Tuesday 26 December 2017

በጋሻው “አፍንጫው ሲነካ[ስሙ ሲነሣ]፣ ዓይናችኹ ላላቀሰ” ኹሉ!



Please read in PDF
    በግልጽ አንድ ያልተግባባነው ነገር አለ፤ የሐሰት ትምህርትን መቃወምና የሐሰት መምህራንን አለመቀበል የወንጌል ልብ አለመያዝ ወይም በወንድም ላይ መፍረድ ማለት አይደለም፡፡ ለበጋሻው ሳልራራለት ቀርቼ አልነበረም የሐሰት ትምህርቱን የተቃወምኩት፡፡ “አንዳንዶች ተከራካሪዎችንም ውቀሱ፥ አንዳንዶችንም ከእሳት ነጥቃችሁ አድኑ፥ አንዳንዶችንም በሥጋ የረከሰውን ልብስ እንኳ እየጠላችሁ በፍርሃት ማሩ፤” (ይሁ.22-23) የሚለውን የቅዱስ ይሁዳ ቃልም ፈጽሞ ጠፍቶኝ ወይም ተዘንግቶኝ አይደለም፡፡
  ብናስተውል፣ የሐሰት ትምህርትን እንደቃሉ መቃወም እውነተኛ አማንያን እንዲጠበቁና እንዲጠነቀቁ ማድረግ ብቻ ሳይኾን፣ ሐሰተኛውን መምህር እንዲመለስ ተግሳጻዊ በኾነ መንገድ “የመማጸንም ሥራ” ነው፡፡ ትምህርቱን ስንቃወም ሰውየውን[የሐሰት አስተማሪውን] ከመጥላት ጋር አይደለምና፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ በቆሮንቶስ የነበረውን የታወቀውን አመንዝራ ሰው፣ “ … እንደዚህ ያለው ለሥጋው ጥፋት ለሰይጣን እንዲሰጥ ፍርዴ ነው” ሲል፣ ከጥላቻና መዳኑን ካለመፈለግ አንጻር ሳይኾን፣ “  መንፈሱ በጌታ በኢየሱስ ቀን ትድን ዘንድ” ነው፤ (1ቆሮ.5፥5)፡፡

