Friday, 2 May 2025

ማርያምን ከጌታ የሚያስበልጡማ በኦርቶዶክስ ቤት አይነኩም!

Please rad in PDF 

ማስረጃው ይኸው!

በኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ውስጥ፣ ስለ ማርያም የሚሰሙ “ስብከቶች” ማርያም ያለ እግዚአብሔር ሳይኾን፣ እግዚአብሔር ያለ ማርያም ሕይወት አልባ የሚያስብል ብካይና የተመረዘ ትምህርት አለ። ነገረ ማርያም በነገርነቱ ሳይኾን፣ “እንደ ተሰቀለው ክርስቶስ” በደረጀ ስብከቱና እምነቱ አለ!

ሊቀ ጳጳስ ገብርኤል “ማርያም ቤዛ አይለችም” ብለው ሲናገሩ፣ ከኢየሱስ የመስቀል ሥራ ጋር አነጻጽረው መናገራቸው በአደባባይ እየታወቀ፣ የኦርቶዶክስ ካራ ጀማ በአንድነት ተሰባስቦ፣ “ቤዛ ዐውድ አለው፣ እንኳን ማርያም ወ/ሮ ቤዛና ነቢይ ሙሴም ቤዛ ተብለዋል” ... የሚል ኢየሱስንና የመስቀሉን ሥራ በግልጥ የሚነቅፍ ምላሽ ሲሰጡ አየን። ከዚህ የሚከፋው ደግሞ፣ ማርያምን ያከበሩ ለማስመሰልና እውነተኞች ለመምሰል፣ ከእግዚአብሔር በላይ አድርገዋት ሲያቀርቡ ነው።


ይህ “ሰባኪ” የሚናገረውን ከዚህ በታች ልጥቀስ።

“… እርሷ[ማርያም] የኹሉም ነገር ጥንስስ ናት፤ ሰማይና ምድር እየተባሉ የሚጠሩት ነገሮች በሙሉ መነሻቸው ለፍጥረት ይኾናል እንጂ ፍጻሜያቸው ለእመቤታችን ነው። ኸረ እንደውም ይህ ነገር አይድነቃችሁ፣ እግዚአብሔር አምላክ ፍጥረትን ያዘጋጀው፣ ለእመቤታችን ነው ብዬ ብነግራችሁስ! ኹሉም ነገር የተፈጠረውና የተገኘው ስለ እርስዋ ሲባል ነው። በጣም የሚደንቃችሁ እነዚህ ፍጥረታት ሁሉ ከመኖራቸው በፊት፣ … እግዚአብሔር የራሱ ዓለም ነበረው። ያ ዐለሙ በኅሊናው ታስባ የነበረችው እመቤታችን ናት። ለእግዚአብሔር ኅሊና መታሰቡ እንደ እናቱ ብቻ እንዳይመስላችሁ፤ እመቤታችን ለእግዚአብሔር ዓለሙም ጭምር ናት …”

በዚህ ልጅ ንግግር ውስጥ አእላፋት ኑፋቄዎች አሉ። ኹለቱ ላይ ብቻ ላተኲር፣

1.   እውን ፍጥረት የተፈጠረው ለእመቤታችን ሲባል ነው? የፍጥረት ፍጻሜስ ማርያም ናት? … እኒህ ጥያቄዎች ቀላል ግን ሙሉውን የነገረ መለኮት ትምህርት ሊቀይሩ የሚችሉ ናቸው፤ ምክንያቱም ፍጥረት ለፍጥረት እንደ ተፈጠረ ጨርሶ አይነግረንምና፤ የፍጥረት መፈጠርን ዓላማ ከመጽሐፍ ቅዱስ ልጥቀስ፣

