Wednesday 18 July 2018

በሕማሙና በትንሣኤው ዙርያ የነበሩ ምስክሮች (ክፍል ኹለት)

2   ሴፍጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ወቅት እጅግ አስደናቂና አስገራሚ ክስተቶች ተከስተዋል፤ አንክድህም አብረንህ እንሞታለን ያሉቱ መከራና ፍርሃት ፈቷቸዋል፤ ፈጽመው ወደ ኋላ አፈግፍገዋል፤ ምንም እንኳ መከራ እንደ ሚመጣ ጌታችን አስቀድሞ የተናገረ ቢኾንም፣ በሥጋ ጉልበት ሊቋቋሙ በማሰባቸው ተሸንፈዋል፤ ጴጥሮስ በፈሪ ሰይፉ ጆሮ ሲቆርጥ ተስተውሏል።

  በተቃራኒው ግን ፈሪዎችና ድፍረት ያልነበራቸው ሰዎች ከተደበቁበት ማንነታቸው ወጥተው በአደባባይ ታይተዋል፤ ጐበዛዝት ሸሽተው፣ ያልተጠበቁት ግን ጀግነዋል። በብዙ መሃላ “አልለይም!” ቢሉም፣ በመጨረሻይቱ የቁርጥ ሰዓት ግን መለየታቸውንና ሽሽታቸውን በተግባር ገልጠዋል። ከእነዚህ የቁርጥ ቀን ወዳጆች አንዱ የአርማትያሱ[1] ዮሴፍ ነበር፤ ወንጌላዊው ዮሐንስ ስለ እርሱ እንዲህ ይላል፦
“ከዚህም በኋላ አይሁድን ስለ ፈራ በስውር የኢየሱስ ደቀ መዝሙር የነበረ የአርማትያስ ዮሴፍ የኢየሱስን ሥጋ ሊወስድ ጲላጦስን ለመነ፤” (ዮሐ. 19፥38)
በሕጉ የተሰቀለ እንደ ተሰቀለ በዚያው ማደር የለበትም፤ በሕጉ እንዲህ እንዲል፦
   “ማንም ሰው ለሞት የሚያበቃውን ኃጢአት ቢሠራ፥ እንዲሞትም ቢፈረድበት፥ በእንጨትም ላይ ብትሰቅለው፥ በእንጨት ላይ የተሰቀለ በእግዚአብሔር ዘንድ የተረገመ ነውና ሬሳው በእንጨት ላይ አይደር፤ ነገር ግን አምላክህ እግዚአብሔር ርስት አድርጎ የሰጠህን ምድር እንዳታረክስ በእርግጥ በዚያው ቀን ቅበረው።” (ዘዳግ. 21፥22)
   በሠራው ከባድ ጥፋት በሞት ቅጣት የተቀጣና የተሰቀለ ሰው በተሰቀለበት በዚያው ቀን በመስቀል ላይ ማደር የለበትም። ሥጋው የተረገመ ስለኾነ ከተሰቀለበት ቀን በላይ በመስቀል ላይ ቢቆይ ምድሪቱን ፈጽሞ ያረክሳል። “የጋይንም ንጉሥ እስከ ማታ ድረስ በዛፍ ላይ ሰቀለው፤ ፀሐይም በገባች ጊዜ ኢያሱ አዘዘ፥ ሬሳውንም ከዛፍ አወረዱት፥ በከተማይቱም በር አደባባይ ጣሉት፥ በላዩም እስከ ዛሬ ድረስ ያለውን ታላቅ የድንጋይ ክምር ከመሩበት።” (ኢያ. 8፥29) እንዲል፣ በማናቸውም ምክንያት የተሰቀለን ሰው ማሳደር አይገባም። የተሰቀለ ሰው በአደባባይ መዋረዱን ያመለክታል፤ ፍርዱንም እንደ ሕጉ ተቀብሏልና ፈጽሞ የተረገመ ነው። ከሕዝቡም አንድነት ተለይቷልና ፈጽሞ የተጠላ ነው። በተለይም ደግሞ ዕርቃኑን በአደባባይ ተሰጥቷልና እጅግ መዋረዱንና የረከሰ መኾኑን ያመለክታል።
    የአርማትያሱ ዮሴፍ ይህንን ሕግ በሚገባ ሳያስተውል አይቀርም፤ ለሕጉ ቀናተኞች ነን የሚሉት ጸሐፍትና መምህራን እንዲሁም ሐናና ቀያፋ በፍጹም ጥላቻ ጌታችንን ኢየሱስን በመስቀል ላይ እንደ ሰቀሉት ትተውታል። በግልጥም የራሳቸውን ሕግ ተላልፈው ተገኝተዋል። ይህም ብቻ ሳይኾን፣ በአይሁድ ነገረ መለኮት አንድ ንጹሕ ሰው ፈጽሞ የግፍ ተግባር ሊፈጸምበት አይገባም፤ ነገር ግን በክርስቶስ ኢሱስ ላይ የኾነው በተቃራኒው ነው።
