Wednesday, 14 May 2025

ክርስቶስ ከማርያም ይበልጣል!

 Please read in PDF

የዕብራውያን መልእክት ጸሐፊ የአይሁድን ሃይማኖት ሲከተሉ ኖረው፣ ፊታቸውን ወደ ክርስትና ዘወር ስላደረጉ ሰዎች መልእክትን ሲጽፍላቸው፣ በቀደመው እምነታቸው ታላላቅና የሚከበሩ ነገሮችን ከኢየሱስ ጋር በማነጻጸር “ኢየሱስ ከኹሉም[ከመላእክት፣ ከሊቀ ነቢያት ሙሴ፣ ከመገለጦች ኹሉ፣ ከእንሰሳት መሥዋዕቶች] ይልቃል፤ ይበልጣል” በማለት በታላቅ መገለጥ ይጽፍላቸዋል። ከዚህ ቀደም የተሠሩት ሥራዎች ኹሉ፣ በኀጢአት በወደቁት ነቢያት፤ አባቶችና እናቶች ፍጡራን አማካይነት መኾኑን በመግለጥ በስፋት ይጽፋል። በርግጥም በብሉይ ኪዳን የነበሩት የእግዚአብሔር ሰዎችም፣ ስለ ሥራቸውና ጽድቃቸው ሲናገሩ፣ “ ..ሁላችን እንደ ርኩስ ሰው ሆነናል፥ ጽድቃችንም ሁሉ እንደ መርገም ጨርቅ ነው፤ ሁላችንም እንደ ቅጠል ረግፈናል፥ … ” (ኢሳ. 64፥6) ብለዋል።

የዕብራውያን ጸሐፊ “ክርስቶስን ከኹሉ ይልቅ አልቆ ወይም አስበልጦ” ያቀረበበትን ምክንያት እኒህ ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛሉ መጥቀስ፤

·       ዕብራውያን የብሉይ ኪዳን አማኞች ናቸው፤ ለረጅም ዓመታት በዚህ እምነት ውስጥ በመቆየታቸውም አይሁዳዊ ብሔርተኝነትንና ሃይማኖታቸውን እጅግ በማጥበቃቸው፣ ወደ ክርስትናም ሲመጡ በክርስትና ውስጥም ባዕድና ባዳ ጠባይን ማንጸባረቅ ጀመሩ። እንዲያውም፣ ወደ ክርስትና ያልመጡ አይሁድ፣ ወደ ክርስትና የመጡትን አይሁድ አይሁዳዊነታቸውን እንደ ካዱ ጭምር ቈጠሩአቸው።

·       ቅዱስ ጳውሎስ፣ “ … ልጅነትና ክብር ኪዳንም የሕግም መሰጠት የመቅደስም ሥርዓት የተስፋውም ቃላት ለእነርሱ ናቸውና፤ አባቶችም ለእነርሱ ናቸውና …” (ሮሜ 9፥4-5) እንዲል፣ አይሁድ በዚህ የዘመናት ውርሳቸው እጅግ ይመኩና ይኰሩ ነበር። የእግዚአብሔር እስትንፋስ ያረፈበት ቃልና ኪዳናት ነበሩዋቸው። የዕብራውያን መልእክት ጸሐፊ አንዳንዶች እንደውም፣ ወደ ብሉይ ኪዳን የአምልኮ መንገድ ሊመለሱ እንዳላቸው ደጋግሞ ይናገራል።

የመልእክቱ ጸሐፊ ዕብራውያን የሚመኩባቸውን እኒህን ነገሮች ኹሉ፣ ከክርስቶስ የሚያንሱና በቀደመው ኪዳን ውስጥ የተሰጡትም ተስፋዎችና የዘመናት ውርሶችም በክርስቶስ መፈጸማቸውንና ፍጻሜ አጊኝተው፤ ክርስቶስ የሚሻል ተስፋ (7፥18-19)፣ የሚሻል ዋስ (7፥22)፣ እጅግ የሚሻል አገልግሎትና ኪዳን (8፥6)፣ የሚበልጥ ስምና ክብር (1፥4፤ 3፥3) ይዞ፣ በሚሻል ኪዳን ብቸኛ የአዲስ ኪዳን መካከለኛ መኾኑን አሳየ (8፥6፤ 9፥15፤ 12፥24)።

