Monday 12 November 2018

ቤተ ክርስቲያን፣ ተጐታችና ዘመነኛ ችግሮቿን አስተውላ ይኾንን!? (ክፍል 3)

Please read in PDF

1.1. ጥንቈላ
 ይህ ችግር በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በግልጥ እንዳለ ይታወቃል፤ ግን አይደፈርም፣ ደፍረው የሚናገሩ ይገደላሉ፣ ይገለላሉ፣ ይተቻሉ፣ ይነቀፋሉ፣ ይወገዛሉ፤ ነገሩ ግን ሥር ሰድዷል፤ ከምንናገረው በላይ በቤተ ክርስቲያን ስምና አከባቢ ተሰግስገው አሉ፤ ዓርማቸው፣ መለያቸው፣ መታወቂያቸው … ቤተ ክርስቲያኒቱ የእኔ በምትላቸው ንዋያትና ሰዎች ጭምር ነው። መስተፋቅር፣ አንደርቢ፣ ሰብስቤ፣ “አስማት” … የሚባሉ የጥንቆላ ሥራዎች በብዛት የሚሠሩት በቤቱ ጥቂት በማይባሉ ቀሳውስትና ደባትራን ነው። ይህን ያጋለጡ ብዙዎች አይሰደዱ ተሰደዋል፣ አይንገላቱ ተንገላተዋል፤ ይህ ሲኾን እማኝ ምስክር ከሚኾኑት መካከል አንዱ ነኝ! ጠንቋይ ቀሳውስትን፣ ደባትራንን፣ መሪ ጌቶችን፣ መነኮሳዪይቶችን … በመቃወማቸው የተሰደዱ፣ የተዋረዱ፣ የተገደሉ … ሰዎችን ከሚያውቁ ምስክሮች አንዱ ነኝ!
    የእግዚአብሔርን እውነተኛ አስተማሪነት (ኢሳ. 30፥20) አለመቀበል፤ በትምህርቱም አለመጽናት የሐሰት መምህራን ትምህርት ሾልኮ ለመግባት ሠፊ በር ይከፍታል (2ጴጥ. 2፥1)፤ በቤተ ክርስቲያናችን እንደ ቤተ ክርስቲያናችን የመጻህፍት ጽህፈት ቀኖና መሠረት በቀለማት አጊጦ ከሚባዙትና ከቤተ ክርስቲያኒቱ መጻህፍት ጋር ታትሞ እኩል በየመጻህፍት መደብሩ ከሚሸጡት መጻህፍት መካከል አንዱ ዐውደ ነገሥት የሚባለው የጥንቈላ መጽሐፍ ነው። መሥተፋቅር፣ አስማት የሚደግሙ፣ ሞራ ገላጮች፣ መናፍስት ጠሪ፣ ሙታን ሳቢዎች … እና ሌሎችም የጥንቈላ ሥራዎች ሁሉም ለማለት ሊያስደፍር በሚችል መልኩ የሚከናወነው ከደብተራ እስከ ካህናት ባሉት የቤተ ክርስቲያኑቱ አገልጋዮች ነው።

