Friday 16 July 2021

መድሎተ ስሑት ወይስ “መድሎተ ጽድቅ”?! (ክፍል ፲፩)

 Please read in PDF

ካለፈው የቀጠለ …

አንድን እውነት ማመን ብቻውን እምነት አይኾንም። ለምሳሌ፦ ሰዎች የእግዚአብሔርን መኖር ብቻ ቢያምኑ እርሱ እውነተኛ እምነት አይደለም። እውነተኛ እምነት ግን ከእግዚአብሔር የሚሰጠውን የዘላለም መዳን ለማግኘት ወይም ለመቀበል በክርስቶስ ኢየሱስ ፍጹም ማመንን የሚጠይቅ ነው። በልጁ የማያምን እምነቱ ርቱዕና ምሉዕ አይደለም። ስለዚህም የአዲስ ኪዳን እምነት በግልጥ ከዚህ በታች የሚከተሉትን እውነቶችን በውስጡ የያዘ ነው፤ እኒህም፦



1.   እምነት የእግዚአብሔር ስጦታ ነው፤ ሰዎች ሲያምኑ እምነትን ያገኙት ቅን ስለ ኾኑ ወይም ካመነ ቤተሰብ ስለ ተወለዱ አይደለም። ቅዱስ ጴጥሮስ፣ “በአምላካችንና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ጽድቅ ካገኘነው ጋር የተካከለ የክብር እምነትን ላገኙ፤” (2ጴጥ. 1፥1) ብሎ እንደ ተናገረ፣ እምነት የእግዚአብሔር ስጦታ ነው። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዳለው፣ “የላከኝ አብ ከሳበው በቀር ወደ እኔ ሊመጣ የሚችል የለም፥” (ዮሐ. 6፥44)።

“እግዚአብሔር በመንፈስ መቀደስ እውነትንም በማመን ለመዳን እንደ በኵራት መርጦአችኋልና፤” (2ተሰ. 2፥13)። እግዚአብሔር በእምነት ስለሚገኘው ቅድስና መረጠን እንጂ እኛ አልመረጥነውም። ይህን ደግሞ መንፈስ ቅዱስ ክርስቶስን ለመቀበል የተዘጋጀን እንኾን ዘንድ ባለማቋረጥ ይሠራናል። ይኹንና ዘወትር መዘንጋት የሌለብን እውነት፣ ሰው ለመዳን የማመን ኀላፊነት እንዳለበት ነው። ሰውን የማዳንና የመቀደስ ሥራ ደግሞ፣ የእግዚአብሔርና የእግዚአብሔር ብቻ ነው።

2.   በክርስቶስ ኢየሱስ ጌታችን በሠራው ሥራ ፍጹም ማመን ይጠበቅብናል። ማመን ስንልም ከላይ እንደ ተናገርነው የተሰቀለውንና ከሙታን መካከል የተነሣውን ጌታ፣ ጌታና መድኃኒት አድርገን መቀበል ይገባናል። ለእርሱም ደግሞ ኹለንተናችንን ማስገዛትና መታመን ይገባናል፤ (ሮሜ 6፥17፤ ኤፌ. 6፥6፤ ዕብ. 10፥22)። ይህን የምናደርገው ደግሞ፣ ነባራዊው ኑሮአችንን ፍጹም በሚለውጥና በክርስቶስ ከኀጢአት ወደ እግዚአብሔር መመለስን የሚጨምር ነው፤ ምክንያቱም በቃሉ የተነገረውን ማመንና ያመንነውን እምነት ደግሞ መታዘዝ ፈጽሞ የማይለያዩ እውነቶች ናቸውና፤ (ዮሐ. 14፥15፤ ሮሜ 16፥26፤ ዕብ. 5፥8)።

ከዚህ በመነሣት እምነት የምንለው በክርስቶስ የተሠራውን ሥራ በፍጹም መደገፍና ለእርሱም መታዘዝ፣ ከእርሱም በቀር ሌላ የመዳኛ መንገድ የለም ብሎ ማመንን የሚያካትት መኾኑን መዘንጋት የለብንም። ሊቀ ጉባኤ አበራ እንዲህ ይላሉ፣

