Tuesday 14 September 2021

“ኑ! ወደ ኦርቶዶክስ[ዊነት] እንመለስ!” (ክፍል ፩)

 Please read in PDF

ኦርቶዶክስ[ዊነት] ምንድር ነው?

“ኦርቶዶክስ ማለት ኦርቶ ርቱዕ፤ ዶክስ ባህል ሐሳብ፣ ኅሊና፣ ስብሐት፣ ምስጋና ይኾናል፤ በተገናኝ ርቱዐ ሃይማኖት ማለት ነው። … ኦርቶዶክሳዊ ማለት ደግሞ የኦርቶዶክሳዊ ወገን እውነተኛ ቅን፣ በሃይማኖቱ ሐሰትና ስህተት ጽነት የሌለበት።”[1]



እንግዲህ በአጭር ቃል ኦርቶዶክስ ማለት፣ እውነተኛ የኾነውን የመጽሐፍ ቅዱስን ትምህርት አመልካች ሲኾን፣ ኦርቶዶክሳዊነት ደግሞ በመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርትና ሕይወት የሚመላለሰውን አማኝ የሚወክል መኾኑን ማስተዋል እንችላለን። ይህም እውነተኛው ክርስትና የተመሠረተበትን እውነተኛነት ያረጋግጥልናል።

በርግጥም፣ እውነተኛው የክርስትና ትምህርት ጤናማና መዳን የሚገኝበት ቃል ወይም ትምህርት ተብሎ ተነግሮአል (ሐዋ. 13፥26፤ 1ጢሞ. 6፥3፤ 2ጢሞ. 1፥13፤ 3፥15)፤ ትምህርቱ ጤናማ ከኾነ የኑሮ ዘይቤና ጠባዩም ፍጹም ጤናማ መኾኑ አያጠራጥርም። ጤናማው ትምህርት ለእግዚአብሔር ክብር በሚያመጣ እውነተኛ ሕይወት እንድንመላለስ ያደርገናል፤ ይህ ጤናማ ትምህርት ደግሞ ርትዕት[እውነተኛ] ከኾነች እምነት ጋር ፈጽሞ ሊነጣጠል የሚቻለው አይደለም። ሕይወት የሚቀዳውና የሚመነጨውም ከእውነተኛ ትምህርትና ከእውነተኛ ፍቅር ነውና። ነገር ግን “ካራና ቅባት ባህላቸውና ትምህርታቸው ከቅዱስ መጽሐፍ የሚጣላ ስህተት የተመላ ክፉ ጥፉ ሲኾን ኦርቶዶክስ ነን ይላሉ።”[2]

የኦርቶዶክሳዊነት ትምህርቱና ሕይወቱ

“… ክርስቲያናዊ እምነትና ምግባር በክርስቲያዊ አስተምህሮ/ዶክትሪን/ ላይ የተመሠረተ ነው። ጤናማ ነገረ መለኮት ጤናማ የኑሮ ጠባይ ይከተለዋል፤ አክብሮተ እግዚአብሔር ያልተለየው ርቱዕ ሕይወት (orthopraxy) እና ርቱዕ ጥልቅ ፍቅር (orthopathy) ከርቱዕ እምነት (orthodoxy) ጋር የተቈራኘና ከእርሱም የሚመነጭ ነውና።”[3]

ኦርቶዶክሳዊነት ፍጹም መጽሐፍ ቅዱሳዊና ለመጽሐፍ ቅዱስ መወገንንም የሚያሳይ ነው። አንድ አማኝ እውነተኛ ኦርቶዶክሳዊ ሊባል የሚችለው፣ በክርስቶስ ትምህርትና ሕይወት ሲጸናና በዚያም ሲመላለስ ሲታይ ነው። የክርስትና ርቱዐዊነት ወይም ትክክለኛነት ምንጩ፣ የክርስቶስ እንከን አልባነትና ፍጹም ቅዱስ መኾን ላይ የተመሠረተ መኾኑን አለመዘንጋት ተገቢ ነው። የክርስትና ትምህርት ዘመን ተሻጋሪና እጅግ ዓመጸኛና ጠማማን ትውልድ አሸንፎና ቀድሶ፣ ወደ ቅኑና ቀናው መንገድ የመለሰው፣ ክርስቶስ በትምህርቱና በሕይወቱ ያለ አንዳች እንከን በምድር ተመላልሶ ክርስትናን በመመሥረቱ ነው።

