ነቢየ እግዚአብሔር ኤርምያስ በሙሾና በልቅሶ፤ ከፍ ባለ ሕመም ውስጥ ኾኖ
ያገለገለ፤ ከ“ዐበይት” ነቢያት መካከል አንዱ ነው። ገና እጅግ ወጣት በነበረበት ጊዜ (ኤር. 1፥6) ለነቢይነት የተጠራው ኤርምያስ፣
ሕዝበ እግዚአብሔር ተብላ የተጠራችው እስራኤል እጅግ በኀጢአት በተዘፈቀችበት፤ ከያህዌ ይልቅ ሌሎች አማልክትን በማፍቀር በነሆለለችበት፤
የማያረኩና ጥምን የማይቆርጡ ምንጮችን ለራስዋ በቆፈረችበት ወራት መምጣቱ፣ ልቡን በሥጋትና በፍርሃት፣ በጥርጣሬም ንጦት እንመለከታለን።
የኤርምያስ አገልግሎት፣ “ትነቅልና ታፈርስ
ዘንድ፥ ታጠፋና ትገለብጥ ዘንድ፥ ትሠራና ትተክል” (1፥10) ዘንድ እንዲል፣ መንታ ገጽታ ያለው ነው። እግዚአብሔር በሕዝቡ መካከል
ሊነቅል፣ ሊያፈርስ፣ ሊያጠፋና ሊገለብጥ ያለው ነገር አለ፤ እርሱም ኀጢአት ነው። ለዚህ ደግሞ ሕዝቡ ኀጢአትን በማድረግ እጅግ አመጸኛ
ኾኖ ተገኝቶአል፤ እናም እግዚአብሔር፣ “ሕዝቤ ሁለቱን ክፉ ነገሮች አድርገዋልና” (ቊ. 13) በማለት በሕዝቡ ላይ ክርክሩን ወይም
ቅሬታውን ያሰማል፤ (ቊ. 9)፤ እስራኤል፣ በዙሪያቸው ያሉትን አሕዛብ በመመልከት ከእግዚአብሔር ይልቅ ሌሎች አማልክትን ወድደዋል፤
ሕዝቡም ታማኝነታቸውን ከያህዌ ይልቅ ለቆጵሮስ(ኪቲም) እና ከቄዳር የባሕር ዳርቻ ማዶ ላሉ አማልክት ገልጠዋል። በሚያስደንቅ ኹኔታ
እስራኤል፣ ኀጢአትዋ አማልክትን ከሚያመልኩ ከነዚህ ሕዝቦች እንኳ ይበልጣል።
በምን? ብለን ብንጠይቅ፣ አማልክትን የሚከተሉ ሕዝቦች አማልክቶቻቸውን ፈጽሞ
አልተዉም፤ “ሐሰተኞች አማልክት ቢሆኑም እንኳ አማልክቱን የሚቀያይር ሕዝብ የለም፤” (ቊ. 11 አት) እንዲል። እስራኤል ግን ከነዚህ
አሕዛብ እጅግ በሚከፋ ኹኔታ፣ “ክብር ያጐናጸፍኳቸውን እኔን አምላካቸውን ምንም ሊያደርጉላቸው በማይችሉ ከንቱ አማልክት ለውጠውኛል።”
(ቊ. 11 አት) የሚል ጠንካራና ሕጋዊ ክስ ከያህዌ ቀርቦባታል። ይህ የይሁዳ ኀጢአት ደግሞ ያመጣው መቅሰፍት አለ፤ ሰማያት እንዲረገሙና
እንዲንቀጠቀጡ አድርጎአል (ቊ. 12)።
አሕዛብ ምንም ላላደረጉላቸው አማልክት ታማኝ ነበሩ፤ እስራኤልን ያከበረው
የክብር አምላክ እግዚአብሔር ግን በእስራኤል መካከል ተተወ፤ ተካደ፤ ተረሳ፤ ከእርሱ ፊታቸውን መለሱ። እንዲህ ያለ ዓመጽ በፍርድ
መዘጋቱ አይቀሬ ነው። አስቀድሞ ግን እግዚአብሔር በተደጋጋሚ ኃጢአተኞችን ከመቅጣቱ በፊት፣ ወደ ንስሐ እንዲመጡ ይማጸናቸዋል።
የእግዚአብሔር
ልብ በይሁዳ እጅግ አዝኖአል፤ አሕዛብ አማልክቶቻቸውን አልለወጡም፤ ይሁዳ ግን “እኔን የሕያውን ውኃ ምንጭ ትተውኛል፥ የተቀደዱትንም