“ከመስቀል ሌላ የመዳን አማራጭ አለ ብሎ ማሰብ ከእውነትና ከእግዚአብሔር ፈቃድ ውጪ መኾንን ያመለክታል። መስቀል አያስፈልገንም ከነኃጢአታችን ወደ እግዚአብሔር ለመቅረብ እንችላለን ማለት ዘበት ነው፤ ሐሰት ነው፤ ከእግዚአብሔር ተለይቶ መቅረት ካልኾነ በስተቀር የእግዚአብሔር የቅድስና መለኮታዊ ባሕርዩ የሚያቃጥል እሳት ስለ ኾነ በክርስቶስ መስቀል በኩል ካልኾነ ማንም ሊድንና ወደ እግዚአብሔር ሊቀርብ አይችልም።”[1]

ስለዚህም የምንድነው በእምነት ብቻ ነው ስንል፣ በክርስቶስ በኩል ካልኾነ በቀር ወይም ክርስቶስን በማመን ካልኾነ በቀር በሌላ በምንም አንድንም፤ መዳኛችን እምነት ብቻ ወይም ክርስቶስን ማመናችን ብቻ ነው ማለታችን ነው። ይህም “ብቻ” የሚለው ቃል፣ ምርጫ አልባ፣ ብቻውን በቂ፣ ተከታይ የሌለው፣ ለመዳናችን ብቻውን ብቃት ያለው ማለታችን መኾኑን ፈጽሞ ልንዘነጋ አይገባንም።

የ“መድሎተ ጽድቅ” ጸሐፊ፣ ስለ እምነት ብቻ ብርቱ ስህተት

ለ“መድሎተ ጽድቅ” ጸሐፊ፣ እምነት መሠረትና መጀመሪያ እንጂ መደምደሚያና መጨረሻ አይደለም።[2] ይህም ማለት ያመነ ሰው ለመዳንና ለመጽደቅ ምስጢራትን በግዴታ ሊፈጽም ይገባዋል እንጂ በክርስቶስ ኢየሱስ ብቻ ማመኑ አያድነውም። ይህንንም በተለያየ መንገድ ሲገልጠው እንዲህ ይላል፣

 “የእግዚአብሔር መንግሥት ለመውረስ እምነት ብቻ ሳይኾን በማመን ላይ ጥምቀት የግድ ከኾነ … ተሐድሶዎች መዳን የሚሉት ምኑን ይኾን?”[3]

“ለመዳን መሠረቱና ዋናው እምነት ነው፣ እምነት ብቻ ግን አይደለም። … መጽሐፍ ቅዱስ በእምነት እንደሚገኝ ይናገራል እንጂ “በእምነት ብቻ” ግን አይልም።”[4]

“መዳን በአንድ ቅጽበት፣ ያውም ምሥጢራትን ኹሉ ሳያካትት፣ እንዲሁ በእምነት ብቻ ይፈጸማል ስለሚሉ ከዚያ ወዲያ ምንም ነገር ማድረግ እንደማያስፈልግ ያስተምራሉ። “መዳን በእምነት ብቻ ነው፤ተጋድሎ፣ ጽናት፣ ምግባር ትሩፋት … አያስፈልግም” ይላሉ።”[5]

““በእምነት መዳን” መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትምህርት ሲኾን፣ “በእምነት ብቻ መዳን” የሚለው ግን የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት አይደለም። ይህ … የፈጠራ ትምህርት ነው። ቀጥሎ ደግሞ እንዲህ ይላል፣ “ቅዱስ ጳውሎስ … መዳን የሚገኘው ሕገ ኦሪትን በመፈጸም (በመሥዋዕተ ኦሪት) ሳይኾን መሥዋዕተ ወንጌል በኾው በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን መኾኑን በአጽንኦት ይናገራል እንጂ መዳን “በእምነት ብቻ ነው” አላለም።”[6]