ጌታችን ኢየሱስ ትምህርቶቹ እንከን አልባና ፍጹማን ናቸው፤ “እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ፤ የሚከተለኝ የሕይወት ብርሃን ይሆንለታል እንጂ በጨለማ አይመላለስም” (ዮሐ. 8፥12) ብሎ እንደ ተናገረ፣ ሕይወቱ ፍጹም የተገለጠ በመኾኑ፣ ሰዎች በፍጽምና እንደሚከተሉት ተናገረ (ማቴ. 5፥48፤ 19፥21)፣ ቅዱሳት ደቀ መዛሙርትም በመንፈስ ቅዱስ መነዳት፣ “እርሱም ኃጢአት አላደረገም፥ ተንኰልም በአፉ አልተገኘበትም፤” (1ጴጥ. 2፥22)፣ በእርሱም ኃጢአት የለም።” (1ዮሐ. 3፥5)፣ “ነውርና እድፍ የሌለው” (1ጴጥ. 1፥19)፣ “ከኃጢአት በቀር በነገር ሁሉ እንደ እኛ የተፈተነ” (ዕብ. 4፥15)፣ “ሕይወትንና አለመጥፋትን ወደ ብርሃን ያወጣ” (2ጢሞ. 2፥10)፣ “ቅዱስና ያለ ተንኮል ነውርም የሌለበት ከኃጢአተኞችም የተለየ ከሰማያትም ከፍ ከፍ ያለ፥” (ዕብ. 7፥26)፣ ብለው መሰከሩለት።

በሕይወቱ ምልልስም ስለ ሕይወቱ፣ “ከእናንተ ስለ ኃጢአት የሚወቅሰኝ ማን ነው?” (ዮሐ. 8፥46) ብሎ ለጠየቀው ጥያቄ፣ ስለ ኃጢአተኝነቱ የመለሱለት አንዳችም መልስ አልነበረም። በርግጥም፣ ሊፈርድበት የነበረው ጲላጦስ እንኳ በተደጋጋሚ ቢመረምረውም ምላሹ፣ “ያደረገውስ ክፋት ምንድር ነው? ለሞት የሚያደርሰው በደል አላገኘሁበትም፤” (ሉቃ. 23፥22) የሚል ነበር። አዎን፤ ሕይወቱና አገልግሎቱ እንከን አልባና ፍጹማን መኾናቸው ተመስክሮለታል። ለእኛም እውነተኛ የሕይወት ልኬትና መመዘኛ ኾኖ መዳረሻችን፣ “የክርስቶስም ሙላቱ ወደሚሆን ወደ ሙላቱ ልክ እስክንደርስ ድረስ፥” (ኤፌ. 4፥12) ተብሎ ተነግሮአል።

ለታሪካዊው ኦርቶዶክሳዊነት[ለመጽሐፍ ቅዱሳዊው እምነት] መመሥረት መሠረት የኾነው፣ የክርስቶስ ትምህርትና ሕይወት አንዳች እንከን የለበትም፤ የክርስቶስ ኃጢአት አልባነት መሠረቱ ከመዳናችንም ከማንነቱም ጋር ጭምር ፍጹም የተዛመደ ነው፤ “ክርስቶስ ኀጢአት ቢሠራ ኖሮ በኀጢአተኛ ፈንታ መሞት አይችልም ነበር። እንግዲህ ክርስቶስ ቅዱስ፣ ጻድቅና ኀጢአት አልባ በመኾኑ የሕዝቡን ኀጢአት ተሸክሞ ደሙን አፈሰሰ፤ (1ጴጥ. 1፥18-19፤ 2፥22-24፤ 3፥17-18።”[4]  

ስለዚህም በክርስቶስ ትምህርትና ሕይወት ላይ፣ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነትና ሥልጣን ያከበረና የተቀበለ፣ በታሪክ ውስጥ የተገለጠውን የእግዚአብሔርን ዐሳብና ፈቃድ ጸጥ፤ ለጥ ብሎ የሚቀበል እርሱ ርቱዕ ኦርቶክሳዊ ነው። እንግዲህ ኦርቶዶክሳውያን ነን ስንል ይህን እውነት ብቻ ተቀባዮች ነን ማለታችንን ኹሉ ሊያውቀው ይገባል።

ጸጋና ሰላም ይብዛላችሁ፤ አሜን!

ይቀጥላል …



[1] ኪዳነ ወልድ ክፍሌ(አለቃ)፤ ገጽ 243

[2] ዝኒ ከማኹ

[3] ሰለሞን አበበ ገብረ መድኅን፤ የደነበረው በቅሎ፤ 2007 ዓ.ም፤ ዐዲስ አበባ፤ ርኆቦት አታሚዎች፤ ገጽ 39

[4] ኮሊን ማንሰል(ቄስ)፤ ትምህርተ ክርስቶስ፤ ገጽ 242

2 comments:

  1. በጣም አስተማሪ ነው ክፍል 2 ይቀጥል

    ReplyDelete
  2. GOD bless you for sharing Abiny. May the SPIRIT be your guide and strength for days to come

    ReplyDelete