     ጥንቈላ የሥጋ ሥራና (ገላ. 5፥20) ከእግዚአብሔር ሃሳብና ፈቃድ ውጪ መንፈሳዊ ኃይልና መገለጥን የሚፈለግበት መንገድ ነው። እግዚአብሔር ጠንቋይንም አስጠንቋይንም አብዝቶ ይቃወማል። እስራኤል በጠንቋዮች መንገድ እንዳይሄዱ አስጠንቅቋቸዋል፤ እንዲያጠፏቸውም ነግሮአቸዋል (ዘጸ. 22፥18፤ ዘሌ. 20፥27)። ሐዋርያት የክርስቶስን ወንጌል ለብዙዎች ከመሠከሩ በኋላ ከጥንቈላና አስማተኝነት የተመለሱትን አማኞች ይገለገሉበት የነበረውንም ዕቃ እንዲያቃጥሉ አድርገዋል። ለጥንቆላ ሥራ አገልግሎት ይሰጠው የነበረው ማናቸውም ነገር ሲቃጠልና ሲወድም ተቀይሮ ለመንፈሳዊ ሥራ ሲውል አልታየም፤ (ሐዋ. 19፥19)።
      የዚህ ጽሁፍ ጸሐፊ የገዛ “ወንድሞቹና የቤተ ክርስቲያኒቱ አገልጋዮች ያደረጉበትን የድግምትና የጥንቈላ” ሥራ ፈጽሞ አይረሳውም። ጥንቁልና ዛሬ በብዙ የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮችና አማኞች በተለይም ጠበል በሚያጠምቁ አገልጋዮች ዘንድ የማንክደው የአደባባይ እውነት ነው። ጠንቋዮቹም የልብ ልብ ተሰምቷቸው በሚጠነቁሉበት ቤት “ቅዱሳት ስዕላትን” ከመስቀል አልፈው፤ በግልጥ በብዙ ድጋፍና ተቀባይነት አብያተ ክርስቲያናትን ሲያንጹ  ይታያሉ። በተለይ ደግሞ በየዓመቱ ግንቦት አንድ በየአድባሩና በየወንዛ ወንዙ የእንሰሳት መሥዋዕት የሚያቀርቡ ካህናት እንዳሉ ስንሰማ ምን ሊሰማን እንደሚችል ለመረዳት ያዳግታል። የዚህ ጽሁፍ ጸሐፊ በአንድ አመት ግንቦት አንድ የሚደረገውን ካህናት የተሳተፉበትን የጣዖት አምልኮ እርድ በመቃወሙና በዚህ ዙርያ በማስተማሩ ምክንያት የደረሰበትን የግድያ ሙከራ መቼውም አይረሳውም። 
   ቤተ ክርስቲያን በመካከሏ ካሉት መጻህፍት ጀምሮ እስከአገልጋይ ጠንቋይና አስጠንቋይ አማኞቿ ግልጥና ቁርጥ ያለ ነገር ማስቀመጥና እንዲህ የሚያደርጉትን ሰዎች ያለማወላወል የንስሐ ዕድል ሰጥታ ካልተመለሱ ለብዙዎች ሳይሆን ለአንድ ሰው እንኳ መሰናክል እንዳይሆኑ ለመጠንቀቅ (ማቴ. 18፥6) ስትል ከመካከልዋ ልትለይ ይገባታል።
1.2.    ዘረኝነት