   እርግጥ ነው፣ ጌታችን ኢየሱስ ኀጢአተኞች ስለኾንነው ስለ እኛ የውክልናን ቅጣት ውስዷልና፣ “በእንጨት የሚሰቀል ሁሉ የተረገመ ነው ተብሎ ተጽፎአልና ክርስቶስ ስለ እኛ እርግማን ሆኖ ከሕግ እርግማን ዋጀን” ነው፤ (ገላ. 3፥13)። እኛ መቀጣትና መዋረድ ያለብንን ኹሉ እርሱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዕዳችንን ኹሉ ለመክፈል ሲል፣ በሥጋው ተቀብሏል። እናም መዋረዳችንን ተቀብሎ ከመዋረድ፣ እርግማናችንን “ተረግሞ” እኛን ከመረገም ተቤዥቶናል፤ ክብር ይኹንለት፤ አሜን።
       ዮሴፍ ለምን ይኾን የፈራው? መጽሐፍ ቅዱስ በጥቂቱም ቢኾን መልሱን ይጠቁማል፤ ጥቂቱን ብናነሣ፦
V  ፍርሃት አለ፦ ኃጢአት ካስከተለብን መዘዝ አንዱ ድንጉጥነትን፣ ሽሽግነትን፣ ድብቅነትን ነው፤ (ዘፍ. 3፥10)። ባለሥልጣናትን የምንፈራው፣ ስናጠፋና ስንበድል ድንጉጥና ፈሪዎች የምንኾነው፣ ከፍርሃትም የተነሣ የምንቅበዘበዘው፣ መሸሸጊያ የምንፈልገው ... ከኃጢአታችን የተነሣ ነው። ይህን ከእግዚአብሔር መንፈስ፣ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ዘወትር በመኾን የምናመልጠው ነው። በቃሉ ከበረታን፣ በደሙ ዘወትር ከታጠብን፣ መንፈስ ቅዱስን ዘወትር ከተደገፍን መንፈሳዊ ድፍረት አለን። ክብር ይብዛለት፤ አሜን።
V  ሹመቱን እንዳያጣ ፍርሃት፦ የነበረው ሥልጣን ታላቅና በጊዜው ከነበረው ታላቁን ሥልጣን ነው። እናም ከ70ው አንዱ የኾነበት የአይሁድ ሸንጎነት ታላቅ ሥልጣኑን ሊያጣ ይችላል፣ ባለጠግነቱ ባንዴ ሊጠፋ ይችላል፤ ሃብቱንም ሊያጣው ይችላል፤ በምድራዊ ብእልና ክብር እጅግ ለተከበበ ሰው ይህን ነገር ባንዴ ማጣት እጅግ ያስፈራል፤ ከምንም በላይ ደግሞ የክርስቶስን ክብር በትክክል አለማየትና ዳግመኛ አለመወለድ ምድራዊውን “ንቀን” ሰማያውዊውን አልቀንና አክብረን ለመቀበልና ለመያዝ አይቻለንም።
  በእረኝነት ዘመኔ ከማልረሳቸው ክስተቶች አንዱ፣ በአንድ ወቅት ጅብ በረት ጥሶ ገብቶ፣ ከከብቶች ጋር በበረቱ የነበረውን አህያ ማጅራቱን እንደ ነከሰው ነጋበት፤ ማለዳ ላይ በብዙ ትግል፣ በመንጋጋው መካከል ብረት በመክተት ነበር ቤተሰቦቼ ውዱ አያቴ ያላቀቀው። ፍርሃትና ሥጋት አደገኛ ነገር ነው፤ ብዙ እንዳንሠራ፣ የምናውቀውን መንፈሳዊ እውነት በትክክል እንዳንገልጥ ፍርሃትና ቈንጥጦ ይዞናል። ጅብ አህያውን እንደ ያዘ ያስቀረው ነገር ፍርሃትና ሥጋት ነው። ብዙዎቻችን ከወንጌል ምስክርነት ወደ ኋላ ስቦ የያዘን ትልቁ ነገር ፍርሃት ነው፤ ከማኅበረሰቡ እንዳንገለል፣ በወዳጅ እጦት እንዳንንገላታ፣ መቀበሪያ ሥፍራ እንዳናጣ፣ በማኅበራዊ ሕይወት እንዳንገለልና ... ብዙ የፍርሃት ምክንያቶች አሉን።
V  ከምኩራቦቻቸው ሰዎችን ያስወጣሉ፦ አይሁድ ከእነርሱ ጋር የማይተባበረውን ኹሉ ከምኩራቦቻቸው ያስወጣሉ (ዮሐ.9፥34)፣ ከማኅበራዊ ሕይወትም ያገላሉ። በዚህ ተጽዕኖም ሰዎች ሃሳቦቻቸውንና ባሕሎቻቸውን፣ እምነታቸውንም ጭምር እንዲቀበሉ ያስገድዳሉ። አስተውሉ! ያ ዓይኑ የተፈወሰለት ሰው ስለኢየሱስ ክርስቶስ በመመስከሩ አይሁድ ከምኩራባቸው ወደውጭ አስወጡት፤ ነገር ግን ልክ ሲያስወጡ ጌታችን ኢየሱስ መጣለት። ዮሴፍ ይን እውነት አስቀድሞ አልተረዳም ነበር።