እናም የዕብራውያን ጸሐፊ፣ አይሁድ ዕብራውያን ክርስትናን ከተቀበሉ በኋላ ወደ ብሉይ ኪዳን የአምልኮ መንገድ ቢመለሱ፥ በክርስቶስ የመስቀል ላይ ሞት ማመናቸውን እንደ ካዱ አጥብቆ አስረዳ። ክርስቶስ ታላቅ ሰው ነው ብሎ ቢያስቡም እንኳ፥ ወደ ብሉይ ኪዳን መመለሱ የክህደት ተግባር እንደ ኾነና ያፈሰውንን የኪዳን ደም የመርገጥ ያህል በጠንካራ ቃል ወቀሰ። ለኃጢአታቸው መሞቱን ጭራሽ እንዳልተፈጸመ ታሪክ ከንቱ ማድረጋቸው እንደ ኾነም ጮኾ ተናገረ። የእግዚአብሔርን የመዳን መንገድ ባለመቀበላቸው ሌላ የመዳን መንገድ እንደማያገኙም ቁርጡን ነገራቸው። ስለዚህ ክርስቶስ ላይ ዓይኖቻቸውን መትከል እንዳለባቸውና ወደ ይሁዲነት መመለስ እንደሌለባቸው በመልእክቱ በማስጠንቀቂያ ጭምር ተናገረ።

ዛሬም ሰዎች ከክርስቶስ በላይ የሚመለከቷቸው ነገሮች አሏቸው፤ እኒህ ሰዎች በቃላቸው ሲናገሩ ክርስቶስን ብቻ እንደሚያስቀድሙ ሊናገሩ ይችላል፤ ነገር ግን ክርስቶስን የሚያስበልጡ ነገሮች እንዳላቸው ተግባራቸው ምስክር ነው። ለምሳሌ፦ ኦርቶዶክሳውያን ማርያምን ከክርስቶስ አናስበልጥም ሲሉ እንሰማቸዋልን፤ ነገር ግን ተግባራቸው ከክርስቶስ በላይ እንደሚመለከቷት እሙን ነው። ለክርስቶስ የሚነገረውን የቤዝወት ትምህርት ከመጥቀስ ይልቅ፣ በደፈናው “ማርያም ቤዛዊተ ዓለም ናት” ሲሉ፣ በቅዱሳት መጻሕፍት የተመሰከረለትን የክርስቶስ ቤዝወት ወደ ጎን መተዋቸው እንደ ኾነ አያስተውሉም።

ለዚህም ነው፣ ልክ ለዕብራውያን አማኞች ክርስቶስ ከኹሉ እንደሚልቅ መልእክት እንደ ተጻፈ እንዲኹ፣ ዛሬ ላሉ ኦርቶዶክሳውያንም ክርስቶስ ከማርያምና ከኦርቶዶክሳዊ የዘመናት ውርስና ቅርስ ኹሉ እንደሚበልጥ መናገር ያለብን። 

ክርስቶስ ከማርያምና ከኦርቶዶክሳዊ የዘመናት ውርስና ቅርስ ኹሉ ይበልጣል!

“በማያቋርጥ ፍቅር ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን ለሚወዱ ሁሉ ጸጋ ይሁንላቸው።” (ኤፌ. 6፥24)

8 comments:

  1. ኦርቶዶክስን ሳታውቅ ወተህ ከማርያም ጠላትነት አዚም ያረገብህ ዲያቢሎስ ሸፍኖብህ መቼም ጨበጣ ከመዋጋት ልብህን ክፍት ብታረግ ለእውነት ብትጨክን ፍራሽ አዳሽ አዳራሽ ለሰከንድም አትቆምም እሩጠህ ታመልጥ ነበር ።