      ዘረኝነት የሚለውን ቃል ሶሻሊስታዊው “ማርክሳዊ ሌኒኒናዊ” መዝገበ ቃላት “ከቀለም ወይም ከዝርያ ልዩነት የተነሳ ራስን የተሻለ አድርጐ ማየትና ሲቻልም ማስገበር ማለት ነው። የዚህ ዓይነት የዘረኝነት ተግባርም በአንድ አገር ውስጥ ባሉ ልዩ ልዩ ጐሳዎች፥ ነገዶች ወይንም ዝርያዎች መካከል ወይንም ደግሞ በዘር በቀለም ፣ በመሳሰሉትና በተለያዩ ምክንያቶች ላይ ተመርኩዞ ልዩነቶችን ልዩነቶችን በመፍጠር የአንድ ሐገር ሕዝብ በሌላው ሐገር ህዝብ ላይ ሊፈጽመው የሚችለው ነው።”[1]
       ዘረኛ የሚለውን ቃል ደግሞ ኣማርኛ መዝገበ ቃላቱ ሲተረጉመው፦ “ሰዎችን በዘር ከፋፍሎ የሚያጋጭና በዘር ምክንያት ለአንዱ እያደላ፤ ሌላውን የሚጎዳ፥ የዘረኝነትን አስተሳሰብን፥ አመለካከትን የሚያራምድ” በማለት ይተረጉመዋል።[2]    
   ጌታ እንዳስተማረን በዘመን ፍጻሜ ከሚፈጸሙት ታላላቅ የትንቢት ቃላት መካከል አንዱ “ሕዝብ በሕዝብ ላይ … ይነሣልና” (ማቴ. 24፥7) የሚለው ነው። ይህ ሕዝብ በሕዝብ ላይ የሚነሳበት አንዱና አስቀያሚ መንገድ ዘረኝነት ነው። ዘረኝነት ሁላችን የእግዚአብሔር ልጆች መሆናችንን የሚክድ፤ ሰዎች የሰዎች ልጆች ብቻ መሆናቸውን የሚያስረዳ መርዝ ፖለቲከኞች የሚዘሩት መንፈስን በካይ ዘር ነው። የጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ሞት ለኃጢአት መሥዋዕት የቀረበ ነው። ስለዚህም ክርስቶስ በሞቱ “ለእግዚአብሔር ከነገድ ሁሉ ከቋንቋም ሁሉ ከወገንም ሁሉ ከሕዝብም ሁሉ ሰዎችን ዋጅቶ  ለአምላካችን መንግሥትና ካህናት ይሆኑ ዘንድ አድርጎናል”ና (ራእ. 5፥9-10) በሥጋችን እግዚአብሔርን ልናከብር ይገባናል፤ (1ቆሮ. 6፥20)።
     ዘረኝነት በሥጋ የራስን ነገድና ቋንቋ ተናጋሪን ፈልጎ የመግባባት መንገድ ነው። ይህ መንገድ በራሱ ችግር አይኖርበት ይሆናል፤ ነገር ግን ዘረኝነቱ የሚንጸባረቀውና ጎልቶ የሚወጣው “ከእኔ በላይ ሌላ ዘር የለም፤ የእኔ ዘር ብቻ ነው ንጹሕ፤ ሌላው ዘር ከእኔ በታች ነው ፤ እንደእኔ ዘር ታማኝ እንደእኔ ዘር ቆንጆ የለም፤ የእኔን ዘር የእገሌ ዘር ጨቁኖታል፣ በድሎታልና የእገሌን ዘር ፈጽሞ አልወደውም፤ የእኔ ዘር ካልሆነ በዚህ ሥፍራ ሌላ ሰው ሊቀጠር፣ ሊሠራ፣ ደመወዝ ሊያገኝ አይገባውም፤ የእኔ ዘር ... የእኔ ዘር…. የእኔ ዘር … ” የሚለው ንግግር ምንጩ ወይም መንፈሱ ከእግዚአብሔር፤ ከማይጠፋው ዘር ከተወለደ ማንነት የሚወጣ አይደለም።
    ይህ ሥር የሰደደ ክፋት ናዚዎች አይሁዳውያንን እንዳይቀበሉና ለእስከመጨረሻው ለመጥላት፤ ለመጨፍጨፍና ለጅምላ ግድያ ምክንያት ሲሆን ፣ ሩዋንዳ አንድ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በእኛ ዕድሜ አንድ ሚሊየን ገደማ የሚገመት ሕዝብ መጥረቢያና በገጀራ የመተላለቁ ምክንያት (የአብያተ ክርስቲያናት መሪዎችና አብያተ ክርስቲያናት ሳይቀሩ የተሳተፉበት) ምንጩና መነሻው የዘረኝነት መንገድ ነው። በዚህ መንገድ እኛም ብዙ ጊዜ እንዲህ ያለ ከማድረግ የእግዚአብሔር እጅ ከልክላን እንጂ እንዲህ ያለ ደም ለማፍሰስ የታቀዱ ብዙ ዕቅዶች ነበሩ። እግዚአብሔር ግን ትልቅ ነው!!!
     እኛ ከእግዚአብሔር በመወለዳችን የዚህ አለም ዘር (ማንነት) አያንጨረጭረንም። እኛ “በእምነት በኩል ሁላችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጆች ነንና” በመካከላችን “አይሁዳዊ ወይም የግሪክ ሰው የለም፥ ባሪያ ወይም ጨዋ ሰው የለም፥ ወንድም ሴትም የለም፤ ሁላችን በክርስቶስ ኢየሱስ አንድ ሰው ነንና” (ገላ. 3፥26፤ 29) እንዲህ በክርስቶስ የጸናውን አንድነት በቤተ ክርስቲያን መካከል እንዲያቆጠቁጥ ማድረግ አደገኛ አጋንንታዊ አስተምህሮ ነው።