   ይህ ብዙዎችን ዛሬም ያስፈራል፤ በዚህ በ21ኛ መቶ ክፍለ ዘመን፣ የሰዎች የግል መብትና ነጻነቶቻቸው ተከብሯል በሚባልበት ዘመን እንኳ ክርስቶስን ማመንና እርሱን ብቻ መከተል ከብዙ ነገር ያስገልላል።
@ ነገር ግን ዮሴፍ በብዙ ነገር ቢፈራም፣ ደግነቱን አልጣለም፦ ደግ ነው፤ በጐነቱን አልተወም፦ በጐም ነው፤ ትክክለኛነቱንም አልጣለም፦ ጻድቅም ነው፤ እንዲያውም፣ ማርቆስ ለሸንጎው የከበረ አማካሪ እንደኾነ ጭምርም ይነግረናል፤ አኹን ግን ዋጋ በመክፈል ስለሕጉና ስለኢየሱስ ይመሰክር ዘንድ ተነሣ፤ [“የከበሩ መማክርት ከጉባኤው ከተለዩ ሌሎቹ ምን ሊመክሩ ይኾን?”]።
     የጽድቁም መገለጫ በክርስቶስ ሞት ከተማከሩት ሰዎች ጋር በአንድነት ተቀምጦ ፈጽሞ አልተማከረም፤ ቢኾንም ፈጽሞ ኢየሱስን በግልጥ አልተከተለውም። አኹን ግን ጨክኖ ሊወጣ ወሰነ። እናም ጌታችን ኢየሱስ በሞተ ጊዜ፣ ሰው ኹሉ ከእርሱ በሸሸና ሊቀርበው ባልወደደ ጊዜ፣ ሥጋውንም ከመቃብር ላይ “የሚያወርድና የሚቀብር አንድ ወዳጅ በጠፋ ጊዜ”፣ ራሱን ለአደጋ በማጋለጥ በፊት ለፊት በኩል መጣ፤ ይህን በማድረጉም በጌታችን ኢየሱስ ላይ ያለውን ጠንካራ እምነቱን አሳየ።
   ጌታችን ኢየሱስ መቀበርያ ሲያጣ በራሱ መቃብር ወስዶ ቀበረው፤ በኢሳይያስ ትንቢት እንዲህ እንደ ተባለ፦ “ከክፉዎችም ጋር መቃብሩን አደረጉ፥ ከባለጠጎችም ጋር በሞቱ፤ ሆኖም ግፍን አላደረገም ነበር፥ በአፉም ተንኮል አልተገኘበትም ነበር” (ኢሳ.53፥9)። ኢሳይያስ በክፋት፣ በማጭበርበር፣ ሃብት የሚሰበስቡ ባለጠጎችን በዚህ ሥፍራ ይነቅፋል፤ በሃብታቸው መመካታቸውንና ከእግዚአብሔር ይልቅ በሃብታቸው በመታመናቸው ይኰንናቸዋል፤ የተከበረው አማካሪ ዮሴፍ ኢየሱስን በራሱ መቃብር ቀበረው፤ ይህም ጽኑ ፍቅሩን ያሳያል፤ እርሱ በብዙ ይቅር የተባለ ነውና።
    መቃብሩን ከክፉዎች ጋር ሊያደርጉ ነበር፤ ለዚህም ቀብሩን በሥርዓት እንዳይፈጸም አደረጉ፤ ለሰማይ ወፎች ጎጆ፣ የምድር ቀበሮዎች ጉድጓድ ሳላቸው ጌታ ኢየሱስ ግን፣ መቀበርያ እንኳ አጣ፤ እናም በወዳጁ በአርማትያሱ ዮሴፍ መቃብር ተቀበረ። አቀባበሩም እንደ አይሁድ ሃሳብ ሳይኾን፣ ወደ ሠላሣ አራት ኪሎ ግራም የሚመዝን (አንድ መቶ ንጥር የሚያህል የከርቤና የእሬት ቅልቅል) ለንጉሣውያን ቤተሰብ እንደ ሚደረግ የቀብር ሥርዓቱ ተፈጸመ። ይህንንም የአርማትያሱ ሰው በድፍረት አደረገው።
   ድፍረት በሓዋርያት ሥራ ውስጥ ተደጋግሞ የተጠቀሰ ቃል ነው፤ ድፍረት ግልጥ የቃልና የሕይወት ምስክርነትን ያሳያል፤ ፍርሃት ከፍቅር ይለያል፤ ለመንፈሳዊ ምስክርነት መድፈር ግን ጸጋ ያበዛል፤ ጽኑ ፍቅርን ይገልጣል። በፍጻሜው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትን ድል ነሥቶ ተነሣ፤ [የአርማትያሱ ሰው ጌታችን ኢየሱስ ከሙታን ተነሣ ሲባል ምን ተሰምቶት ይኾን? በተውሶ መቃብር የተቀበረው ጌታ፣ የጌትነቱ ኃይል ሲገለጥ እንዴት ይኾን ደስታውን የገለጠው?!] ጌታችን ኢየሱስ ተነሥቷል ማለትና ለእርሱ በጽድቅ ሕይወት እኖራለሁ ማለት፣ ታላቅ ድፍረትና መንፈስ ቅዱሳዊ አቅም ይፈልጋል! መንፈስ ቅዱስ ጸጋውን ያብዛልን፤ አሜን፡፡
ይቀጥላል ...





