መጽሐፍ ቅዱስ ቃል በቃል ስለ ስብከት ሲናገር፣ “እኛ ግን የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን፤”
(1ቆሮ. 1፥23) ይላል። ይህ ክርስቶስን የቀመሱትና አምነው በነፍስ ተወራርደው የሚከተሉት ኹሉ፣ በቃልም በሕይወታቸውም
የሚመሰክሩት ነው። ለዚህም ነው፣ “ኢየሱስ ጌታ እንደ ሆነ በአፍህ ብትመሰክር እግዚአብሔርም ከሙታን እንዳስነሣው በልብህ
ብታምን” የሚለው ቃል የመዳን መሠረት ኾኖ የተቀመጠው፤ (ሮሜ 10፥9)።
ስብከት ግልጥ ምስክርነት ነው፤ “አድኖኛልና
እናንተም ዳኑ” የሚል ጥልቅ መልእክትን በውስጡ የያዘ ነው፤ የሰማርያ ሰዎች በኢየሱስ ያመኑትና ከእነርሱ ጋር እንዲኖር
የለመኑት ሳምራዊቷ ሴት፣ “ያደረግሁትን ሁሉ ነገረኝ ብላ ስለ
መሰከረችው ቃል” ነው፤ (ዮሐ. 4፥39) እንዲሁም ትሁቱ ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ፣ በክርስቶስ አምኖ የተጠመቀውና የዳነው፣
“ፊልጶስም አፉን ከፈተ፥ ከዚህም መጽሐፍ ጀምሮ ስለ ኢየሱስ ወንጌልን ሰበከለት” ከተባለ በኋላ ነው፤ (ሐ.ሥ. 8፥35)።
ስብከትና ሕይወት፤ ሕይወትና ስብከት
ሊነጣጠሉ አይችሉም። ሰባኪውም ተሰባኪውን ሕይወታቸው ከኢየሱስና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ካልተነካካ በቀር፣ ስብከት ነፋስን
የመጎሰም ያህል ከንቱ ነው። በሌላ ንግግር የሚሰብከው ሰው፣ ከቃሎቹ ይልቅ በሕይወቱ ሊሰብክ ይገባዋል፤ ጌታችን ኢየሱስ “እናንተ
በቃሌ ብትኖሩ በእውነት ደቀ መዛሙርቴ ናችሁ፤” (ዮሐ. 8፥31) በሌላ ስፍራም፣ “እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ፥ ደቀ
መዛሙርቴ እንደ ሆናችሁ ሰዎች ሁሉ በዚህ ያውቃሉ።” (ዮሐ. 13፥35) እንዲሁም፣ “ብዙ ፍሬ ብታፈሩና ደቀ መዛሙርቴ ብትሆኑ
በዚህ አባቴ ይከበራል።” (ዮሐ. 15፥8) ሲል፣ ትምህርቶች ውስጥ ፍሬና ሕይወት ተያያዥ፤ አልፎም ለሌሎች ብርቱ መልእክት
ያለው መኾኑን ያሳያል።
ጌታችን ኢየሱስ ስለ ጨውና ብርሃንም
ባስተማረበት ክፍሉ፣ “መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ እንዲሁ በሰው ፊት
ይብራ።” (ማቴ. 5፥16)፣ “በነፍሳችሁ ጨው ይኑርባችሁ፥ እርስ በርሳችሁም ተስማሙ።” (ማር. 9፥50) ብሎ ሲናገርም፣ ሰዎች
ከስብከታችን በላይ ሕይወታችንን ጭምር እንደሚመለከቱና የሕይወታችን ጤናማነት የስብከታችንን ኃይልና ጥራት ከፍ እንደሚያደርገው
ተናግሮአል።
ስለዚህ ክርስቲያን ከዳነ መዳኑን፣
ከተማረ ምሕረቱን፤ ይቅር ከተባለ ይቅርታውን ሊያወራ ተጠርቶአል፤ የዳንንበትን እውነት በውክልና እንድናወራ አልተጠራንም፤
በምሳሌም እንድንመሰክር አልተባለም፤ ምክንያቱም በምሳሌና በጥላ የሚነገርበት የብሉይ ኪዳን ዘመን አልፎአልና፤ አኹን አዲስ
ዘመን፤ አዲስ ኪዳን ነው፤ ኢየሱስ በከበሮና በጸናጽል፤ በመቋሚያና በበገና ክሮች ምሳሌነት አይሰበክም፤ በምንናገረውና በመንፈስ
ቅዱስ ኃይል በሚሠራው በቅዱስ ቃሉና በቃሉ ብቻ እንደሚሠራ እናምናለን።
የተሰቀለውን ክርስቶስ ኢየሱስን በትክክል
የምትወዱትና የምትከተሉት ከኾነ፣ “ሐዋርያትም የጌታን የኢየሱስ ክርስቶስን ትንሣኤ በታላቅ ኃይል ይመሰክሩ ነበር፤” (ሐ.ሥ.
