Friday 16 July 2021

መድሎተ ስሑት ወይስ “መድሎተ ጽድቅ”?! (ክፍል ፲)

Please read in PDF

“እምነት ብቻ”ን መጥላት!

ካለፈው የቀጠለ …

ስለ እውነተኛ መዳን ስንናገር፣ ምርጫ አልባ አድርገን የምናቀርባቸው የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች አሉ። ከእነዚህ ምርጫ አልባ እውነቶች መካከል አንዱ፣ “መዳን በእምነት ብቻ ነው” የሚለው የማይለወጥ እውነት ነው። የ“መድሎተ ጽድቅ” ጸሐፊና አብዛኛው ኦርቶዶክሳውያን ግን ይህን ዐሳብ የሚረዱት በተቃራኒው ነው። መጽሐፍ ቅዱስ፣ “መዳን በእምነት ብቻ ነው” ሲል፣ ሥራን የሚክድና የሚቃወም ወይም ደግሞ በሌላ ጽንፍ፣ “ድነናልና ሥራ ለምኔ!” ለሚሉ አያሌዎች ይኹንታ የሚሰጥ የሚመስላቸው ብዙ ናቸው።



በተለይም ደግሞ የ“መድሎተ ጽድቅ” ጸሐፊ፣ ኾን ብሎ ወይም የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት በማጣመምና ወደ ቃሉ በመተርጐም፣ “ለመዳን ወይም ልጅነትን ለማግኘት እምነት ብቻውን በቂ አይደለም፣ መልካም ሥራና ምሥጢራት መፈጸም ግዴታ ያስፈልጋል” የሚልና፣ “ከዳኑ በኋላ መልካም ሥራ አያስፈልግም ይላሉ” የሚለውን እጅግ በጣም በተምታታና ባልተገናዘበ መንገድ ያቀርባል።

እምነት ግን ምንድን ነው?

“ሃይማኖት ወይም እምነት ማለት በባሕርዩው የማይታየውና የማይዳሰሰው አምላክ መኖሩን እርሱም የዓለም ፈጣሪ፣ ሠራኢ፣ መጋቢ አዳኝ … መኾኑን በኅሊና በልቡና ተገንዝቦ ያለመጠራጠር እውነት ነው ብሎ መቀበልን የሚያመለክት ቃል ነው። እንዲሁም ለተሰጠው ተስፋ አዎንታዊ ምለሽ በመስጠት ይኾንልኛል ይደረግልኛል … አሜን ወአሜን ብሎ ያለማወላወል በሙሉ ልብ እግዚአብሔርንና ቃሉን በተአምኖ መቀበልን ያሳያል።”[1]

   “እምነት፣ በቁሙ ሃይማኖት፣ ማመን፣ መታመን፣ አስተማመን፣ እሙንነት”[2]

“እምነት፤ እግዚአብሔር ታማኝ አምላክ በመኾኑ የጠናገረውን በፍጹም ልብ ተቀብሎ በእግዚአብሔር የተስፋ ቃል ላይ ማረፍ ነው፤ 2ጢሞ. 2፥13፤ ቲቶ 3፥8። ስለዚህ ክርስቲያናዊ እምነት የሚመሠረተው በእግዚአብሔር ቃል ላይ ብቻ ነው፤ ሮሜ 10፥17።”[3]

እንግዲህ እምነት ስንል፣ እንደ ጌታ ቃል በእግዚአብሔር ላይ ፍጹም መደገፍን፣ መታመንን፣ ለእርሱ ብቻ መታዘዝን፣ ኹለንተናዊ በኾነ መንገድ በአምላክ ፍጹም ተስፋ ማድረግን የሚያመለክት ነው። እንደ መጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት፣ ኹለት ዓይነት እምነት አለ ብለን ብንናገር፣ አንደኛው እንደ አጋንንት ያለ እምነት ሲኾን፣ እርሱም እግዚአብሔር መኖሩን የሚያውቅና ነገር ግን አንዳች ሥራን የማያስከትል፣ በቅዱስ ያዕቆብ ትምህርት “የሞተ እምነት” ተብሎ የተጠራው ነው፤ (ያዕ. 2፥17-19፤ 26)።

ኹለተኛውና ከያዝነው ርዕስ ጋር የሚሄደው የእምነት ዓይነት ደግሞ፣ በእግዚአብሔር ላይ ፍጹም መደገፋችንን የሚያሳየውና እውነተኛ እምነት ብለን የምንጠራው ነው።[4] ይህን እምነት የሚያምኑ፣ በእግዚአብሔር ቃል ብቻ ይመራሉ። እንዲህ ያለው እምነት እጅግ በሚያስደንቅ መልኩ ፍጹም መታዘዝን ያስከትላል። እንደ ቃሉ የኾነ እውነተኛ እምነት፣ ዘወትር ሥራን ያስከትላልና። ሥራን የሚያስከትለው የእምነቱ አቅም እንጂ፣ እምነት በሌለበት ሥራ ከቶውንም ሊኖር አይችልም።

