እግዚአብሔር፣ ኀጢአትን እንደሚጠየፍ በግልጥ ከተናገረባቸው
የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች መካከል አንዱ ክፍል ይህ ነው። ጠቢቡ የገለጣቸው ስድስት ኀጢአቶች በፍጻሜያቸው፣ መለያየትና ግጭት ብሎም
ወንድሞች እንዳይቀባበሉ የሚያደርግ ኀጢአት እንደ ኾነ መረዳት እንችላለን። በወንድሞች መካከል ጠብን ለማነሣሣት ወይም ለመዝራት
አስቀድሞ ሐሰተኛ ምላስ ትዋሻለች፤ መዋሸቷ ብቻ ሳይኾን ጠብን ለመጫር ሌሎችንም ማታለሏ አደገኛ ያደርታል።
አስተውሉ፣ "መዝራት" የሚለው ቃል፣ ከእርሻ ተግባር ጋር ተመሳሳይነት አለው። ይህም "ጠብን የሚዘሩ" ድርጊቱን ኾን ብለው በዓላማ የሚያደርጉ መኾናቸውን ያመለክታል። ሰዎች ጠብን ሲዘሩ፣ ዐላማቸው በትክክል ግቡን እንዲመታ እንደ ተራ አሉባልታ፣ ስም ማጥፋት፣ ሐሜት፣ የሐሰት ወሬ፣ ማንሾካሾክ፣ ተራ ትችትና ንቀትን እንዲኹም ግብዝነትና ሽንገላን እንደ መሣሪያነት ይጠቀማሉ። የእነዚህ ዘሮች ውጤቱ ወይም ቡቃያው ጠብና መለያየት፤ ግጭትና ጥላቻ ነው። እንዲህ ያለ ኀጢአት ስልና እጅግ አደገኛ ደግሞም ውስብስብ ነው።
በሰዎች፤ በአገልጋዮችና በአገልግሎቶች መካከል አለመግባባት
እንዲመጣና ኅብረት እንዲናድ ወይም እንዲበላሽ፣ ሳይታክቱ መሥራት እግዚአብሔር ከሚጠየፋቸው ኀጢአቶች ዋነኛው ነው። እግዚአብሔር
ከርሱ ጋር እንድንኾን የሚፈልገውን ያህል፣ ከሌሎችም ጋር እንድንኾን ይሻል። ጠቢቡ ሌሎችን የሚጎዱትን ኀጢአቶች የምንሠራባቸውን
አካላቶቻችንን ይገልጣቸዋል። "ትዕቢተኛ ዓይን፥ ሐሰተኛ ምላስ፥ ንጹሕን ደም የምታፈስስ እጅ፥ ክፉ አሳብን የሚያበቅል ልብ፥
ወደ ክፉ የምትሮጥ እግር፥" በማለት።
አማኞች እኒህን ብልቶቻቸውን፣ "...የዓመፃ
የጦር ዕቃ አድርገው ለኃጢአት እንዳያቀርቡ፥ ነገር ግን ከሙታን ተለይተው በሕይወት እንዲኖሩ ራሳቸውን ለእግዚአብሔር እንዲያቀርቡ፥
ብልቶቻቸውንም የጽድቅ የጦር ዕቃ አድርገው ለእግዚአብሔር ማቅረብ እንደሚገባቸው" ይናገራል፤ (ሮሜ 6፥13)።
እንዲኹም፣ አማኝ ከአማኝ ጋር ግንኙነቱ የርስ በርስ
ነው፤ በንግግሩና በድርጊቱ ለሌላው ሊጠነቀቅም ይገባዋል። እግዚአብሔርም ከሌሎች ኹሉ ጋር ጤናማ ግንኙነት እንዲኖረን ይሻል። ሌሎችን
በመበደል የምንሠራው ኀጢአት፣ ከባድና አሰሰጨናቂ ነውና።
አንዳንዶች "ወንድሞች ሆይ፥ እናንተ የተማራችሁትን
ትምህርት የሚቃወሙትን መለያየትንና ማሰናከያን የሚያደርጉትን ሰዎች እንድትመለከቱ እለምናችኋለሁ፥ ከእነርሱ ዘንድ ፈቀቅ በሉ፤"
(ሮሜ 16፥17) እንደ ተባለው፣ መለያየትን የሚያደርጉት እንግዳ ትምህርት በማስተማር ነው። ሌሎች ደግሞ በቅንአትና ረብ የለሽ
በኾነ ሥጋዊ ክብርና ምድራዊ አመኔታን ለማግኘት ከመጎምጀት ነው።
"ታማኝ ምስክር" የተባለውን ኢየሱስን
(ራእ. 1፥5) ኹለት ምስክሮች በሐሰት እንደ መሠከሩበት አንዘነጋም (ማቴ. 26፥60)። ቅዱስ ጳውሎስም "በውሸተኞች ወንድሞች
በኩል ፍርሃት ነበረብኝ፤" (2ቆሮ. 11፥26) በማለት መናገሩን። ጌታችን ኢየሱስን በሐሰተኛ ምስክሮች እንደ ሰቀሉት፣
ቅዱስ ጳውሎስንም ሐሰተኛ ወንድሞች ከማስፈራት በዘለለ፣ በአገልግሎቱ ላይ እንዴት አስቸጋሪዎች እንደ ነበሩ እንደ ገላትያ ካሉ መልእክቶቹ
ማስተዋል እንችላለን።
ከሐሰተኛ ምላስና ጠብን በወንድሞች መካከል ከሚዘሩ
ሸንጋዮች ተጠበቁ፤ ተጠንቀቁ።
No comments:
Post a Comment