   በበጋሻው ዙርያ ባለው ነገር የቆሙቱ ተቃዋሚዎች ሦስት ዓይነት መልክ ነበራቸው፤ (1) ሲኖዶሱ በጋሻውን ሲቃወምና ሲያወግዘው የተናገረውን እንጂ ያስተማረውንና ያለበትን ኹኔታ በትክክል ከመረዳት አንጻር አልነበረም፡፡ ለዚህም የሲኖዶሱ ውግዘት ኹለት ዓይነት ነገር ገጥሞት ነበር፤ ከመጀመርያውም በጋሻውን የማይቀበሉቱ በተቃውሞአቸው በርትተዋል፤ መወገዙም ጥሩ ዕድልን ፈጥሮላቸዋል፤ ውድቀቱንም የትንቢታቸው ስምረት ያህል ተደስተው የጻፉ ብዙዎች ናቸው፤ ከመጀመርያውም ከእነርሱ ጋር ስላልገጠመ ያልተደሰቱ፣ ሌላ ተልእኮ እንዳለው በማሰብ በጥርጣሬ ሲመለከቱት የነበሩቱ፣ “ይኸው ያልነው ደረሰ” በማለት ትንቢታቸው እንዲጸድቃላቸው በጽኹፎቻቸው ተማጽነዋል፡፡ ሌሎቹ ደግሞ የተወገዘበትን ምክንያት ስለጠሉት፣ በአገልግሎት ስለበለጣቸው እንደኾነ በምቀኝነት ምክንያት እንደተወገዘ አድርገው አቅርበዋል፡፡
   የሲኖዶሱ አሳዛኙ ገጽታ፣ የእምነት እንቅስቃሴ ትምህርትን አደገኛነት በማስተዋል፣ በትክክል ከማወቅና ይህንንም ትምህርቱን በዓላማ ከመቃወም አንጻር ውግዘትን አለማስተላለፉ ነው፡፡ የውግዘቱ ጠቅላላ ውጤት የቤተ ክርስቲያንን ልእልና መጋፋቱን፣ የጽርፈት ቃል ከአፉ በመውጣቱ ብቻ ላይ ማተኮሩ ግልጥ አይደለም፡፡ ለምን ተግቶ የትምህርቱን ኑፋቄነትና መራዥነት፣ ክርስቶስን[ክብር ይግባውና] የሚያሰየጥን ትምህርት መኾኑን በሚገባ አጥንቶ፤ አብጠርጥሮ ኹሉም አማኞች እንዲጠነቀቁና እንዲጠበቁ እንዳልሠራ ግልጥ አይደለም፡፡ አውግዞ ዝም ከማለት በቀር፣ የተነጠቁት ነፍሳት ግድ ለምን እንዳላለውም ሲታሰብ ለባለአእምሮ ይጨንቃል፡፡ ሲኖዶሱ እንዲህ ያሉ ተመሳሳይ የአደባባይ ስህተቶችን ይፈጽማልና ቢያስተካክለው እጅግ መልካም ነው፡፡ ውግዘትን ብቻ በማጮኽ “እንደዕቅበተ እምነት” ከመጠቀም፣ ትምህርቱን በሚገባ ማጋለጥና ለምዕመናን ኹሉ እንዲረዱት ማድረግን ይበልጥ ተግቶ ሊሠራበት በተገባው ነበር፡፡
    (2) ኹለተኛዎቹ ተቃዋሚዎች ከወንጌላውያን ሕብረት መካከል ናቸው፡፡ እኒህ በአብዛኛው ኹለት መልክ አላቸው፤ አንዳንዶቹ በግልጥ የመቃወማቸው ምክንያት የእምነት እንቅስቃሴ አማኞች በመኾናቸው ነው፡፡ እኒህ አካላት ከበጋሻው ጋር ፍጹም አንድነት ያላቸውና ወደእምነቱ በመግባቱም ደስተኞች የኾኑት ናቸው፡፡ አቋማቸውንም ወይም በጋሻውን የሚደግፉ መኾናቸውን አንዳንድ የፕሮቴስታንት ድረ ገጻትን አስተውያለኹ፤ ለምሳሌ እንደChristian Tube ያሉ ድረ ገጻት በጋሻውን በግልጥ የሚደግፉ መኾናቸውን በአብዛኛውም በዚያ ቲዩብ ላይ የእምነት እንቅስቃሴ ሰዎች እንደሚወጡም አስተውያለኹ፡፡ ስለዚህ እኒህ እኔን መቃወማቸው ምንም አያስደንቅም! ኹለተኛዎቹ ደግሞ “በጋሻው የወንጌል ልብ በመያዙ እኔ ቀንቼ በክፋት ልብ የጻፍኹበት እንደኾነ” ትንሽ አጩኸው አቅርበውታል፡፡ እንዴት እንዲህ ሊረዱ እንደቻሉ አላውቅም፡፡ እንዲህ ካላሉ በቀር በእርግጥ ሊቀበላቸው የሚችል ስለማይኖርም ይኾናል፡፡ “የራሳቸውን የቤት ሥራ” ሳይጨርሱ ተሻግረው በብዙ መጥተው ለምን መኮነንን እንደመረጡ አላውቅም፡፡ ብቻ ግን ከቴክኖሎጂው የተነሣ የዓለምን አንድ መንደርነት ማስታወሱ በቂ ነው፡፡
     (3) ከተሐድሶያውያን አንዳንዶች በግልጥ አምርረው ስለበጋሻው ሲከራከሩ ፊት ለፊቴ ተጋጥመዋል፡፡ አንዳንዶች እንደሙጫ ተጣብቀው እስካኹንም ሊተዉኝ አልወደዱም፡፡ ምናልባትም ወደፊት ይተውኛል ብዬም አላስብም፡፡ ከልባቸውም ተግተው ለክፋት እንደሚሠሩ አስባለኹና ለጌታ ሥራ በብዙ መጨከን እንዳለብኝ አምናለኹ፡፡ ስለክርስቶስ በጥልቅ ፍቅር ያስተምሩና ይዘምሩ የነበሩ ሰባክያን፣ መምህራን፣ ዘማርያንና ሌሎችም ድንገት በአደገኛ ኑፋቄ ተጠምደው ሳይ በብዙ አዝኛለኹ፡፡
   ልብ የሚነካውና የሚያደማው ነገር የሐሰት ትምህርት ይህን ያህል እግር አውጥቶ ከመሮጡ ባሻገር፣ ወንጌልን ተረድተዋል ከሚባሉ አካላት ይህን ያህል ተከታይና ተሟጋች ማግኘቱ፣ ከዚህ ቀደም እንዳነሣኹት ይህን የፈጠጠ የሐሰት ወንጌል እየተመለከቱ ለእውነተኛው ወንጌል የጨከኑ ጥቂት ሰዎችን አለማግኘታችን ነው፡፡ በወንጌል ሕይወታቸው ድርድር አያውቁም የተባሉ ብዙዎች በበጋሻውና በዚህ የስህተት ትምህርት አቋማቸው ላሽቆና አሽቆልቁሎ መመሳሰልን የመረጡበት ኹኔታ ተስተውሏል፡፡
   የስህተት ትምህርትን ለመቃወም ማመቻመችና የጐንዮሽ ማፈግፈግ ባላስፈለገ ነበር፡፡ የስህተት ትምህርት በማንም ይተግበር በማን የስህተት ትምህርት አስተማሪው መመለሱን በአንደበቱ እስካልተናገረና ተግባራዊ የንስሐ ፍሬን በሕይወቱ ካላሳየ በቀር የሌሎች ስለእርሱ መሟገትና ጥብቅና መቆም በአደባባይ ከመታለል በቀር ምንም ምክንያት ልናቀርብለት አንችልም፡፡ እናውቃለን! የሐሰት መምህራን ተከታዮቻቸው አሸን ነው፤ በምድር ላይ ያሉት እነርሱና እነርሱ ብቻ ያሉ እስኪመስሉ ድረስ ምድርን ሊመሉ ይችላል፤ ግና ብቻውን አምላክ የኾነውን አምላክ እናመልካለንና፣ ከሥራችን ቸል አንልም፡፡
     ሳጠቃልለው፣ ሰዎች ለሐሰተኛ አገልጋዮች የሚሟገቱትን ያህል ለሞተላቸውና ላዳናቸው ጌታችን ኢየሱስ ከቅዱስ ቃሉ ማጥናትና ማስተዋል ቢጀምሩ በታላቅ መንፈሳዊ ባርኮት መባረክ እንደኾነ፣ ከኢየሱስ ባሕርይ ተነሥተውም አገልጋዮቹን ቢመለከቱ ምንኛ መሳሳታቸውን ባስተዋሉ ነበር፡፡ አዎን! በክርስትና ብዙ ተቃውሞ ሲያሳድግ እንጂ ሲያቀጭጭ አልታየም፡፡ ስለዚህም ዓረቦቹ እንደሚሉት፣ “ውሾቹ ይጮኻሉ ግመሎቹም ይኼዳሉ”፤ ተቃዋሚዎች ቢበረቱም፣ በክርስቶስ ደም ጉልበትና በመንፈስ ቅዱስ ኃይል “በፊታችን ያለውን ሩጫ በትዕግሥት እንሮጣለን፤” (ዕብ.12፥2)፡፡ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ሆይ! የዚህን ነገር ክብር ኹሉ አንተ ውሰድ፤ አሜን፡፡

