Wednesday, 27 December 2023

መድሎተ ስሑት ወይስ “መድሎተ ጽድቅ”?! (ክፍል ፳፮)

 Please read in PDF

1.5.    ወደ መጽሐፍ ቅዱስ መተርጎም፦ ለዚህ እጅግ አያሌ ማስረጃዎችን ማቅረብ ይቻላል። በኑዛዜና ቀኖና ውስጥ ከጠቀስናቸው ባሻገር፣ ሌሎች ጥቂት የመጽሐፍ ቅዱስን ክፍሎችን እንዴት ወደ መጽሐፍ ቅዱስ እንደ ተረጐመ እንጥቀስ።

1.5.1. “ … ከክርስቶስ መወለድ በኋላ ያለው የሰው ኹኔታ፣ በምልዓተ ኀጢአት ከደረሰበት ርኩሰት ነጽቷል፤ ተቀድሷል፤ ከድካሙ በርትቷል፤ ከውድቀቱ ተነሥቷል።” [1]

የ“መድሎተ ጽድቅ” ጸሐፊያንና አያሌ ኦርቶዶክሳውያን እንደሚያምኑት፣ የክርስቶስ መሥዋዕታዊ ሞቱ የአዳምን ኀጢአት በማስተሥረይ የተጠናቀቀ ብቻ ነው። ይህም ማለት ሰው የአዳምን ኀጢአት በተመለከተ ዕዳ የለበትም፤ ከጥንተ አብሶ ኀጢአት ነጽቷል፤ ተቀድሷል፤ በዚያ በደሉም ጨርሶ አይጠየቅም የሚል ሲኾን፣ ነገር ግን አኹን ለሚሠራው ኀጢአት ደግሞ ንስሐና ቀኖና እንጂ የክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ የሚያስፈልገው አይደለም የሚል ትምህርት አላቸው።

መጽሐፍ ቅዱስ ክርስቶስ ለመላ ዓለሙ ቤዛ ኾኖ መሰጠቱን እንጂ መላ ዓለሙ በምልዓተ ኀጢአት ከደረሰበት ርኩሰት መንጻቱን ወይም መቀደሱን የሚናገርበት ሥፍራ የለውም። ይልቁን የክርስቶስ መሰጠት ለመላለሙ ስለኾነ፣ መላለሙ በክርስቶስ ለመዳንና የእግዚአብሔር ምንግሥት ወራሽ እንዲኾን፣ በክርስቶስ መኾን ወይም ማመን እንዳለበት በግልጥ ይናገራል።

በዮሐንስ ወንጌል እንዲህ ተነግሮአል፤

ሙሴም በምድረ በዳ እባብን እንደ ሰቀለ እንዲሁ በእርሱ[በክርስቶስ] የሚያምን ሁሉ[መላለሙ] የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ የሰው ልጅ ይሰቀል ይገባዋል።” (ዮሐ. 3፥15)

ቅዱስ ዮሐንስ በወንጌሉ በጻፈው በዚህ ክፍል ሦስት መሠረታዊ ዐሳቦችን እናገኛለን፣

  • ማናቸውም ሰው ያለ ክርስቶስ ስቅለት ወይም ሞት ይጠፋል፣
  • ማናቸውም ሰው በክርስቶስ ስቅለት ወይም ሞት ካመነ የዘላለም ሕይወት ያገኛል፣
  • ቀድሞ ወደ ተሰቀለው የነሐስ እባብ የተመለከቱት እስራኤል ከመቅሰፍትና ከቁጣ እንደ ዳኑት እንዲኹ፣ ዛሬም ወደ ተሰቀለው ክርስቶስ የሚመለከቱ ኹሉ ከጥፋት ድነው ሕወትና ዕረፍትን ያገኛሉ።

እንግዲህ ይህ ንግግር አኹንም፤ ወደፊትም በክርስቶስ በማመን ስለሚገኝ የዘላለም ሕይወትነት የሚናገር እንጂ ውስንነት ወይም የጊዜ ገደብ ያለበት መኾኑን የሚያመለክት አንዳችም ዐሳብ የለውም።

መጥምቁ ዮሐንስም እንዲህ ብሎ ተናግሮአል፤

በልጁ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው፤ በልጁ የማያምን ግን የእግዚአብሔር ቍጣ በእርሱ ላይ ይኖራል እንጂ ሕይወትን አያይም።” (ዮሐ. 3፥36)

