Tuesday, 20 May 2025

የተዘነጋው የመዳናችን ክፍል!

 Please read in PDF

“እነዚህ ነገሮች የሌሉት ዕውር ነውና፥ በቅርብም ያለውን ብቻ ያያል፥ የቀደመውንም ኃጢአቱን መንጻት ረስቶአል።” (2ጴጥ. 1፥9 - 1954)

እነዚህ ባሕርያት የሌሉት ግን የሩቁን የማያይ ወይም ዕውር ነው፤ ከቀድሞው ኀጢአቱ መንጻቱንም ረስቷል።” (ዐመት)

መጽሐፍ ቅዱስ “በክርስቶስ ኢየሱስ ላሉት አሁን ኵነኔ የለባቸውም” (ሮሜ 8፥1)፣ “ማንም በክርስቶስ ቢሆን አዲስ ፍጥረት ነው፤” (2ቆሮ. 5፥17) ብሎ መናገሩ የታመነና የተረጋገጠ ሕያው እውነት ነው። ስለ መዳናችን በኀላፊ ንግግር ስንናገር እኒህ ኹለቱን መናገር እንችላለን፣ (1) ድነናል (ኤፌ. 2፥8፤ ቲቶ 3፥6-7፤ ሮሜ 3፥24፤ 8፥24፤ 9፥30)፣ (2) ተቀድሰናል (ሮሜ 6፥24-25፤ 1ቆሮ. 1፥12፤ 6፥11፤ ዕብ. 10፥10፡ 14፤ 1ጴጥ. 2፥24)።

ጌታችን እግዚአብሔር በክርስቶስ ኢየሱስ በሠራልን ሥራ፣ ያዳነንና የቀደሰን ደግሞ እንዲያው በጸጋው በታላቅ ፍቅሩና ከማያልቀው ርኅራኄው የተነሣ ነው (ዮሐ. 3፥16፤ ሮሜ 11፥6፤ ኤፌ. 2፥4፡ 9፤1ጴጥ. 1፥3-5)። እናም ብዙ የተተወልንና ብዙ ይቅርታ ያገኘን ነንና፣ እጅግ አብዝተን ልንወድደው፤ ልንታዘዘውም ይገባናል፤ (ሉቃ. 7፥47) በሌላ ንግግር ወዶ ገብ ባሪያዎች፤ የፍቅር ተገዢዎች ነን፤ ቀድሞ የተተወልን እንጂ በብቃታችን እንድንመላለስ የተባልን አይደለንም፤ የዳንነውም፤ ድነን የምንኖረውም በክርስቶስ ኢየሱስ ጸጋ ብቻ ነው።

የዳነ አማኝ ይህን ፈጽሞ ሊዘነጋ አይገባም፤ የእስራኤል ዘሥጋ ትልቁ ችግር ይህ ነበር፤ “ … በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት በኮሬብ በቆምህበት ቀን ዓይኖችህ ያዩትን ነገር እንዳትረሳ፥ በሕይወትህም ዘመን ሁሉ ከልብህ እንዳይወድቅ ተጠንቀቅ፥ ነፍስህንም በትጋት ጠብቅ፤” (ዘዳግ. 4፥9-10)፣ “ከግብፅ ምድር ከባርነት ቤት ያወጣህን እግዚአብሔርን እንዳትረሳ ተጠንቀቅ።” (ዘዳግ. 6፥12)፣ “ … አባቶችህ ያላወቁትን መና በምድረ በዳ ያበላህን አምላክህን እግዚአብሔርን እንዳትረሳ፤ …” (ዘዳግ. 8፥16) … ብሎ በተደጋጋሚ የተናገረው፣ እስራኤል ከዳነችና ነጻ ከወጣች በኋላ በመርሳት ኀጢአት ለሚታክት ጊዜ ተይዛ መውደቋን ጌታ እግዚአብሔር ስለሚያውቅ ነበር።

በተመሳሳይ መንገድ የአዲስ ኪዳን የእግዚአብሔር እስራኤልም፣ ትልቁ ስህተቷ ይቅር መባልዋን ልትረሳ እንደምትችል መንፈስ ቅዱስ መናገሩ ነው። ቅዱስ ጴጥሮስ የቀደመ በደልና ኀጢአቱ ይቅር የተባለ ሰው፣ ይቅር እንደ ተባለ የሚረሳ ከኾነ፣ የቅርቡን ብቻ የሚያይ ወይም ኾን ብሎ ላለማየት ዓይኑን የሚጨፍን ነው፤ ከዚህ የተነሣ ዕውር ነው ይለናል።

ድነን እግዚአብሔርን ስንከተል፣ በ2ጴጥ. 1፥5-7 ያሉትን ባሕርያት እንድንይዝ በጸጋው አድሎናል፤ ነገር ግን ድነናል እያልን፣ እኒህ ባህርያት በእኛ ባይገኙብን፣ አማኞች እግዚአብሔርን የመምሰል ሕይወታችንን እያጣን፣ ዓይነ ስውር እስከምንሆን ድረስ በቅርብ የማየት ችሎታ ላይ ደርሰናል ወይም እንመላለሳለን እያልን በሥራችን የማያምኑ ሰዎችን መስለን እየኖርን ማለት ነው። ዘላለማዊ ዕይታ አጥቶ ወደ ጊዜያዊ ነገር ብቻ ያዘነብላል እያለን ነው።

ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ የዘረዘራቸውን መልካም ባሕርያት ወደ ጐን ያደረጉ ሰዎች፣ ከቀደመ ኀጢአታቸው መንጻታቸውን ረስተዋል ማለት ነው። እነዚህን ባሕርያት መተውና ከርስ በርስ ይልቅ  ለራሳችን ብቻ መኖር አግባብ አይደለም፤ እግዚአብሔር በምድር ላይ ያለውን ዓላማ ለመፈጸም እንዳሰበው ልንመላለስ የተጠራነው ለዚህ ነውና። ከዚህ መጉደል ወይም እግዚአብሔር እንድንኾን ካሰበው አንሶ መገኘት ወይም አለመቻል እጅግ ልብን ይሰብራል።

እናም ከዳንን፣ የዳነ ሰው መኖርንና እግዚአብሔርን የምንመስልባቸውን ባሕርያትን መያዝን ፈጽሞ ልንዘነጋ አይገባንም፤ ይህም የመዳን አንዱና ትልቁ ክፍል ነውና፤ አትዘንጉ!

“ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን በማይጠፋ ፍቅር ለሚወድዱ ሁሉ ጸጋ ይሁን።” (ኤፌ. 6:24) አሜን።

   

2 comments:

  1. ቢያንስ ለሰው የውድቀት ምክንያት እንዳንሆን እንጠንቅ።

    ReplyDelete
  2. አባቴ ከመፅሐፍ ቅዱስ መጥቀስ ምንፍቅና ነው አሉ ዘመዶቻችን

    ReplyDelete