     ዘረኝነት በመካከላችን አብቦ አፍርቷል።ሲካድና ሲስተባበል እንዳልነበር አሁን በግልጥ ቃል እንዲህ እስከመባል ተደርሷል ፦ “ … አሁን አሁን ነገራችን እንደዖዝያን ለምጽ ሊሸፈንበት ከማይችልበት ደረጃ ላይ ደርሷል። ራሱ ችግሩም “አለሁ ፣ አለሁ” ብሏል። የለህም ብንለውም ራሱን በራሱ ያስመሰክራል። … የዘመድ አሠራሩ … ወዘተ አግጠው ወጥተዋል።”[3]
    በምዕራቡ ዓለም በአሜሪካና በአውሮፓ ያሉ ጥቂት ያይደሉ “ክርስቲያኖች” በጽዋና በማህበር ሰበብ የሚሰባበሰቡትና የሚያመልኩት “ከዘራቸው” ካልሆነ ሰው ውጪ እንዳልሆነ የጠራራ ሐቅ ሆኗል። ኹላችን የአዳም ልጆች ሆነን፣ የአዳምን እጁን ከንባታ፣ እግሩን አፋር፣ ጭንቅላቱን ሶማሊያ፣ አይኑን ሐዲያ፣ አፍንጫውን ኦሮሞ፣ ጆሮውን ትግሬ፣ ጡቱን ሲዳማ፣ ጥርሱን ሐመር … አድርገን የምንከፋፍል አይንና አይንን ለማበላለጥ የምንሻ የህሊና ድሆች እንዴት ይሁን የምናሳዝነው? … ለብዙዎቻችን እውቀታችን ከዘረኝነት ሀሁ አለማለፉ እንዴት ያሳዝናል? ሐገርንና ወገንን መውደድ ከዘረኝነት መርገም ጋር ለውሰን ሌላውን ለመስበክ የምንጥር ከንቱዎችም በጌታና በባዕለ ህሊናዎች ፊት ሥራችሁ የጠራ መሆኑን አምናችሁ ንስሐ ብትገቡ እጅግ መልካም ነው።
    በተለይ ቤተ ክርስቲያን በአንዳንድ “መጻህፍቶቿ” ውስጥ “እገሌ የሚባለው ዘር ወይም ከእገሌ ዘር ጋር መጋባትና በሩካቤ መገናኘት መንግሥተ ሰማያት አይገባም፤ አብሮ የፈጸመውም አይገባም” (መጽሐፉን መጥቀስ አስፈላጊ መስሎ አልታየኝም) የሚል ጽሁፍ በግልጥ ተቀምጧል። እነዚህ መጻህፍት አንዳንዶቹን ማተሚያ ቤቶቹ በሌላ ሲቀይሩት ቢታይም አሁንም በገበያ ላይ አሉ። ስለነዚህ መጻህፍት ቤተ ክርስቲያን ዝምታን እንጂ ሌላ ነገር የመረጠች አይመስልም። ነገር ግን እነዚህ መጻህፍት ለብዙ ምዕመናን መሰናክል ምክንያት እንደሆኑ መካድና ማስተባበል ሳያሻ ቤተ ክርስቲያን ያለአንዳች ማቅማማት ይቅርታ በመጠየቅ እኒህን የዘረኝነት መርገም ያለባቸውን መጻህፍት ከመካከልዋ ልታስወድግ ይገባታል።
መንፈስ ቅዱስ ሆይ ልባችንን አድስ፣ ዘመናችንን እንደ ቀድሞው መልስ፤ አሜን።
ይቀጥላል …



[1] የማርክሲዝም ሌኒኒዝም መዝገበ ቃላት፤ አዲስ አበባ ፤ 1978 ዓ.ም፤ ኩራዝ ማተሚያ ድርጅት
[2] አማርኛ መዝገበ ቃላት፤ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ጥናትና ማርምር ማዕከል፤ አዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ፤ የካቲት 1993፤ አርቲስቲክ ማተሚያ ድርጅት። ገጽ 437
[3] ዲ/ን ዳንኤል ክብረት፤ ስማችሁም የለም፤ 2006 ዓ.ም፤ አዲስ አበባ፤ ገጽ 15።

6 comments:

  1. እግዚአብሔር ጨምሮ እና አብዝቶ ይባርክህ ማለት እወዳለሁ።

    ReplyDelete
  2. አንተ አጽራረ ቤተ ክርስቲያን

    ReplyDelete
  3. እግዚአብሄር ሆይ ይህን ክፉ ተግባር በኢየሱስ ስም ከቤ/ክያኔ ላይ አንሳ!

    ReplyDelete
  4. God bless you. what you said is true and now working in the church.bu the finger of God will come upon who do this activities.

    ReplyDelete