በአጭር ቃል መጽሐፍ፣ “ምድርና ሞላዋ ለእግዚአብሔር ናት፥ ዓለምም በእርስዋም የሚኖሩ ሁሉ።” (መዝ. 24፥1) ይላል። ሲፈጥርም አዝዞ የተፈጸመለት፤ ምድርን በቃሉና በኃይሉ የፈጠረ፣ ዓለሙን በጥበቡ የመሠረተ፣ ሰማያትን በማስተዋሉ የዘረጋ ጌታ እግዚአብሔር ብቻ ነው፤ (ዘፍ. 1፥3፡6፡9፡11፡14፡20፡24፡26፤ ኢሳ. 40፥12-14፤ ኤር. 10፥12-16፤ ዮሐ. 1፥3)፤ ይህ ብቻ ያይደለ በቀንና በሌሊት ላይ ፀሐይና ጨረቃን ያሠለጠናቸው፤ የፈጠራቸውም ርሱ ብቻ ነው (ዘፍ. 1፥16፤ መዝ. 136፥7፤ አሞ. 4፥13፤ ዮሐ. 1፥3፤ ቈላ. 1፥15-16፤ ዕብ. 11፥3)

-     ፍጥረት የተፈጠረው ለእግዚአብሔር ሊሰግድና ለክብሩ ሊኖር ብቻ ነው፣

አንተ ብቻ እግዚአብሔር ነህ፤ ሰማዩንና የሰማያት ሰማይን ሠራዊታቸውንም ሁሉ፥ ምድሩንና በእርስዋ ላይ ያሉትን ሁሉ፥ ባሕሮቹንና በእነርሱ ውስጥ ያለውን ሁሉ፥ ፈጥረሃል፥ ሁሉንም ሕያው አድርገኸዋል፤ የሰማዩም ሠራዊት ለአንተ ይሰግዳሉ።” (ነህ. 9፥6)፣

“ … በስሜ የተጠራውን ለክብሬም የፈጠርሁትን፥ የሠራሁትንና ያደረግሁትን ሁሉ አምጣ” (ኢሳ. 43፥7)፣

“ሀያ አራቱ ሽማግሌዎች በዙፋን ላይ በተቀመጠው ፊት ወድቀው፥ ከዘላለም እስከ ዘላለም በሕይወት ለሚኖረው እየሰገዱ፦ ጌታችንና አምላካችን ሆይ፥ አንተ ሁሉን ፈጥረሃልና ስለ ፈቃድህም ሆነዋልና ተፈጥረውማልና ክብር ውዳሴ ኃይልም ልትቀበል ይገባሃል እያሉ በዙፋኑ ፊት አክሊላቸውን ያኖራሉ።” (ራእ. 4፥101-11)።

-     ፍጥረት በክርስቶስ ለክርስቶስ ተፈጥሮአል፣

“እርሱም የማይታይ አምላክ ምሳሌ ነው፤ የሚታዩትና የማይታዩትም፥ ዙፋናት ቢሆኑ ወይም ጌትነት ወይም አለቅነት ወይም ሥልጣናት፥ በሰማይና በምድር ያሉት ሁሉ በእርሱ ተፈጥረዋልና ከፍጥረት ሁሉ በፊት በኵር ነው፤ ሁሉ በእርሱና ለእርሱ ተፈጥሮአል፤” (ቈላ. 1፥15-16)።

ጥቂት ነገር ልጨምር፣ አስቀድሞ፣ የእስራኤል ልጆች ምድርን በተመለከተ ልክ እንደ አሕዛብ ወይም እንደ አንዳንድ የኦርቶዶክስ ሰባኪያን ደካማ አመለካከት ነበራቸው፣ ያሉበትና የሚኖሩበትን ብቻ የእግዚአብሔር እንደ ኾነ ያስባሉ፡፡ ዮናስና አንዳንዶች እግዚአብሔር የሌለበት የምድር ክፍል ያለ መሰላቸው፤ እንደ ዳዊት ያሉ ቅዱሳን ግን እስራኤል ብቻ ሳትኾን አሦርም፤ ግብጽም፤ ባቢሎንም ምድር ኹሉም የእግዚአብሔር ናቸው ብለው ያምናሉ።

