Thursday 25 May 2023

“ከእነርሱ ተለይቶ ወደ ሰማይ ዐረገ” (ሉቃ. 24፥51)

Please read in PDF 

የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ዕርገት ከዘገቡልን ወንጌላት መካከል ሉቃስ ቀዳሚውና ብቸኛው ነው። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን መካከል ከተነሣ በኋላ፣ ለአርባ ቀናት ያህል ለደቀ መዛሙርቱ እየተገለጠ ታያቸው፤ በመካከላቸውም ተመላለሰ፤ በመጨረሻም ከሚወዳቸው ደቀ መዛሙርት ጋር በመኾን ወደሚወዳት ከተማ ቢታንያ ሄደ።

ወደ ቢታንያም ከወሰዳቸው በኋላ ባረካቸው፣ ኢየሱስ የባረካቸው ባርኮት፣ ደቀ መዛሙርቱ ወደ መላለሙ እንዲሄዱ ሥልጣን፣ ኃይልና ተስፋ የሚኾናቸው ነው፤ (ማቴ. 28፥19-20፤ ማር. 16፥15፤ ዮሐ. 20፥21-23)። ደቀ መዛሙርት ወደ ፍጥረት ኹሉ መሄድ የሚችሉት በዚህ ታላቅ ባርኮትና ሥልጣን ነው። የመዳንን ወንጌል ለመስበክ፣ ንስሐና የኀጢአት ስርየትን ለማወጅ፣ አጋንንት ለማውጣት፣ ዕውር ለማብራት፣ አንካሳ ለመተርተር፣ ለምጻም ለማንጻት፣ ሙት ለማስነሣት የሚቻላቸው ከጌታችን ኢየሱስ በተቀበሉት ሥልጣንና ኃይል ነው፤ (ማቴ. 4፥23፤ 15፥29፤ ማር. 3፥10፤ ሉቃ. 6፥17)።

በርግጥ ጌታችን ኢየሱስ ከሙታን መካከል ሲነሣ፣ ከደቀ መዛሙርት  አንዳንዶች አላመኑበትም፤ ስለዚህም “አለማመናቸውንና የልባቸውን ጥንካሬ ነቀፎአል” (ማር. 16፥14)፤ አኹን በቢታንያ ግን ደቀ መዛሙርቱን ከባረካቸው በኋላ፣ “እነርሱ እያዩት ከፍ ከፍ አለ፤ ደመናም ከዓይናቸው ሰውራ ተቀበለችው።” (የሐ.ሥ. 1፥9)፤ ጌታችንም ኢየሱስ በክብር ዐረገ። ከዚህ በፊት ከዓይናቸው እንደ ተሰወረው አይደለም (ሉቃ. 4፥30፤ 24፥3፤ ዮሐ. 8፥59)፣ እያዩት ከዓይናቸው እየራቀ ዐረገ እንጂ።

ጌታችን ኢየሱስ ወደ ሰማያት ካረገ በኋላ፣ የደቀ መዛሙርቱን ኹኔታ ቅዱስ ሉቃስ ሲናገር እንዲህ ይላል፤

ሰገዱለትና በብዙ ደስታ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ፥ ዘወትርም እግዚአብሔርን እያመሰገኑና እየባረኩ በመቅደስ ኖሩ።” (ሉቃ. 24፥52-53)

ደቀ መዛሙርት ከጌታ ዕርገት በኋላ፣

  1. ሰገዱለት፦ ይህም ማለት ጌታ ኢየሱስን አመለኩት፤ የእግዚአብሔር ልጅነቱን አመኑ፤ መሲሕና ጌታ መኾኑን ተቀበሉ፤ ከተነቀፉበት ነቀፋ ነጻ ወጡ፤ በኢየሱስ ጉዳይ መጠራጠርን ትተው አምነው ሰገዱለት።
  2. በደስታ ተሞሉ፦ ስጋትና ፍርሃት ከእነርሱ ራቀ፤ በኢየሱስ ላይ የነበራቸው ጥርጣሬ ፍጹም ተወገደ። በዚህ ታላቅ ደስታ ተሞልተው፣ የኢየሱስን መሄድና ዳግመኛ መምጣት በመናፈቅ እንዲሁም የመንፈስ ቅዱስን መውረድ ሲጠባበቁ ደስታቸው ሙሉ ነበር።
  3. እግዚአብሔርን እያመሰገኑና እየባረኩ በመቅደስ ኖሩ፦ የተባረኩት ደቀ መዛሙርት እግዚአብሔርን ወዲያው መባረክ ጀመሩ፤ ባራኪዎች ብቻ ግን አልነበሩም፤ ይልቁን እየባረኩ በመቅደስ በመኖር በኅብረት የሚጸኑ ነበሩ እንጂ። በተለይም ከጌታችን ዕርገት በኋላ፣ ደቀ መዛሙርት በቤተ መቅደስ በመገናኘት ኅብረታቸውን እጅግ ያጸኑ ነበር፤ (የሐ.ሥ. 2፥46፤ 3፥1፤ 5፥21፡ 42)፤ አማኞች ሕያዋን መኾናቸው ከሚታወቅበት ነገር አንዱ ቅዱስ ኅብረት ነው።

ደቀ መዛሙርት ፍርሃት፣ ጥርጣሬ፣ አለማመን ርቆላቸዋል፤ ዕርገቱን ያዩ የዓይን ምስክሮች ስለ ኾኑ መሲሑን በማመን ጸኑ፤ በመሲሑም ደስታ ተሞሉ፤  እናም በመቅደስ ዘወትር ይጸልያሉ፤ ደግሞም በምስጋና ይተጋሉ፤ እንዲህ ባሉት ሰዎች ላይ መንፈስ ቅዱስ ዘወትር ይወርዳል። ይህ የደቀ መዛሙርት ሕይወት እንዲኹ በሕይወታችን ይኹን፤ አሜን።

“በማያቋርጥ ፍቅር ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን ለሚወዱ ሁሉ ጸጋ ይሁንላቸው።” (ኤፌ. 6፥24)

No comments:

Post a Comment