሁ።
“ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን በማይጠፋ ፍቅር ለሚወዱ ኹሉ ጸጋ ይኹን፤ አሜን” (ኤፌ.
6፥24)።
amen tebarek
ReplyDeleteከክርስቶስ መጠጣት የሚለው ዐሳብ ፍጹም በክርስቶስ ማመንንና እርሱን በማመንም አዲስ ሕይወት መቀበልን ያመለክታል። በእርሱ የሚያምን ኹሉ እስኪፈስስ ድረስ በመንፈስ ቅዱስ ይሞላል፤ amen amen amen
ReplyDelete