በሌላ ስፍራም፣

“ለተቀበሉት[ክርስቶስን] በስሙ ላመኑት ሁሉ ግን የእግዚአብሔር ልጆች የመኾን መብት ሰጣቸው፤” (ዮሐ. 1፥12) ተብሎአል።

ቅዱስ ጳውሎስም፣

“አሁን ግን በሕግና በነቢያት የተመሰከረለት የእግዚአብሔር ጽድቅ ያለ ሕግ ተገልጦአል፥ እርሱም፥ ለሚያምኑ ሁሉ የሆነ፥ በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን የሚገኘው የእግዚአብሔር ጽድቅ ነው፤ ልዩነት የለምና፤ ሁሉ ኃጢአትን ሠርተዋልና የእግዚአብሔርም ክብር ጎድሎአቸዋል፤ በኢየሱስ ክርስቶስም በሆነው ቤዛነት በኩል እንዲያው በጸጋው ይጸድቃሉ። እርሱንም እግዚአብሔር በእምነት የሚገኝ በደሙም የሆነ ማስተስሪያ አድርጎ አቆመው፤ ይህም በፊት የተደረገውን ኃጢአት በእግዚአብሔር ችሎታ ስለ መተው ጽድቁን ያሳይ ዘንድ ነው፥” (ሮሜ 3፥21-25)

በማለት እንዲህ ያሉ አያሌ ምስክርነቶችን ሰጥቶአል (ሮሜ 5፥9፤ ዕብ. 2፥17፤ 9፥28፤ 1ዮሐ. 4፥10)።

መጽሐፍ ቅዱስ በእነዚህ ክፍሎች ኹሉ ውስጥ የሚናገረው፣ ክርስቶስ ለመላለሙ ቤዛ ኾኖ መሰጠቱንና ለመዳንና ከዘላለም ፍርድና ሞት ለማምለጥ ግን ጌታ ኢየሱስን ማመንና አምኖም መቀበል እንደሚገባ ነው። ዛሬም እንኳ ለኀጢአታችን ማስተሥረያ እርሱ ወይም መሥዋዕታዊ ሞቱ ብቻ ነው፤ ለዘላለም የታመነ ሊቀ ካህናት ስለኾነም ከእርሱ በቀር ሊራራልንና ሊቀበለን፤ ሊረዳንም የሚችል የለም።

“ልጆቼ ሆይ፥ ኃጢአትን እንዳታደርጉ ይህን እጽፍላችኋለሁ። ማንም ኃጢአትን ቢያደርግ ከአብ ዘንድ ጠበቃ አለን እርሱም ጻድቅ የሆነ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። እርሱም የኃጢአታችን ማስተስሪያ ነው፥ ለኃጢአታችንም ብቻ አይደለም፥ ነገር ግን ለዓለሙ ሁሉ ኃጢአት እንጂ።” (1ዮሐ. 2፥1-2)

“እንግዲህ በሰማያት ያለፈ ትልቅ ሊቀ ካህናት የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ስላለን፥ ጸንተን ሃይማኖታችንን እንጠብቅ። ከኃጢአት በቀር በነገር ሁሉ እንደ እኛ የተፈተነ ነው እንጂ፥ በድካማችን ሊራራልን የማይችል ሊቀ ካህናት የለንም። እንግዲህ ምሕረትን እንድንቀበል በሚያስፈልገንም ጊዜ የሚረዳንን ጸጋ እንድናገኝ ወደ ጸጋው ዙፋን በእምነት እንቅረብ።” (ዕብ. 4፥14-16)

እንግዲህ የ“መድሎተ ጽድቅ” ጸሐፊ፣ የክርስቶስ መሥዋዕታዊ ሞት ዓለምን በሙሉ አዳነ ሲል፣ አኹን ስለምንሠራው ወይም ስለሚሠራው ኀጢአት አንድ ጊዜ ፈስሶ ለዘላለም ያዳነንን የክርስቶስን ደም ከመናገር ይልቅ ወደ ምስጢራት ለማዘንበል መጽሐፍ ቅዱስን ሲተረጕም ሳይኾን፣ ወደ መጽሐፍ ቅዱስ ሲተረጕም እንመለከተዋለን። ይህ ደግሞ ታላቅ በደል ነው! ከመጽሐፍ ቅዱስ እንጂ ወደ መጽሐፍ ተርጕመው እንደ ገዛ ፈቃዳቸው ከሚናገሩ ተጠበቁ!

ይቀጥላል …



[1] ገጽ 185

2 comments: