Tuesday, 27 May 2025

“ድንግል ማርያምን ሳትቀበል ጌታን መቀበል አትችልም!” [እውነት!?]

 Please read in PDF

ይህን ከላይ በርዕስነት የጠቀስኹትን ቃል የተናገረው ስሙር አላምረው ይባላል፤ ባልሳሳት “ሊቀ ሊቃውንት” የሚል ማዕረግ ያለው ይመስለኛል፡፡ ኦርቶዶክሳውያን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በድንግል ማርያም ዙሪያ የሚሰጡት “ትምህርትና ስብከት” ከመጽሐፍ ቅዱስ እውነት እያፈነገጠና መስመር እየሳተ ከመኾኑም ባለፈ፣ ድንግል ማርያምን ታክከው የክርስቶስን መካከለኝነት በትክክል መንቀፍ ደግሞ የአደባባይ እውነት ኾኖአል፡፡


ጌታን ከመቀበል ድንግል ማርያምን መቀበል ይቀድማል ለማለት፣ “ሊ      ቀ ሊቃውንቱ” የጠቀሰው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ማቴ. 10፥40 ላይ የተጠቀሰውን “እናንተን የሚቀበል እኔን ይቀበላል፥ እኔንም የሚቀበል የላከኝን ይቀበላል።” የሚለውን ነው፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ይህን የተናገረው ለደቀ መዛሙርቱ ነው፡፡ ክፍሉም የሚናገረው ስለ ሐዋርያዊ ተልእኮ ነው፡፡

ሙሉውን ምዕራፍ አሥርን የተመለከትን እንደ ኾን፣ ኢየሱስን የሚያሳድዱ ሰዎች የርሱንም ደቀ መዛሙርት እንደሚያሳድዱና መከራ እንደሚያደርሱባቸው ኹሉ፣ ኢየሱስን የሚቀበሉ ሰዎች የርሱንም ደቀ መዛሙርት ይቀበላሉ፤ በመምህሩ ላይ የደረሰ ነገር ኹሉ በደቀ መዛሙርቱም ላይ እንደሚደርስ በርግጠኝነት የሚናገር ክፍል ነው፡፡

ደቀ መዛሙርቱ የኢየሱስን ወንጌል ለማስተማር ወደየትኛውም የምድር ክፍል ሲሄዱ፣ እነርሱን ተቀብሎ የሚያስተናግድ ማንኛውም ሰው ክርስቶስን እንዳስተናገደ ይቈጠራል፡፡ ክርስቶስንም ስንቀበል እግዚአብሔርን ተቀብለን ማስተናገዳችን ነው፡፡ አንድን ደቀ መዝሙር ወይም ነቢይ ወይም አገልጋይ በክርስቶስ ስም ተቀብለን የምናደርግለት ማናቸውም ነገር ትንሽ ሥራ ኹሉ ለክርስቶስ እንዳደረግነው ይወሰዳል፡፡ በአጭር ቃል፣ ለጌታ እውነተኛ አገልጋዮች የተደረገው እዚህ ግባ የማይባል የሚመስል የደግነት ሥራ (አንድ ብርጭቆ ቀዝቃዛ ውኃ) በእግዚአብሔር ዓይን ትርጉም አላቸው ማለት ነው።

ደቀ መዛሙርቱን የምንቀበልበት ዋናው ምክንያታችን፣ እኒህ ደቀ መዛሙርት የተሰቀለውን ክርስቶስን በመስበካቸው ምክንያት በመላው ዓለም የተጠሉና ስዱዳን ናቸው፤ ዓለም ዘወትር ልታጠቃቸው ታሸምቅባቸዋለች፡፡ ስለዚህም እኒህን የጌታን ወዳጆች የሚቀበል ኹሉ ጌታን እንደ ተቀበለ ይቈጠርለታል፡፡

ነገር ግን ይህ ክፍል፣ ድንግል ማርያም ካልተቀበላችሁ በቀር ክርስቶስን መቀበል አትችሉም የሚል ዐውዳዊ ፍቺ ፈጽሞ የለውም፡፡ ቅዱሳት መጻሕፍት ጌታን ለመቀበል ማርያምን ጨምሮ ከፊት ያስቀመጡት ሌላ አንዳች ግለሰብ የላቸውም፡፡ እኒህ የቅዱሳት መጻሕፍት ምንባባት ዋቢ ናቸው፣