   

8 comments:

  1. berta wendem difretehe yasdenekegal.

    ReplyDelete
  2. Tekawmo hulem ale satdenek berta

    ReplyDelete
  3. ሰዎች ለሐሰተኛ አገልጋዮች የሚሟገቱትን ያህል ለሞተላቸውና ላዳናቸው ጌታችን ኢየሱስ ከቅዱስ ቃሉ ማጥናትና ማስተዋል ቢጀምሩ በታላቅ መንፈሳዊ ባርኮት መባረክ እንደኾነ፣ ከኢየሱስ ባሕርይ ተነሥተውም አገልጋዮቹን ቢመለከቱ ምንኛ መሳሳታቸውን ባስተዋሉ ነበር፡፡ ewnet alk wedaje

    ReplyDelete
  4. አንተን ነህ በጋሻውን ነቃፊ፣ ቀሽም አላዋቂ ለቅላቂ ነገር ነህ።

    ReplyDelete
  5. berta Geta ejhn yabertaw.

    ReplyDelete
  6. abenezer bezih guday lay eyeserahew yalew sra ejg betam arif new.berta kegnihn yidegfew

    ReplyDelete
  7. begashaw tilahun10 January 2018 at 20:26

    Etopia wust endelidetu yenigigi chilota yalewn yahl yemastawsew begashaw deselegnn new.begashawn bewengel mastawes yikebdegnal.bzu srawochu bene eyta tru aydelum.Beta gn lib yistew.

    ReplyDelete