4፥33) ተብሎ እንደ ተጻፈው፣ ልክ እንደ ሐዋርያት አበው በአንደበታችሁ መስክሩለት፤ “ከኢየሱስም ጋር እንደ ነበሩ
አወቁአቸው፤” (ሐ.ሥ. 4፥13) ተብሎ እንደ ተጻፈውም በሕይወታችሁ አውጁት፤ በከበሮና በጸናጽል ምሳሌነት፤ በጉልላትና በነጠላ
ጥለት በማለት አትሸፍኑት!
ቃሉ ከከበሮ፤ መንፈሱም ከጸናጽል
ይበልጣልና! ኢየሱስን በሚበልጠው ቅመሱትና ወድዳችሁ ስበኩት!
መጽሐፍ እንደሚል፣ “እግዚአብሔር ቸር
እንደ ሆነ ቅመሱ እዩም፤ በእርሱ የሚታመን ሰው ምስጉን ነው።” (መዝ. 34፥8)
“ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በማይጠፋ ፍቅር ለሚወድዱ ሁሉ ጸጋ ይሁን።” (ኤፌ. 6፥24) አሜን።
ጆሮ ያለው ሰማይና ምድር በመፀሀፍ ቅዱስ ውስጥ?😂😅
ReplyDeleteእግዚአብሔር ተናግሮአልና #ሰማያት_ስሙ፥ #ምድርም #አድምጪ፤ ልጆችን ወለድሁ አሳደግሁም፥ እነርሱም አመጹብኝ።”
— ኢሳይያስ 1፥2“
ከመቼ ዲህ ነው ሰማይና ምድር መስማት የጀመረው??😂
እጅ ያላቸውና የሚያጨበጭቡ ወንዞች የሚደሰቱ ሐሴትን የሚያደርጉ ተራሮች😂😅#ወንዞችም_በአንድነት_በእጅ_ያጨብጭቡ፤ #ተራሮች_ደስ_ይበላቸው፥ በምድር ሊፈርድ ይመጣልና።”
— መዝሙር 98፥8“
እንደ ጥጃ የሚዘሉ ተራሮች
ተራሮች እንደ ኮርማዎች፥ ኮረብቶችም እንደ ጠቦቶች ዘለሉ።”
— መዝሙር 114፥4“
ቅዱስ ዳዊት ተራሮችን አነገገራቸው😂😂
እናንተም ተራሮች፥ እንደ #ኮርማዎች_ኮረብቶችስ፥ እንደ ጠቦቶች ለምን ዘለላችሁ?”
— መዝሙር 114፥6
መቼም ዘይቤያዊ ንግግር መሆኑ ለማንም አይጠፋው ችግሩ የአገሬው ጴንጤ መፀሀፍ ቅዱስን የሚያነበው የጌታን ቤተክርስቲያን ለመቃወምና ለመንቀፍ ነው ይቺን(😂) የተጠቀምኩትም በቅዱስ ቃሉ ሳይሆን ቅዱስ ቃሉን ረጋግጠው በራሳቸው ሐሳብና ምኞት እየተነዱ እንደ ጨው ዘር ብትንትናቸው ለወጣ አንዱ ከአንዱ ለማትስማሙት ነው የክርስቶስን ቤተክርስቲያን ለመቃወም ስትፈልጉ ብቻ ትስማማላችሁ
አምልኮ ስግደት የሚገባው ሁሉን ለፈጠረው እግዚአብሔር ብቻ ነው
ReplyDelete