“… በየትኛውም ቋንቋ የተጻፈ መጽሐፍ ቅዱስ አከራካሪ ነገር ከተነሳበት፣ አስታራቂው በግሪክ የተጻፈው
መጽሐፍ ቅዱስ ነው። አዲስ ኪዳን በመጀመሪያ የተጻፈው በግሪክ ስለ ኾነ። ግሪኩ “በአብ ቀኝ ያለው ስለ እኛ የሚማልደው” ካለ፣
“የሚማልደው” ማለት ምን ማለት ነው? የሚለውን ማብራራት፤ መተርጐም ነው እንጂ ቃሉን ቀይሮ “ይፈርዳል” ማለት ምን ማለት
ነው? … ለምን ተቀየረ? ብሎ መጠየቅ ደግሞ መብቴ ነው … ቃል ቀይሮ መሸሹስ የት ያደርሳል? … ይህ ቢቀየር እኮ ዕብራውያን፣
ቅዳሴ፣ ሃይማኖተ አበው ስንት ቦታ አለ? … ከመሸሽ መተርጐም ይሻላል … ስንቱንስ ቀይረህ ትችለዋለህ? … ”
“ … የብሉይ ኪዳን ካህናት የበግ ደም ይዘው ነው የሚቀርቡት፤ ጌታ ግን ራሱ መሥዋዕት ኾኖ ነው
የቀረበው። … ኹል ጊዜ ኢየሱስን ስናይ ሰውም አምላክም መኾኑን መዘንጋት የለብንም። … በሰውነቱ ሊቀ ካህናት ኾኖ
ይጸልያል፤ ወደ አባቱ። ወደ አባቱ ሲጸልይ እንቢ የማይባል ጸሎት ነው የሚጸልየው፤ ምክንያቱም ያለ ኀጢአት የተገለጠ ሊቀ
ካህናት ነውና፣ ደግሞም ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር በአምላክነቱ ጩኸት ሰሚ ነውና። … እናም በሰውነቱ ይለምናል … መለመን
እንዲችል ያደረገው ሰውነቱ ነው። … ”
“… እግዚአብሔር ሰውን ሲፈጥር አንድ ጊዜ “ብዙ ተባዙ” በማለቱ በኃያል ቃሉ እስከዛሬ ድረስ
ይፈጥራል፤ የክርስቶስም የማስታረቅ ሥራ እንዲኹ ነው።..” (አባ በርናባስ)
ምናልባት “የእግረኛው ሚዲያ - ተይዞ የነበረው ቪዲዮ ተለቀቀ” ሲል፣ ሲኖዶስ የአባ በርናባስን ጉዳይ
ከአባ ገብርኤልና ፊልጶስ ጋር እንዲታይ ውሳኔ በሰጠበት ጊዜ መኾኑ፣ “የአባ በርናባስን ጉዳይ በዚህ ንግግራቸው ለማጋጋልና
ለውግዘት ተጣድፈው እንዲቀርቡ ለማድረግ” ዐስቦ ሊኾን ይችላል። በመግቢያውም ላይ “ይህ ቪዲዮ እንዳይወጣ ብለውኝ ነበር” ብሎ
የማቅረቡ ምክንያቱም ይኸው ይመስለኛል። ይህ ስውር ዐሳቡ ግን ያን ያህል ሚዛን የሚያነሳለት አይመስለኝም። ምክንያቱም
ጳጳሱ ከአቋማቸው ፍንክች አላሉምና።
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ከተነሱ አባቶች መካከል፣ ስለ ክርስቶስ አስታራቂነት በዚህ ልክ ደፍሮ የተናገረ
አባት ወይም ጳጳስ ስለ መኖሩ እርግጠኛ አይደለሁም። በተለይም ደግሞ “የክርስቶስን አስታራቂነት ለመቀበል” እጅግ አዳጋች
በኾነባትና የሚያስወግዝ በኾነባት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንዲህ መናገር ከመንፈስ ቅዱስ በቀር ማንም ሊያስጨክን አይችልም።
አቡነ በርናባስ ያተኰሩባቸው ነጥቦች፦
-
ደሙ ዛሬም ትኩስ ነው፣
-
ክርስቶስ ዛሬም በሊቀ ካህናትነቱ ያስታርቃል፣
-
አንዴ በመስቀል ላይ የሠራው ሥራው ሕያውና
ዛሬም ድረስ የማያቋርጥ ነው፣ ይህን ሲያስረግጡም፣ “አስታርቆአል፤ እያስታረቀ ነው፤ ሲያስታርቅ ይኖራል ማለት ምኑ ነው ነውሩ?”
ይላሉ።
አዎን፤ መጽሐፍ ቅዱስ፣ አንድ ጊዜ ለዘለዓለም የሚያገለግል የሚሻል መሥዋዕት ክርስቶስ ስለ ማቅረቡ ይመሰክራል
(ዕብ. 9፥23)፤ ስለዚህ ምዕመናንና ምዕመናት የሚሻል ተስፋ አላቸው (ዕብ. 7፥18-19)፤ አሁንም ለዘለዓለም የሚኖር ሊቀ ካህናታችን
በእግዚአብሔር ቀኝ በክብርና በባለ ሥልጣንነት ተቀምጦ ለሕዝቡ ይገኛልና በርሱ ወደ እግዚአብሔር የሚመጡትን ፈጽሞ ሊያድናቸው ይችላል፤
(ዕብ. 2፥18፤ 4፥14-16፤ 7፥24-25)።
ሰው የኾነበትም ዋነኛ ዓላማውም ይኸው እንደ ኾነ አበክሮ ይናገራል፡፡ አሮናውያን ሊቃነ ካህናት ዋና ሥራቸው
የነበረው ስለ ኀጢአት መሥዋዕትን ማቅረብ ነበር (ዕብ. 5፥1፤ 10፥11)፡፡ ይህን ለማድረግም ደምን ያፈስሱ ነበር (ዕብ. 9፥7)፤
ነገር ግን አገልግሎታቸው በሞት የተገታና ኀጢአትን ለጊዜያዊነት እንጂ ጨርሶ ማስወገድ ያልቻለ ነበር፡፡ ክርስቶስ ግን ጳጳሱ እንደ
ተናገሩት የራሱን ደም አቀረበ (ዕብ. 7፥26፤ 9፥12፤ 10፥2)፤ በዚህ አገልግሎቱም የብሉይ ኪዳን ካህናትን አገልግሎት ኹሉ
አስቀረ ወይም ሻረ (ዕብ. 7፥18-19)። ከዚህም የተነሣ ጌታችን ክርስቶስ በእግዚአብሔር ቀኝ የሚገኝ በመኾኑ ሕዝቡን እየረዳ
እስከ መጨረሻ ሊያድናቸው ይችላል (2፥18፤ 4፥16፤ 5፥9-10፤ 7፥24-25)።
የአባ በርናባስ የምስክርነት ድፍረት በሌሎችም ጳጳሳት እንዲጋባ እንናፍቃለን። ይህን በምትሰሙና በምታነብቡ
ኹሉ ላይ ጸጋና ሠላም በክርስቶስ ኢየሱስ ይብዛላችኹ፤ አሜን።
ገና ብዝዎች በበጉ ዙፋን ፊት ይመጣሉ አሜን
ReplyDeleteእውነት ነው የዘመናት እውነት ሊደበቅ አይችልም 🎉🎉🎉🎉❤❤❤❤ ጌታ ኢየሱስ ይባረክ ፀጋው ያብዛላቸው🎉🎉🎉
ReplyDelete