Monday, 26 May 2025

ይሁዳና የሌሊት መንገዱ!

 Please read in PDF

ይሁዳ ወዲያው ወጣ፤ ሌሊትም ነበረ።” (ዮሐ. 13፥30)

ጌታችን ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ መካከል በአንዱ፣ ተላልፎ እንደሚሰጥ፣ “እንጀራዬን የሚበላ በእኔ ላይ ተረከዙን አነሣብኝ ያለው ይፈጸም ዘንድ” (ዮሐ. 13፥18-21) በማለት ከትንቢት ጠቅሶ ተናግሮአል። ጌታችን ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ መካከል ወደ ደረቱ ተጠግቶ ለጠየቀው ሐዋርያ፣ “እኔ ቍራሽ አጥቅሼ የምሰጠው እርሱ ነው ብሎ” መልሶአል፤ (ቊ. 26)። ይሁዳ እጅግ በሚያሳዝን መልኩ፣ ጌታችን ኢየሱስ ነገረ ሥራውን ኹሉ እንዳወቀ ባረጋገጠለት ጊዜ፣ “… ወደ ካህናት አለቆች ሄዶ፦ ምን ልትሰጡኝ ትወዳላችሁ እኔም አሳልፌ እሰጣችኋለሁ?” (ማቴ. 26፥14-15) ባለበት ቅጽበት፣ በሰይጣን ቊጥጥር ሥር ዋለ፤ “ቍራሽም ከተቀበለ በኋላ ያን ጊዜ ሰይጣን ገባበት” (ዮሐ. 13፥27) እንዲል።

ደቀ መዛሙርቱ ግን ኢየሱስን አሳልፎ ስለሚሰጠው ሰው፣ ልዩ ምልክት ሰጥቶአቸው እንኳ፣ አለማስተዋላቸውና መሳሳታቸው ቀጣዮቹ ንባባትን ስናነብ እጅግ እንደነቃለን።

ይሁዳ፣ ጌታን አሳልፎ ሊሰጥ የወጣበትን ሰዓት ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ ሲናገር፣ “ቍራሹን ከተቀበለ በኋላ ወዲያው ወጣ፤ ሌሊትም ነበረ።” ይለናል (ቊ. 30)፤ “ሌሊትም ነበረ” የሚለው ቃል፣ ጊዜን ለማመልከት ብቻ በወንጌሉ ውስጥ እንዳልተጠቀሰ፣ ከቅዱስ ዮሐንስ ወንጌልና ከመልእክቶቹ ጠቅላላ ንባባት መረዳት እንችላለን። በዮሐንስ ወንጌል ንባባት ውስጥ፣ “ብርሃን” ሕይወትን፣ እውነትን፣ … ሲወክል፣ “ጨለማ ወይም ሌሊት” ደግሞ መጥፋትን፣ ሞትን፣ … የሚያመለክት ኾኖ እናገኘዋለን።

“የሰው ልጅ አልፎ ለሚሰጥበት ለዚያ ሰው ወዮለት፤ ያ ሰው ባልተወለደ ይሻለው ነበር” (ማር. 14፥21) በሚለው ንግግር ውስጥም፣ ይሁዳ በፈቃዱ ዘላለማዊ ጥፋትን መርጦ መሄዱን እናስተውላለን። የይሁዳ ወደ ሌሊት የመውጣት ምሳሌነቱም ይህን ይበልጥ ያረጋግጥልናል፤ ይሁዳ በተደጋጋሚ ተዘለፈ፤ ነገር ግን ሊመለስ ስላልወደደ አንገቱ ያለ ፈውስ ተሰብሮ ቀረ፤ (ምሳ. 29፥1)።

ጌታችን ስለ ይሁዳ ሲናገር እጅግ በተሰበረ ልብ ኾኖ ነው፤ ይሁዳ ግን የሰፋውንና የበዛውን የእግዚአብሔርን ምሕረት በተደጋጋሚ ገፋ። በገንዝብ ፍቅር ተታልሎ የመልካም ነገሮች ኹሉ ምንጭ ከኾነው ጌታ ፈቀቅ ማለቱ እጅጉን ይደንቃል። ከእጁ በልቶ፤ ከመግቦቱ ቆርሶ ነገር ግን ተረከዙን በጌታው ላይ አነሳ። ብርሃን የኾነውን ኢየሱስን ትቶ ጨለማ የኾነውን ኀጢአትን ወድዶ ሄደ። ቸኩሎ ቦርሳውን አንግቶ፣ ወደ አስፈሪውና አሰቃቂው የሞት ጥላ ውስጥ ራሱን ዘፈቀ።

በእግዚአብሔር አምላክ የዘላለም ዕቅድ ውስጥ ግን የይሁዳ መሰናበት ግድ ነበረ፤ ይሁዳ እንደ ወጣ ጌታችን ኢየሱስ እንዲህ አለ፣ “ … አሁን የሰው ልጅ ከበረ እግዚአብሔርም ስለ እርሱ ከበረ፤እግዚአብሔር ስለ እርሱ የከበረ ከሆነ፥ እግዚአብሔር ደግሞ እርሱን ራሱን ያከብረዋል ወዲያውም ያከብረዋል።” (ቊ. 31-32)።

የክርስቶስ መሥዋዕታዊ ሞት በዮሐንስ ወንጌል ውስጥ የተገለጠው ዕድገትን በሚያሳይ መልኩ ነው፤ “ጊዜዬ ገና አልደረሰም” (2፥4፤ 7፥30፤ 8፥20) እያለ ይሄድና፣ እያየን ባለነው ክፍል ግን “የሰው ልጅ ይከብር ዘንድ ሰዓቱ ደርሶአል።” ይላል፤ ስለዚህ የይሁዳ በሰይጣን ቊጥጥር ሥር መኾንና የኢየሱስን ብርሃንነት መግፋት የክርስቶስን የመጣበትን ዋነኛ ዓላማ ማለትም የሞቱን ጊዜ ፈጽሞ ያፋጥነዋል።

በአንድ በኩል ሲታይ፣ ክርስቶስ ወደ ሞት እየሄደ ይመስላል እንጂ፣ እየገሰገሰ ያለው ወደ ፍጹም ክብር ነው። መስቀልና ክብር፤ ሞትና ትንሣኤ ፈጽሞ ሊነጣጠሉ አይችሉምና። በርግጥ የክርስትና አንዱ ማዕከላዊ ትምህርት ያለው እዚህ ጋ ነው። ሰው የኾነው አምላክ፣ በሰው ልጆች እጅ አሰቃቂ መከራ ይቀበላል በዚህም የሰው ልጆች ዕዳ ኹሉ ይከፈላል፤ ርሱም ደግሞ ፍጹም ይከብራል የሚለው ትምህርት ለአይሁድ ማሰናከያ ለአሕዛብ ደግሞ ሞኝነት ኾኖ ነው። እግዚአብሔር በዚህ መክበሩ፤ ለሰው ልጆችም ደግሞ ምሕረትና ፍትሕ መረጋገጡ እጅግ ይደንቃል። እግዚአብሔር የይሁዳን የጨለማ ጉዞ ለክብሩ ለወጠው፤ ሉዓላዊ ነውና!

“ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን በማይጠፋ ፍቅር ለሚወድዱ ሁሉ ጸጋ ይሁን።” (ኤፌ. 6:24) አሜን።

 

1 comment:

  1. That's what we pass eko Orthodox church passes all of her pains including you.

    Dude starting form period of Apostles upto now we saw thousands of enemies ....we pass all of them ...and you are nothing relative to what we already pass ok

    ReplyDelete