እንግዲህ፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት፣ ሰዎች መዳን የሚቻላቸውና የዘላለም ሕይወትን መውረስና፣ ዳግም ልጅነትን ሊያገኙ የሚችሉት በእምነት ብቻ ነው። “… ለማይሠራ፥ ኃጢአተኛውንም በሚያደድቅ ለሚያምን ሰው እምነቱ ጽድቅ ሆኖ ይቆጠርለታል።” (ሮሜ 4፥5)፣ “ኢየሱስ ጌታ እንደ ሆነ በአፍህ ብትመሰክር እግዚአብሔርም ከሙታን እንዳስነሣው በልብህ ብታምን ትድናለህና፤ ሰው በልቡ አምኖ ይጸድቃልና በአፉም መስክሮ ይድናልና።” (ሮሜ 10፥9-10)፣ “ሰው በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን እንዲጸድቅ እንጂ በሕግ ሥራ እንዳይሆን አውቀን፥ ሥጋን የለበሰ ሁሉ በሕግ ሥራ ስለማይጸድቅ፥ እኛ ራሳችን በሕግ ሥራ ሳይሆን በክርስቶስ እምነት እንጸድቅ ዘንድ በክርስቶስ ኢየሱስ አምነናል።” (ገላ. 2፥16)።

ደቀ መዛሙርት ይህን እውነት ሲመሰክሩ፣ ሰዎች በክርስቶስ እንዲያምኑና እንዲድኑ መሰከሩላቸው፤ ያመኑትም በኃጢአታቸው ምክንያት ክርስቶስ እንደ ሞተና እንደ ተነሣም አምነው ተጠመቁ። የደቀ መዛርት ደቀ መዛሙርት ማዕከላዊ ትምህርት፣ “ሰው ያለ ሕግ ሥራ በእምነት እንዲጸድቅ እንቆጥራለንና።” የሚል ነው። ምክንያቱም ሰው የሚድነው በእምነት ብቻ ወይም ሲያምን ብቻ ነውና። “መዳንም በሌላ በማንም የለም፤” (ሐ.ሥ. 4፥12) በሚለው ቅዱስ ቃል ውስጥ፣ አዳኝ መድኀኒት አንድ ብቻ ነው፤ የምንድነውም እርሱን ብቻ በማመን ነው።

በሮሜ መልእክትና በገላትያ መልእክቶች ውስጥ፣ በእምነት ስለ መዳን በስፋት የተጻፈ ሲኾን፣ በዮሐንስ ወንጌልም በኢየሱስ ክርስቶስ ማመን፣ የዘላለም ሕይወት እንደሚያስገኝ በግልጥ ተጽፎአል፤ (ዮሐ. 1፥12፤ 3፥14-15፡ 16፡ 18፡ 36፤ 5፥24፤ 6፥29፡ 35፡ 40፡ 47፤ 11፥26፤ 14፥6፤ ሮሜ 1፥17፤ 3፥21-22፡ 30፤ 4፥3፡ 5፡ 9፡ 13፤ 5፥1፤ 9፥32-33፤ ገላ. 3፥6፡ 8፡ 11፡ 24፤ ኤፌ. 2፥8)። ስለዚህም በቅዱሳት መጻሕፍት ክርስቶስን በማመን ብቻ፣ የዘላለም ሕይወት እንደሚገኝ የታመነና የተረጋገጠ እውነት ነው!

ይቀጥላል …



[1] አበራ በቀለ(ሊቀ ጉባኤ)፤ ትምህርተ ሃይማኖት እና ክርስቲያናዊ ሕይወት፤ 1996 ዓ.ም፤ አዲስ አበባ፤ ንግድ ማተሚያ ድርጅት(ማኅበረ ቅዱሳን)። ገጽ 19-20

[2] ኪዳነ ወልድ ክፍሌ(አለቃ)፤ ገጽ 227

[3] የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት 6ኛ ዕትም፤ ገጽ 178

[4] (Greeke – Pisteuo; Eng. Believe; to believe, put one’s faith in, trust, with an implication that actions based on t hat trust may follow. (NIV Exhaustive concordance (Zondervan 1999); Electronic Edition.

2 comments:

  1. ይኼን ቁንጽል ዕውቀት ይዘህ መድሎተ ጽድቅን ስትተች አለማፈርህ? በመሠረቱ በእምነት ብቻ ብቻ የሚለው ቃል የትኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ነው ያነበብከው።

    ReplyDelete