[1]  አርማትያ ከኢየሩሳሌም በስተሰሜን ምዕራብ 32 ኪ.ሜ ርቃ በኤፍራታ ኮረብታማ ምድር የነበረች ገጠራማ ከተማ ናት፡፡

3 comments:

  1. amen amen tebarek kalehiwot yasemaln.

    ReplyDelete
  2. ድፍረት በሓዋርያት ሥራ ውስጥ ተደጋግሞ የተጠቀሰ ቃል ነው፤ ድፍረት ግልጥ የቃልና የሕይወት ምስክርነትን ያሳያል፤ ፍርሃት ከፍቅር ይለያል፤ ለመንፈሳዊ ምስክርነት መድፈር ግን ጸጋ ያበዛል፤ ጽኑ ፍቅርን ይገልጣል። በፍጻሜው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትን ድል ነሥቶ ተነሣ፤ [የአርማትያሱ ሰው ጌታችን ኢየሱስ ከሙታን ተነሣ ሲባል ምን ተሰምቶት ይኾን? በተውሶ መቃብር የተቀበረው ጌታ፣ የጌትነቱ ኃይል ሲገለጥ እንዴት ይኾን ደስታውን የገለጠው?!] ጌታችን ኢየሱስ ተነሥቷል ማለትና ለእርሱ በጽድቅ ሕይወት እኖራለሁ ማለት፣ ታላቅ ድፍረትና መንፈስ ቅዱሳዊ አቅም ይፈልጋል! መንፈስ ቅዱስ ጸጋውን ያብዛልን፤ አሜን፡፡ tsega yibzalh

    ReplyDelete
  3. አሜን አሜን የቃሉን መገለጥ ያብዛልህ

    ReplyDelete