Thursday, 1 May 2025

ካራው “አቡነ” እንድርያስና “ዝክረ ኒቂያ” ስለ ወንጌላዊው አቡነ ገብርኤልና …!

 Please read in PDF

“የዝክረ ኒቂያ” ጉባኤ ትላንት ማምሻውን ማጠቃለያ ዐሳብና “የአቋም መግለጫ” በማውጣት ተጠናቅቆአል፤ “የመዝጊያ ንግግር” የሚመስል የካራ ትምህርት የተንሠራፋበትን ንግግር ያቀረቡት አቡነ እንድርያስ ናቸው፡፡ አቡኑ ገና ከጅማሬያቸው፣ “"ማርያም ቤዛዊተ ዓለም አትባልም የሚለው ስብከት ሕገ ወጥ ነው!" ማለታቸው እምብዛም አላስደነገጠኝም፤ ከዚህ የተሻለ ከነርሱ አልጠብቅምና፡፡ ነገር ግን በዚያ ኹሉ ንግግራቸው ማርያም ለኦርቶዶክስ አስፈላጊነቷን ደጋግመው ያጐሉትን ያህል፣ ክርስቶስ ኢየሱስን ደጋግመው ለማንሳት ይቅርና አንድም ጊዜ “እርሱ በርግጥ ቤዛና መድኃኒታችን ነው” አለማለታቸው እጅግ አስደንቆኛል፡፡

ጌታችን ኢየሱስ በናዝሬት ገሊላ በተደጋጋሚ ተአምራት አድርጎ፤ ትምህርትም አስተምሮ ነገር ግን አለማመናቸውን ማርቆስ ወንጌላዊው ሲነግረን፣ “ስለ አለማመናቸውም[ኢየሱስ] ተደነቀ” (ማር. 6፥6) ይለናል፡፡ እንደ አቡነ እንድርያስ ያሉ ጳጳሳትን ስመለከት፣ ዘወትር ትዝ የሚለኝ ቃል ማርቆስ ወንጌላዊ በወንጌሉ የጠቀሰው ቃል ነው፡፡ በንግግራቸው በአንድ በኩል በጣም ደስ ብሎኛል፤ ጨለማው ግጥጥ ብሎ ወደፊት በመውጣቱና “በማኅበራዊ ሚዲያው እነሄኖክ ኃይሌና ያረጋል አበጋዝ፤ ብርሃኑ አድማስ የሚሏትና ውስጥ ባለችው ኦርቶዶክስ መካከል የፈጠጠ ልዩነት መኖሩን እንዲህ አደባባይ በመውጣቱ ደስ ብሎኛል፤ በትላንትናው የአቡነ እንድርያስ ንግግር እንድትታደስ ወይም በዚሁ ትምህርቷ የምትጸና ከኾነ፣ “ለሰላምሽ የሚሆነውን በዚህ ቀን አንቺስ ስንኳ ብታውቂ፤ አሁን ግን ከዓይንሽ ተሰውሮአል።”  (ሉቃ. 19፥42) የሚለውን ጌታ ኢየሱስ ለኢየሩሳሌም በሃዘን ስብራት ኾኖ የተናገረውን ቃል በድጋሚ መናገር ይገባናል፡፡

እውነት ለመናገር “ኢየሱስ የኀጢአታችን ቤዛ ነው፤ ሌላ ቤዛ የለንም፤ ማርያም ቤዛችን አይደለችም” የሚለው ትምህርት፣ ይህን ያህል የድንጋጤና የሽብር ድምጽ ሳይኾን የመዳንና የምሥራች ድምጽ ነው፡፡ ክርስትና ያለ ማርያም “ከንቱ” እንደ ኾነ ለሚያስቡ ይህ ትምህርት ሁከትና ድንጋጤ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ደግሞ አባ ገብርኤልን “ለቁም እስር” መዳረግ፣ በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ ምን ያህል ኢ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትምህርት እንደ ገነነ ትልቅ ማሳያ ነው፡፡  በኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የክርስቶስ የኀጢአት ቤዝወትነት ተገፍቶ፣ ከማርያም ቤዝወት ጋር ተካክሎ አለመነገሩ ለምን ብዙዎችን እንዳስቆጣና እንዳስገነጠ ለማወቅ ይቸግራል፡፡

አንድ ሊቀ ጳጳስ ስለማርያም ተቆጭቶ፣ ስለ ኢየሱስ ግን አንድም የስብከት ቃል ትንፍሽ ሳይሉ መውረዳቸው እጅጉን ያስደንቃል፡፡ በዚያው ትይዩ ደግሞ ወንጌል የሰበከን ጳጳስ በዚያ ልክ ማጣጣልና ማልኮስኮስ፣ ከሊቅ እስከ ደቂቅ፤ ከጳጳስ እስከ ምእመን የተካኑበት መኾኑ እጅግ አስፈሪ ያደርገዋል፡፡ አባ በርናባስና አባ ገብርኤል እንዲህ ባሉ ጳጳሳት መካከል ተከብበው ስመለከት ጥቂት ተስፋ በውስጤ ቢኖርም፣ የትላንቱን ዓይነት “ዝክረ ኒቂያ” ጉባኤ ስመለከት ግን “ፍርድ የሚጠብቅ ብርቱ ጨለማ” መኖሩን አስተውላለሁ!

ወንጌል ግን እንዲህ ባሉ ሰዎች መካከልም እያሸነፈ መሄዱ አይቀርም፤ ቃሉ በብርቱ ተቃዋሚዎችም መካከል እያሸነፈ ይሄድ ነበርና፣ “የእግዚአብሔርም ቃል እየሰፋ ሄደ፥ በኢየሩሳሌምም የደቀ መዛሙርት ቍጥር እጅግ እየበዛ ሄደ፤ ከካህናትም ብዙ ሰዎች ለሃይማኖት የታዘዙ ሆኑ።” (ሐ.ሥ. 6፥7) እንዲል ይህ ቃል በኦርቶዶክስ እንደሚፈጸም ከአቡኑ የጨለማ ንግግር ጀርባ ተስፋ አደርጋለኹ!  

2 comments:

  1. በቃ ኦርቶዶክስ ማርያምን ታስበልጣለች
    ከዛስ ?
    ይመለከትሀል ?

    ReplyDelete
  2. በዉሀላ አልሰማንም አንዳይሉ በገዛ ጳጳሳቸው ወንጌል ተሰብኮላቸዋል!!!

    ReplyDelete