ለተቀበሉት ሁሉ[ክርስቶስን] ግን፥ በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው፤” (ዮሐ. 1፥12)

“ኢየሱስ ጌታ እንደ ሆነ በአፍህ ብትመሰክር እግዚአብሔርም ከሙታን እንዳስነሣው በልብህ ብታምን ትድናለህና፤” (ሮሜ 10፥9)

“ይህንም በሰሙ ጊዜ ልባቸው ተነካ፥ ጴጥሮስንና ሌሎችንም ሐዋርያት፦ ወንድሞች ሆይ፥ ምን እናድርግ? አሉአቸው።ጴጥሮስም፦ ንስሐ ግቡ፥ ኃጢአታችሁም ይሰረይ ዘንድ እያንዳንዳችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ፤ የመንፈስ ቅዱስንም ስጦታ ትቀበላላችሁ።” (ሐ.ሥ. 2፥37-38)

“በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ እመን አንተና ቤተ ሰዎችህ ትድናላችሁ” (ሐ.ሥ. 16፥31)

እኒህና አያሌ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ክርስቶስን ብቻ ስለ መቀበል የሚመሰክሩ ናቸው፤ ኢየሱስ ክርስቶስን መቀበል ማለት የዘላለም ሕይወትና ዕረፍትን መቀበል ማለት ነው፤ በርሱ ማመን፤ ለርሱ መታመንም ማለት ነው፡፡ የደቀ መዛሙርት ኹሉ ስብከት “ጌታን ኢየሱስን ተቀበል!” እንጂ በእኔ በኩል ወይም በማርያም በኩል ካልተቀበልኽ ክርስቶስን አታገኘውም የሚሉ አልነበሩም፤ ይህን ማለት ነውርና ኑ-ፋ-ቄ ነው!

“ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን በማይጠፋ ፍቅር ለሚወድዱ ሁሉ ጸጋ ይሁን።” (ኤፌ. 6:24) አሜን።

5 comments:

  1. ኣንተ ወንድሜ ያለ ማርያም ሰላም የለም ።ምክንያቱ ማርያም ድንግል ወላዲተ ኣምላክ ናት።ኣምላክ ደግሞ ፈጣሪያችን፣ኣባታችን ፣ፈራጅ ገዢ ነው ስለዚ ኣባት ከለ እናት ኣለች እናት ካለች ኣባት ኣለ ስለዚ ጌታችን መድሓኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ተሰቅሎ ሳለ ንወንጀላዊ ቅዱስ ዮሓንስ እኖሆ እናትህ ብሎ ቤዛዊተ ዓለም ድንግል ማርያም ን ሰጠን።

    ReplyDelete
  2. አንተ ጴንጤ ነህ አታምንበት ለማሳሳት ካልሆነ በቀር!

    ReplyDelete
  3. አምልኮተ ማርያም ብለህ ትዋሻለህ አንተ ውሸታም

    ReplyDelete
  4. እውነተኛ አምላክ ብቻ የሆንክ አንተን❤ የላክኸውንም❤ ያውቁ ዘንድ ይህቺ የዘላለም ህይወት ናት!! ዮሀንስ17:3❤❤❤

    ReplyDelete
  5. ሲጀመር ክርስቶስ ሁለተናችን ነዉ እመቤታችን እናታችን ናት እናከብራታለን እንወዳታለን እንታዘዛታለን ምክንያት ብትለኝ ክርስቶስ የደቀመዛሙርቱን እግር ካጠበ አንተ ማነህና ነገር ግን እናትና ልጅን አታወዳድሩ ያስጠላል አንዱን ባንዱ ቦታ ለማስገባት አት ሞክሩ አወ እመቤታችን ታማልዳለች ክርስቶስ እራሱ ያማልዳል ያለ እመቤታችን ጽድቅ የለም ብትለኝ አልቀበልም ሲጀመር ክርስቶስ ሰዉን ወደራሱ ያቀርባል ይቅር ይላል ያለ ጻድቃን አማላጅነት ብትለኝ አንተ ክርስቶስ አልገባህም

    ReplyDelete