Saturday 26 May 2018

ከአጋንንት ምስክርነት?


ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ወደዚህ ዓለም የመጣበት ዋና ዓላማ የዲያብሎስን ሥራ ያፈርስ ዘንድና (1ዮሐ.3÷8) በኃጢአት የታሰሩት ነጻ ወጥተው ህይወት እንዲሆንላቸው፤ እንዲበዛላቸውም ነው፡፡ (ዮሐ.10÷10)፡፡ ይህንን ለማድረግም ቀድሞ “ኃይለኛውን ሰይጣን ማሰር” እንደሚገባና ከዚያ በኋላ “ወደኃይለኛው ቤት በመግባት ቤቱን መዝረፍ” ማለትም ሰይጣንን በማሸነፍ አጋንንትን ማውጣት ፣በክፉ መንፈስ የሚሰቃዩትን፣ በኃጢአት ባርነት የተያዙትን በጽድቅ ነጻ በማውጣት ምርኮን መከፋፈል እንደሚገባ አስተምሮናል፡፡ ትልቁ የጌታ ምስራችና የአገልጋዮቹ ደስታ በመንፈስ ቅዱስ ምሪት፣ ምስክርነትና የሥልጣን ቃል የአጋንንትና ግዛት በማስደድ መንግስቱን ወደሰዎች ልብ ግዛት ማቅረብ ነው፡፡

በሮማይስጡ ላቲን ሉሲፈር የተባለው አጥቢያ ኮከብ (ኢሳ.14÷12)፣ ኃጢአትን ከውስጥ ከራሱ አመንጭቶ በማፍለቁ ምህረትን ያጣው ሰይጣን(ህዝ.28÷18፤ ዮሐ.8÷44)፣ በእግዚአብሔር ገነት ዔድን የነበረው ኪሩብ በተቀደሰው በእግዚአብሔር ተራራ በእሳት ድንጋዮች መካከል ሊመላለስና ሊጋርድ የተቀባ ነበር፡፡(ህዝ.28÷13-14)፡፡ ዕውቀቱም ፍጹም የሆነና በእኔነቱ በመመካት “እኔ እግዚአብሔር ነኝ” በማለቱ ምክንያት በተመኘው የትዕቢት ከፍታ ልክ ወደታላቁ ጥልቅ ወደታች ወረደ፡፡
ይህ ብርቱ ባላጋራ ወርዶ የቀረ ብቻ አይደለም፡፡ ድል መንሳቱና ኃይሉ በክርስቶስ ኢየሱስ የተወሰደና ያበቃለት ቢሆንም ጥቂት የሚሰራበት ጊዜ ግን እንዳለው ተብሎለታል፡፡(ራዕ.12÷12)፡፡ የቀረው ዘመን በእግዚአብሔር ቅመራ ጥቂት ቢሆንም በዚህችም ጊዜ ወደምድር የወረደው በታላቁ ቁጣ ነው፡፡ በገዛ ትዕቢቱ የወረደው ሰይጣን ዛሬም በብርቱ ቁጣ ይቆጣል፤ ዳቦ እንደተነጠቀ ህጻን ሳይሆን ግልገሏ እንደተነጠቀባት እንስት አንበሳ ነው እንጂ፡፡ ቁጣውን ግን ፀጥ የሚያደርግ ኃይል ብርቱ ብርታት አለ፡፡ ደሙና መንፈስ ቅዱስ፡፡
ባለው ጥቂት ዘመን ወደሴቲቱ ልጆች ወደቤተክርስቲያን ፊቱን የመለሰና በብርሐናዊው መልክ ዛሬ አለልክ እያሳሳተ ነው፡፡ “በተለያየ መንገድ” ዛሬ በየአብያተ ክርስቲያናት አጋንንት ወጡ፣ አጋንንት ወጡበት የተባሉ ቪሲዲዎች በየገበያው ደርተው ሲሸጡ እናያለን፡፡ ከሁሉ በላይ አሳዛኙና አሳፋሪው ነገር ከሰይጣን መረጃ ተፈልጎ የማስለፍለፉ ሥራ ነው፡፡
አጋንንትን በማውጣት መፈወስና የወጡትን አጋንንት መለየት ሁለት የተለያዩ ጸጋዎች ናቸው፡፡ (1ቆሮ.12÷9-10)፡፡ ሁለቱም ጸጋዎች ለአንድ ሰው ተሰጡ ብንል እንኳ አሁን እየሆነ ያለው ነገር የሚያሳፍር ነው፡፡ ህዝብ ባለበት ሥፍራ እየለፈለፈ ሰይጣን “እገሌ መድኃኒት አሰርቶበት ነው፣ እገሌ በቡዳ በልታት ነው፣ መቃብር ስፍራ ሲሄድ ይዤው ነው፣ እገሌ በምግብ አጉርሶት ነው … ብዙ ሲባል ይደመጣል፡፡ ሲጀመር ሰይጣን እውነት እንኳ ቢናገር ፈጽሞ እውቅና ሊሰጠው አይገባም፡፡
ቅዱስ ጳውሎስ በሁለተኛው ሐዋርያዊው ጉዞው ላይ እንዲህ ያለ ነገር ገጥሞት ነበር፡፡ በፊሊፒስዩስ አንዲት በምዋርት ሥራ የምትተዳደር ሴት እነርሱ ወደጸሎት ስፍራ ሲሄዱ “የመዳንን መንገድ የሚነግሩአችሁ እነዚህ ሰዎች የልዑል አምላክ ባሪያዎች ናቸው…” ብላ ጮኸች፤ ይህንንም ደጋግማ ተናገረችው፡፡ የተናገረችው እውነት ቢሆንም ጳውሎስ ግን በመንፈሱ ተጨነቀና ዘወር ብሎ “ከእርስዋ እንድትወጣ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አዝሃለሁ አለው፤ በዚያም ሰዓት ወጣ።”(ሐዋ.16÷16-18)፡፡
ሰይጣን የሚናገረው እውነት ቢሆን እንኳ በምንም አይነት መንገድ ከአጋንንት ምስክርነት መቀበል አያሻም፡፡ ብዙዎች ወደ አጋንንት ትምህርት ተስበው የሄዱት ሲለፈልፍ የሚናገረው እውነት ነው እያሉ ነው፡፡
እንዲህ ፍጥጥ ያለ የክርስቶስ የወንጌል የእውነት ቃል እያለ ቤተክርስቲያን ለምን አጋንንትን አስለፍልፋ መረጃ እንደምታፈላልግ ግራ ነው፡፡ አጋንንት አጋንንት ናቸው፤ ምንም አይነት ነገር ከእነርሱ መሰብሰብ መዘዙ ብዙ ነው፡፡ በልፍለፋው ከትዳር መፋታት እስከ መቃቃር፣ ከጥላቻ እስከ ለግድያ መፈላለግ የደረሱ ሰዎችን አውቃለሁ፡፡ እንኪያ ታዲያ ሰይጣንን ከሰው ግዛት ማስደድና በሰው ግዛት ላይ የእግዚአብሔርን መንግስት ሥራ ማስፋፋት እንጂ ሰይጣንን አቁሞ መረጃ ጠይቆ በቪሲዲና በካሴት ቀድቶ መቸብቸቡ የአጋንንትን ትምህርት ከማስፋፋትና እውነት ነው ብሎ ከማጉላት ውጪ ፈጽሞ ምስክርነት ሊሆን አይችልም፡፡
ምስክርነት ከዳኑና ከተፈወሱ በኋላ እንጂ መንፈሱ ገና ግዛቱን ባልቀቀበት ሁኔታ ምስክርነት የለም፡፡ ምስክርነት ቃሉን ላመኑ እውነተኞች እንጂ ቃሉን እየሸቃቀጠ ለሚያስት ሰይጣን ፈጽሞ ሊሆን አይገባውም፡፡ ደግሞም ክፉ መናፍስትን የሚያወጣ ሁሉ መናፍስትን መለየት አይችልም፡፡ በልዩ ሁኔታ ሁለቱም ጸጋዎች ካልተሰጠው በቀር ጸጋዎቹ የተለያዩና ለሁለት አካላት ሊሰጡ የሚገባቸው ናቸው፡፡
እንኪያስ ሳናውቀው ለዲያብሎስ ዕውቅና በመስጠት ብዙዎችን የበደልንበትንና ለአጋንንታዊ ትምህርት ተላልፈን የተሰጠንበትን መንገዳችንን በንስሐ እንድናድሰው የአጋንንት ምስክርነት ምን እውነት ቢሆን አያስፈልግምና ልባችንንና መንፈሳችንን ወደ ኢየሱስ የወንጌል ቃል እንመልስ፡፡
አቤቱ! ህዝብህን ከማይታይና ከሚታይ ስህተት በርህራኄህ አድን፡፡ አሜን፡፡
ይህ ጽሑፍ የተጻፈው የዛሬ ሰባት ዓመት በወርኀ መጋቢት ነው፤ ለሰሞኑ አጋንንዊ ምስክር ጮቤ ለሚረግጡ ምላሽ ቢኾን ብዬ እንደ ወረደ አቅርቤዋለሁ፡፡