ጌታ እግዚአብሔር በእነዚህ አገር ካሉ አማልክት እጅግ የተለየና ታላቅ ነውና። ምድርና መላዋ የርሱ ከኾነች፤ ለርሱ ክብርና ፈቃድ ብቻ ትታዘዛለች ማለት ነው። ምክንያቱም “ምድርና በእርስዋ የሞላባት ሁሉ የጌታ ነውና።” (1ቆሮ. 10፥26)፡፡

የፍጥረት ፍጻሜ ግቡም፣ “በዘመን ፍጻሜ ይደረግ ዘንድ ያለው አሳቡም በሰማይና በምድር ያለውን ሁሉ በክርስቶስ ለመጠቅለል ነው።” (ኤፌ. 1፥10) ተብሎአል፡፡

2.   ማርያም ከፍጥረት በፊት ነበረችን? ማርያም ዓለም በሌለበት ዘመን ለእግዚአብሔር ዓለሙ ነበረች? … እንዲህ ብሎ ማስተማር በራሱ፣ “ከሰንበት ተማሪ” ያነሰ ማንነትን መያዝ ነው። አንድ ጤናማ የኦርቶዶክስ ሰንበት ተማሪ የማርያምን ፍጡርነት እንዴት ይስታል? “እናቷ ሐና አባቷ ኢያቄም” ብሎ ገና በማለዳ እየሰማ አድጓልና። ግን ከኦርቶዶክስ ውጭ ያለ የካቶሊክንም ትምህርት የቀዳ ሰው፣ እንደዚህ “ሰባኪ” መቃዠቱ አይቀርም።

ካቶሊካውያን ማርያምን “ኃይለ አርያማዊት” ማለታቸውን ከዚህ በፊት አንስተን መልስ ሰጥተንበታል፤ ኦርቶዶክሳውያንም በመጽሐፋቸው ያለውን ትተው ከካቶሊክ የተቀዳ ትምህርት ይዘው “ከፍጡራን በላይ፤ ከፈጣሪ በታች” የሚል አስተምህሮ ይዘዋል። ይህን እውን ለማድረግም፣ እግዚአብሔር ፍጥረትን ሲፈጥር፣ አስቀድሞ ሚካኤልን እንዳማከረውና ሲያማክረውም “ስለ ማርያም ብሎ ፍጥረትን እንዲፈጥርና ጊዜው እስኪደርስ ማርያም በሚካኤል ክንፍ ሥር ታትማ ትቆይ” የሚል ተረት ተዘጋጅቶለታል።

መጽሐፍ ግን በግልጥ፣ “የጌታን ልብ ያወቀው ማን ነው? ወይስ አማካሪው ማን ነበር? ወይስ ብድራቱን ይመልስ ዘንድ ለእርሱ አስቀድሞ የሰጠው ማን ነው?” (ሮሜ 11፥34-35) ይላል፡፡ ማርያም በእግዚአብሔር ኅሊና ትታወቅ ነበር ማለት የእግዚአብሔርን ቅድመ ዕውቀት እንጂ የማርያምን ብቃት አያሳይም፡፡ እግዚአብሔር ገና ያልተደረገውን ሲያውቅ አማካሪም ረጅም የለበትምና!

ዐሳቤን ልቋጭ፣ መጽሐፍ፣ “ሁሉ ከእርሱና በእርሱ ለእርሱም ነውና፤ ለእርሱ ለዘላለም ክብር ይሁን፤ አሜን።” (ሮሜ 11፥36) እንደሚል፣ ፍጥረት ያለ ሰው ዐሳብ በእግዚአብሔርም ዕቅድ ብቻ መጥቶአል። ደግሞም ኹሉም ነገር በርሱ በኩል ካልኾነ በቀር፣ ሊሳካና ሊዋብ፤ ሊራመድና ሊጸና አይችልም፤ ፍጥረተ ዓለሙ ያለ እግዚአብሔር መናና ወና ነው። እኛ ከኀጢአታችን እንኳ ነጻ መውጣት ያልቻልን ደካማ ፍጥረት ነበርን! ኹሉም እንደገና “የጸጋው ክብር ይመሰገን ዘንድ” (ኤፌ. 1፥6) በውዴታ ምስጋናና ክብርን ለእግዚአብሔር ይሰጠዋል።