የያረጋል አበጋዝን ዐሳብ በአጭሩ እንዲህ ማስቀመጥ ይቻላል፤ “መዳን በክርስቶስ ቢኾንም ክርስቶስን በማመን ብቻ ግን አይደለም።” ማመን ብቻ የሚለው ቃል፣ በቂና ብቁነት ያለው መኾኑን ፈጽሞ አላስተዋለም። እምነት ብቻ ስንል፣ አምኖ ለመዳን ክርስቶስ ብቻ ማለታችን ነውና። ነገር ግን ከላይ እንደ ገለጥኩት የመድሎተ ጽድቅ ጸሐፊ ኹለት ነገሮችን ኾን ብሎ፣ በተንኮል ልብ ማምታታቱ የሚደንቅ ነው። በክርስቶስ መዳን ማለትን ከሥራ ነጥሎ ያያል፣ ማመን የሚለውን ዐሳብም ግዴታ ከምስጢራት መፈጸም ጋር ያያይዘዋል። ክርስቶስን በትክክል በማመን የዳነ ሰው፣ እምነቱ ወደ መታዘዝ እንደሚወስደው ለምን እንደማያምንና ኹለቱን ለምን እንደሚነጣጥል ያስደንቃል። በትክክል የዳነ ሰው፣ ላመነው አካል በትክክል ይታመናል፤ ይህም ማለት ያመነው እምነቱ ወደ መታዘዝና ወደ እውነት ኹሉ ይመራዋል። ይህን ያደረገ ሰው፣ ከጌታ ጋር እንደ ተሰቀለውና “ዛሬ ከእኔ ጋር በገነት ትኖራለህ” ብሎ ጌታ እንደ መሰከረለት ወንበዴ ፍጹም ይድናል። ኢየሱስን በማመን የዳነ ሰው ወደሚታዘዝ እምነት ወዲያው መምጣት ባይጀምር ወይም በሂደት እምነቱ ባያድግ (ገላ. 5፥22) እምነቱ ጤናማና ሙሉ አይደለም።

ሌላው በማመን የሚገኘውን እምነት፣ ያለ ምስጢራት መፈጸም ባዶ አድርጎ ማቅረብ እግዚአብሔር በልጁ ማመን የሚገኘውን የመዳን መንገድ መናቅና ማክፋፋት ነው። ምክንያቱም  የዘላለም ሕይወት፣ የዳግም መወለድ፣ የዐዲስ ሰውነት፣ የእግዚአብሔር ልጅነት ማግኘት ጉዳይ፣ እግዚአብሔር በቀጥታ ያያያዘው ልጁን ከማመን ጋር ብቻ ነውና። ለዚህም ነው በግለጥ መጽሐፍ ቅዱስ፣ በውኃ መጠመቅን ከምስክርነት ጋር ሲያያይዝ፣ የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀትን ግን ከዘላለም ሕይወት ጋር በግልጥ አያይዞት የምንመለከተው።

ይቀጥላል …  

 



[1] አበራ በቀለ(ሊቀ ጉባኤ) ፤ ትምህርተ ሃይማኖት እና ክርስቲያናዊ ሕይወት፤ 1996 ዓ.ም፤ አዲስ አበባ፤ ንግድ ማተሚያ ድርጅት(ማህበረ ቅዱሳን)። ገጽ 116) 

[2] ገጽ 126

[3] ገጽ 132

[4] ገጽ 183

[5] ገጽ 184

[6] ገጽ 188-189

4 comments:

  1. Yesew metsehaf sititech kemtul eski 1 bichaki wereket tsaf duket

    ReplyDelete
  2. አነብበኸዋል ወይስ በጭፍን ነው ምትተቸው ይኽን የመሰለ ምርጥ መጽሐፍ ብታነበው ጥሩ ነው ከዚህ ክህደትህ ና ኑፋቄህ ትላቀቀለህ እባክህ አንብበው

    ReplyDelete
  3. ደደብ ነህ ትቀጸፋለህ አትዳፈር

    ReplyDelete
  4. ተኩላ ወከይሲ አታስመስል

    ReplyDelete