Monday 31 January 2022

ስለ ነነዌ፣ የእግዚአብሔርና የዮናስ ልብ!

Please read in PDF

እስራኤል በእግዚአብሔር ፊት እጅግ አስነዋሪ ኀጢአትን ሠራች። የሠራችውም ኀጢአት መቅደሱን የሚያረክስ፣ የእግዚአብሔርን አምልኮ በባዕዳንና በብዙ የአማልክት አምልኮ በመለወጥ በእግዚአብሔር ላይ ማመጽ ነበር። ከዚህ ዓመጿም እንድትመለስ፣ እግዚአብሔር አያሌ ቅዱሳን ነቢያትን ቢልክም፣ እስራኤል በልብዋ ከመኩራራት በዘለለ ወደ እግዚአብሔር ልትመለስ አልወደደችም። 

ከዚህም የተነሣ እግዚአብሔር ሕዝቡን ፈጽሞ እንደማይታገሥ ነቢያትን ልኮ ተናገረ። ሕዝቡ ተላልፈው የሚሰጡትም፣ ከደማስቆ ማዶ በአሦር እጅ እንደ ኾነ አሰምቶ አረጋገጠ። በኀጢአቱ ምክንያት የኪዳኑ ሕዝብ፣ ለሚያስፈራው የአሕዛብ ሕዝብ ሊሰጥ ኾነ። የኀጢአት መንገድ የሚያምር ቢመስልም፣ በፍጻሜው ግን የውርደትና የሞት ቁልቁለት ነው።

 እስራኤል ከኀጢአትዋ እንድትመለስ፣ ሆሴዕና አሞጽ ሲላኩላት፣ ለነነዌ ደግሞ በዚሁ ወራት ዮናስ ተላከላት። ዮናስ የተላከው፣ እግዚአብሔር፣ ነነዌ በንስሐ ፈጥና ባትመለስ፣ በእርሷ ላይ ሊያመጣ ያለውን የተቆረጠ ቊጣ በመናገር ለማስጠንቀቅ ነው። በዚህም እግዚአብሔር ለተመረጠችውና ለኪዳን ባለቤትዋ ለእስራኤል ብቻ ሳይኾን፣ ለአሕዛባዊቷ ነነዌም ያለውን የትድግናና የፍቅር ልብ የሚያመለክት ነው።

ከዮናስ የትንቢት መጽሐፍ እንደምናስተውለው ግን፣ ነነዌን እግዚአብሔር ለማዳን ማስጠንቀቁ በዮናስ እይታ ትክክል አልኾን ብሎ ታየው፤ እግዚአብሔር "ለእስራኤል እንጂ ለአሕዛባዊቱ ነነዌ ለምን ምሕረት ያደርጋል?" ብቻ ሳይኾን፣ "የዚህ ምሕረት ሰባኪ ለምን ያደርገኛል?" በማለት ዮናስ "አኮረፈ"፤ አለመታዘዝንም መረጠ። ዮናስ፣ እግዚአብሔር ነነዌን ሊምር በመውደዱ "መበሳጨቱ" ይደንቃል!  የተቀበለ በሚሰጥ ለምን ይናደዳል? ምሕረት ያገኘ፣ የወደደውን በሚምር ጌታ፣ ለምን ማርክ እንዴት ይላል?!

እግዚአብሔር፣ ለነነዌ በተደጋጋሚ ንስሐ እንዲሰበክ መውደዱ "መድኃኒትና መሐሪ እኔ ነኝ!" ማለቱ ነው። እግዚአብሔር በምሕረቱ፣ የሕዝቡ[የእስራኤል] ጠላት የኾነችውን ነነዌንም ይምራል። በዚህም እግዚአብሔር ለአሕዛብ ያለውን ወደር የለሽ ፍቅር ያሳያል። ይህ ግን የእግዚአብሔር ነን የሚሉትን ዮናስንና እስራኤልን ያናድዳል። ኹለቱም፣ "እግዚአብሔር ከእኛ ውጭ ሌላውን ለምን ወደደ?" የሚሉ ይመስላሉ።

ለዚህም ማሳያ፣ ዮናስ ወደ ተርሴስ በመርከብ ከመኮብለል ጀምሮ እስከ ከነነዌ ከተማ ወጣ ብሎ በጠራራ ፀሐይ በሜዳ ተቀምጦ እስካጉረመረመበት ጊዜ ድረስ ባለመታዘዝና በመቃወም ድርጊት ውስጥ ቆየ። ዮናስ፣ ኹሉን ወዳድ በኾነው በእግዚአብሔር ልብ ደስ አልተሰኘም። በተደጋጋሚም ተናደደ!

እግዚአብሔር ለመላ ዓለሙ የሚገድደው ፍቅር አምላክ ነው። በነነዌ ታሪክ ውስጥ፣ እግዚአብሔር፣ ዮናስና እስራኤል ይህን እንዲረዱ ፈልጎአል። ሚናቸውም ታላቅ እንደ ኾነ እንዲያስተውሉ። ልባቸው አሕዛብን በመጥላትና በመናቅ ሳይኾን፣ በፍቅርና በምሕረት እንዲቀበሉአቸው ለማሳየት። እነርሱ ግን አልወደዱም። ዮናስ ለእስራኤል አድልቶ ነነዌን ናቀ፤ እግዚአብሔር ግን "ግራ ቀኝዋን ላልለየች" ነነዌ ራራ።

የእግዚአብሔር ምሕረት መላለሙን ይቀበላል፤ ዘርና ቀለም፤ ብሔርና ነገድ፤ ወገንና ሕዝብ፤ ቋንቋና ቀለም ሳይለይ ኹሉንም ይቀበላል። ይህን አገልጋዮች ጭምር እንደ ዮናስ ላያስተውሉት ይችላሉ። እግዚአብሔር ግን በልጁ በክርስቶስ አምነው፣ በስሙ ንስሐና የኀጢአት ስርየት ሊቀበሉ እጃቸውን ለዘረጉ ኹሉ፣ ዛሬም የማይለወጥ ትድግናና ምሕረት አለው፤ አሜን።

እግዚአብሔር ምሕረቱ ለዘላለም ነውና!

 


No comments:

Post a Comment