ቅዱስ ጳውሎስ በጥቂቱ እግዚአብሔርን በማወቁ በታላቅ ደስታ ያመሰግነዋል፤ በርግጥም እኛም እግዚአብሔርን ያወቅነው በፍጥረቱና (ሮሜ 1፥20-21) በተለይም ደግሞ በልጁ በኩል በኾነልን መገለጥ ነው (ዮሐ. 1፥18)፤ ያወቅነውን እግዚአብሔርን ባለማወቃችን ይበልጥ እናመልከዋለን እናመሰግነዋለን እንጂ ከቶ ወዴትም አንሄድም!

ይህን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት እየረገጡ፤ የተሰቀለውን ክርስቶስን የሚጋርዱ የማይወገዙ ግን ስለ ክርስቶስ ጥቂት ሲናገሩ የሚረገሙበት ቤት “ኦርቶዶክስ! መኾኑ እጅግ ያሳዝናል፤ ነገር ግን ጌታ ስለ ቃሉ ታማኝ ነውና ለኦርቶዶክሳውያን የወንጌል ብርሃን እንደሚበራ አምናለሁ!

“ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በማይጠፋ ፍቅር ለሚወድዱ ሁሉ ጸጋ ይሁን።” (ኤፌ. 6፥24) አሜን።

3 comments:

  1. ኦርቶዶክስን ሳይሆን መምህራንን መቃወም ጥሩ ነው....እናንቴ ታድሶ የምትባሉ ሰዎችን ወደ ማይሆን ቦታ እያወሰዳችው ነው ተመለሱ...እዝ ኦርቶ ሆናችው ተከራከሩ...ሰዎችን ሜዳ ላይ አታስቀሩ

    ReplyDelete
  2. የራሷ እያረረባት ያስብላል ይሄ መጀመሪያ የቤታችሁን ጉዳይ አስተካክሉ
    ሁለተኛ you can't dictate us how who to worship. You can't. አምልኮተ እግዚአብሔርን ይዛ ከጥንት እስከዛሬ ለመጣች ቤተክርስቲያን አንተ ዛሬ መጥተህ የምታመልከውን ልትመርጥላት አትችልም በፍፁም አምላኳንም ጌታዋንም በደንብ የምታውቅ የምታሳውቅ የምታምን የምታሳምን ቤተክርስቲያን ናት። ላንተ አስተማሪዎችና አስመላኪዎች እንኳን ኢየሱስ ክርስቶስን ያሳወቀቻቸው ቅድስት ቤተክርስቲያን ናት። ስለዚህ እግዚአብሔርን አያመልኩም ማርያምን ያመልካሉ ለማለት የሚያስችል እውቀት ያስፈልግሃል። ቤተክርስቲያንን መስማት ማውቅ መረዳት ያስፈልግሃል ካወቅሃትና ከተረዳሃት በኋላ ልትከተላት ካልፈለክ ባለህበት ልትፀና ትችላለህ። ባላወቅኸው ነገር ላይ መወሰን መበየን መተቸት ግን ሞራላዊ አይደለም።

    ReplyDelete
  3. አንድ Mariology’ን የማያውቅ ሰው እንዲህ አይነት የማይረባ ትንታኔን ቢሰጥ አይገርምም። ምክንያቱም ስለ ጽንሰ-ሃሳቡ ቅንጣት እውቀት ስለሌለህ። እስኪ ቀድመህ ስለ ነገረ ማርያም የተወሰኑ ዶክመንቶችን እይ። ከዚያ ለንግግርህ ይቅርታ ትጠይቅበታለህ

    ReplyDelete