    ReplyDelete
  2. በዚህ ዘመን የኦርቶዶክስ አምልኮተ ማርያም ግልጥልጥ ብሎ የታየበት ጊዜ ነው ።

    ReplyDelete
  3. ለታረደው በግ ክብር ሀይል ምስጋና ይገባል አሜን

    ReplyDelete
  4. “የርኅራኄ አባት የመጽናናትም ሁሉ አምላክ የሆነ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት ይባረክ።”
    — 2ኛ ቆሮ 1፥3

    ReplyDelete
  5. ስለዚህ አንተ የጌታ እናት "እመቤታችን" መባል የለባትም እያለከን ነውን? እሷ ራሷን እንዳለችው ባሪያ ብላችሁ ጥሩ ማለትህ ነው?
    ደግሞ ከእኛ በላይ ለእግዚአብሔር ባሪያ መሆን ክብር እና ደስታ መሆኑን ማነው የተረዳው? ጸሎት ሲያሳርጉ አባቶች ለገብርከ(ለባሪያህ)... ለዓመትከ(ለሴት ባሪያህ)... ብለው ነው።
    እኛ መቼም ፈጣሪን ከፍጥረቱ ጋር አወዳድረን አናውቅም! እናንተ ናችሁ እንጂ እንደ ተፎካካሪ ፓርት በተለያየ ጎራ አስቀምጣችሁ የሚታወዳድሩ።

    አንተም ቢትሆን ራስን ከእግዚአብሔር እናት ጋር እኩል ነኝ እያልክ ራስን በራስህ ከፍ ከፍ አታድርግ!
    እሷ ንግስት ሲትሆን ራሷን ዝቅ ዝቅ አድርጋ፤ እግዚአብሔር ከሁሉም ፍጥረት እንደ እሷ ያለ እንዳይኖር አድርጎ ከፍ ከፍ አደረጋት!
    ከሰው ሰው እንደሚበልጥ መጽሐፍ ቅዱስ በደንብ አንብብ ትረዳለህ!
    እስከመጨረሻው አንብብ ወንድሜ
    " ራሱን ከፍ የሚያደርግ ሁሉ ይዋረዳል፥ ራሱንም የሚያዋርድ ሁሉ ከፍ ይላል።"
    (የማቴዎስ ወንጌል 23:12)
    "ከሁላችሁ የሚያንስ እርሱ ታላቅ ነውና አላቸው።"
    (የሉቃስ ወንጌል 9:48)
    " ከሰው ሁሉ አርነት የወጣሁ ስሆን የሚበልጡትን እንድጠቅም እንደ ባሪያ ራሴን ለሁሉ አስገዛለሁ።"
    (1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 9:19)
    " ወንድሞች ሆይ፥ እናንተ ለአርነት ተጠርታችኋልና፤ ብቻ አርነታችሁ ለሥጋ ምክንያትን አይስጥ፥ ነገር ግን በፍቅር እርስ በርሳችሁ እንደ ባሪያዎች ሁኑ።"
    (ወደ ገላትያ ሰዎች 5:13)
    " ለዋኖቻችሁ ታዘዙና ተገዙ፤"
    (ወደ ዕብራውያን 13:17)

    ReplyDelete
  6. ይሄንን እውነት ሰዎቹ መስማት አይፈልጉም። ለአምላካቸው ሌላ አምላክ እንድኖር አይፈልጉም።

    ReplyDelete
  7. ከማህጸን ጀምሮ ስለጠበቃት መድሃኒቴ አለች እግዚአብሔር ከማህጸን ጀምሮ መጠበቅ ይቻላል ። ት ኢሳ 1፡9። እኛ ግን አምነን ተጠምቀን ቆርበን ነው መንግስቱን የምንወርሰው።

    ReplyDelete
  8. ስንኩል እውቀት ነው ያለህ : ብዙ ግዜ ሳይህ እንካን ቲዮሎጂ ይቅርና ኮሜንቶችን ስትረዳ ራሱ fallacy አለብህ እና ትንሽ ብትረጋጋ ብዙ ሰው ትጠቅም ይሆናል

    ReplyDelete