ጕድጓዶች፥ ውኃውን ይይዙ ዘንድ የማይችሉትን ጕድጓዶች፥ ለራሳቸው ቆፍረዋል።” ብሎ እግዚአብሔር ልብን በሚነካ ሃዘን ይናገራቸዋል።
የእግዚአብሔር ሕዝብ በደል እጥፍ ድርብ ነው፤ የሕያውን ውኃ ምንጭ መተዋቸው ሳያንስ፣ ውኃ መያዝ በማይችሉ ቀዳዳ የውኃ ማጠራቀሚያዎች
እጅግ ታምነዋል።
በጥንቱ ዘመን የጉድጓድ ውኃ እጅግ ውድና አስፈላጊ ነገር ነበር፤ ለብዙ
አገልግሎትም ይውላል። ነገር ግን እስራኤል የእግዚአብሔርን የሕይወት ውኃ ምንጭ ትተው፣ ውኃ የማይይዙ የተሰባበሩ፤ እጅግ ያነሰ
አቅርቦት ያላቸውን የውኃ ጕድጓዶች ለማግኘት ደከሙ። ከቊ. 14 ጀምሮ እንደምናነበው ከዚህ የተነሣ፣ እስራኤል ሕጋዊ ልጅነቷን አጥታ
ባሪያ ኾና በምርኮና በስደት ከገዛ ምድሯ ተነቀለች። ሰው እግዚአብሔር የሠራለትንና ያዘጋጀለትን የሕይወት ውኃ ምንጭ ትቶ፣ ለራሱ
ጥም የሚያረካበትን ቢያዘጋጅ መቀጣቱና መተዉ አይቀርም።
እስራኤል የእግዚአብሔር ብቻ ነች፤ ልክ እንዲኹ በአዲስ ኪዳንም ያለነው
አማኞች የክርስቶስ ብቻ ነን፤ በኵራትነታችን በክርስቶስ ለእግዚአብሔር አብ ነን፤ ጠጡ የተባልነውና ጥምን የሚቆርጠው የሕይወት ምንጭ
ውኃ መንፈስ ቅዱስ ነው (ዮሐ. 7፥37-39)፤ “ማንም የተጠማ ቢኖር ወደ እኔ ይምጣና ይጠጣ” የሚለው ቃል፣ ዛሬም ሕያውና የሚሠራ
ነው። ልክ እስራኤል ያህዌን ትታ፣ የአሕዛብን አማልክት በመከተል ያህዌን ብዙ እንደ በደለች፣ ዛሬም ሰዎች እግዚአብሔር በልጁ ለአንዴና
ለመጨረሻ ጊዜ የሠራውን የቤዝወት፣ የማስታረቅ፣ የማዳን ሥራ ትተው፤ ከክርስቶስ ውጭ ሌላ ቤዛ፤ ከመሲሑ ውጭ እንግዳ መታረቂያ፤
ከኢየሱስ ውጭ ሌላ መድኃኒት፤ ከመንፈስ ቅዱስ ውጭ ሌላ የሕይወት ምንጭ ውኃ በመፈለግ ይንከራተታሉ። በክርስቶስ ዕረፉ፤ በርሱ ላይ
ምንም አትደርቡ፤ ብቻውን በቂና ሙሉ፤ ብቃት ያለው አዳኝ ነውና!
ነገር ግን እንደ እስራኤል፣ እንዲህ ያለውን ኀጢአት ማድረግ በፍጻሜው ቅጣትና
መተውን ማምጣቱ አይቀርም። እናም የምትባዝኑ፣ ከክርስቶስ ይልቅ ሌላ ቤዛና ተስፋ የምትፈልጉ፤ ከመንፈስ ቅዱስ ውጭም ሌላ እርካታና
ጥጋብ የምትሹ አይረባችሁምና ወደ ነፍሳችሁ እረኛ በመመለስ ዕረፉ፤ እፎይ ዐረፍኩ በሉ!
“በማያቋርጥ ፍቅር ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን ለሚወዱ ሁሉ ጸጋ ይሁንላቸው።”
(ኤፌ. 6፥24)
“አቤቱ፥ እንደ ቸርነትህ መጠን ማረኝ፤ እንደ ምሕረትህም ብዛት መተላለፌን ደምስስ።”
ReplyDelete— መዝሙር 51፥1