3 comments:

  1. leka endihm ale

    ReplyDelete
  2. leka endihm ale

    ReplyDelete
  3. መጀመሪያ ስምሕን አስተካክል ማእረግ ይቀድማል
    ካላወከው ጠይቅ የዳቆንነት ትርጉሙን ሳታውቅ
    ዝም ብለሕ አቤኔዘር ዳቆን አትበል?ሴጣንም መልአክ ነበር ነገር ግን እራሱን ፈጣሪ በማድረጉ
    ወደጥልቁ ተጥሏል እናም አንተ እራሥሕን ማን እያደረክነው እንደኔ አና እንዳንተ ሀጢያተኛ ሰው
    የሚናገራቸው አይደሉም እሳቸው በእግዚያብሔር የተመረጡ ሀዋርያ ናቸው አንተ ጠነቋይ ብትላቸውም ባተላቸውም ክብራቸው
    አይቀንስም ይልቅ እንደዚ የሚያናግርህ ፀብአጋንንትነው እራስሕን አሥፈትሽ? የሰውልጅ ፀጋው ልዩልዩ ነው መንፈስ ቅዱስ ግን አንድ ነው
    የመዘመር ፀጋ የሚሰጠው አለ እንዲሁም የመቀደስ ፀጋ የሚሰጠው አለ የመፈወስም የሚሰጠው አለ እናም እሳቸው ደግሞ የመፈወሱ ፀጋ ለሳቸው ተሰጣቸው እና እግዚያብሔር ይመስገን እንጂ የምን ማማረር ነው እንደእነሱ አይነት እግዚያብሔር ያብዛልን።ቅናት አስመሰለብሕ ምነው ፓስተሮቹ ቤት እንደነርሱ
    አይነት በኢየሱስ ክርስቶስ በድንግል ማርያም ለጅ
    ስም የሚፈውስ የለም እንዴ ? ለቤተክርስቲያን የሚያስብ አባት እግዚያብሔር ያብዛልን ዝም ብለህ ከምተች አኔ ለቤተክርስቲያን ምን ሰራሁ በል 😉😉😉😉😉😉😉ሰይጣን አኮ መልካሙን ደብቆ ከፉውን ነው የሚየሳይህ አይንሕን ግለጥ።

    ReplyDelete