ዋቄፈታ ዋቃ ከሰማይ
አውርዶልናል ብሎ ከሚያምናቸው አያሌ በአላት መካከል አንዱ የመስቀላ በአል ነው፤ ካልታተመው መጽሐፌ ዋቄፈታ ስለ መስቀላ የሚያምነውን
እንዲህ አስነብባችኋለሁ፤
“ … በአሉ በሌሎች ስፍራዎች፣ “ዳሞቲ” እየተባለ
ይጠራል።[1] “ሁሉቆ” ብለውም
የሚጠሩት አሉ፤[2] ችግሮችንና ክፉውን
መናፍስት ለማራቅ የጉባ ወይም የማቃጠል ሥርዓት ይከናወናል።[3]
ይህ
በአል “ጉባ” ተብሎ በሰሜን ሸዋ አከባቢ ነሐሴ 16 ቀን ይከበራል። በአብዛኛው ቦታ
ደግሞ ከኦርቶዶክስ ተዋሕዶ የ“መስቀል” ክብረ በአል ጋር ተያይዞ የሚከበር ነው።
የበአሉን መከበር ምክንያት ሲጠቅሱ፣ “ከክረምት
ጨለማ ወደ ፀሃይ ብርሃን የወጣንበት ነው” በማለት ይጠቅሳሉ። ሌሎች ደግሞ የአዲስ ዓመት የመጀመሪያ ቀን ነው
ወይም የአዲስ ዓመት ብሥራት ማብሠሪያ ብለው ያምናሉ።[4] አንዳንዶች ግን፣
አዲስ ዓመት መጀመሪያ፦
“ … ከጊዜ በኋላ ይቀየር እንጂ ድሮ እንደ አዲስ የዘመን መለወጫ ወር ይወሰድ የነበረው ከየካቲት ወር እንደ ነበር ይታወቃል።”
ይላሉ።
በዕለቱ ችቦ ይበራል፤ ሊጥ በእርጥብ ቅጠል ተጠቅልሎ ችቦ
ውስጥ ይገባና ሲበስል ወጥቶ ለከብቶች ያበሉታል፤ የዚህ ምክንያትም “የከብቶችን ሆድ ቁርጠት ይከላከላል” የሚል ነው።[5] በመስቃላ
ዕለት እሳቱ የለበለበውን ቅጠል በዓመዱ አሻሽቶ፣ የተመገበ ሰው እባብ ቢነድፈው እንኳ አይጐዳውም ወይም መርዙን ያበርሰዋል
ተብሎ ይታመናል።
ሌሎች ግን መስቀል የሚባለው በአል፣ “አመስ ቀላ”
ከሚባለው በአል የተወረሰ ወይም ኾን ተብሎ የኦሮሞን ባህል ለማጥፋት ወደ መስቀል የተቀየረ እንጂ፣ መስቀል የሚባል በአል የለም
ይላሉ።[6]
ለዚህም እንደ አንድ መከራከሪያ የሚያቀርቡት፣ የመስቀል በአል በሌላው የክርስቲያን ዓለም የማይከበርና በኢትዮጵያ ብቻ የሚከበር
መኾኑና ሌላው ደግሞ፣ የኦርቶዶክሱ የመስቀል ጥንተ በአሉ በመጋቢት እንጂ በመስከረም አይደለም በማለት ነው።[7]
በተጨማሪም፣ “አመስ ቀላ” ማለት “ደግማችሁ እረዱ”
ማለት ሲኾን፣ ከዚህ በአል ጋር ተያያዥነት አለው በማለት ይናገራሉ። በተለይም የቡና ዕርድ ወይም “ቡነ ቀላ” የሚባለው፣
ለደመራው ከመውጣቱ በፊት የሚያከናወነው ተግባር ነው። የቡና እርድ የሚባለው፣ ድፍኑን ተቆልቶና በቅቤ ተዘፍዝፎ የማማሰል
ሥርዓት ነው። ይኸውም ማማሰያው የወንድን ብልት ሲያመለክት፣ ሲማሰል ከቆለቆሉ ውስጥ የሚወጣው ፍሬ የሴት ልጅ የዘር መራቢያ
አካልን፣ የተዘፈዘፈበት ቅቤ ደግሞ ፍሬያማነትንና ወልዶ ተዋልዶ መባዛትን ይወክላል በማለት ያምናሉ።[8]
በርግጥ፣ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፣
መስከረም 16 ቀን በተለምዶ “የደመራ በአል” ተብሎ፣ ደመራ ተደምሮ፣ አበባ ከጫፉ ታስሮ፣ አብዛኛው ኦርቶክሳዊ በቤቱ ችቦ
በመለኮስ የሚያከብረው በአል፣ ልማዳዊ እንጂ ክርስቲያናዊ አይደለም ብለው የሞገቱም አሉ።[9]
(ዋቄስትና - ዋቄፈናና ክርስትና ምንና ምን ናቸው? ከሚለውና
ካልታተመው መጽሐፌ ገጽ 111-113 ላይ የተወሰደ)
“እኛ ግን የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን፤ ይህም ለአይሁድ
ማሰናከያ ለአሕዛብም ሞኝነት ነው፥” (1ቆሮ. 1፥23)
“ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን በማይጠፋ ፍቅር ለሚወድዱ ሁሉ ጸጋ ይሁን።”
(ኤፌ. 6:24) አሜን።
[1]
ድሪቢ ደምሴ፤ የኦሮሞ የማንነት ታሪክ፤ ገጽ
259
[2] የተባለትን
ምክንያት ሲያብራሩ፣ ክረምቱን ሙሉ ማየት ተስኖአቸው የሚከርሙት እንደ እባብና ጩሉሌ ያሉት ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ስለሚዩየ ነው።
(ብሩ ጸጋዬ፤ የሥልጣኔ አፍሪካዊ ምንጭና በተረት መጋረጃዎች
የተደበቁ እውነቶች፤ 2008 ዓ.ም፤ ገጽ 132)
[3] Tesema Ta’a;
The Political Economy of an African Society
in Transformation: The Case of Macca Oromo (Ethiopia).” 2006.
p.
94
[4] ድሪቢ ደምሴ፤ የኦሮሞ የማንነት ታሪክ፤ ገጽ 259
[5] ዋቅቤካ ኤርፓ፣ የኦሮሞ ብሔር ባህል ሥርዐተ አምልኮ እና የኢትዮጵያ
ቤተክርስቲያን ቁርኝት፣ ቁጥር 2፣ ነሐሴ 2004፣ ገጽ 37
[6] Dirribii
Damusee Bokkuu; Ilaalcha Oromoo:
Barroo Aadaa seenaa fi Amantaa Oromoo; ገጽ 77
[7] ዝኒ ከማኹ እና
አማረ አፈለ ቢሻው፤ ኢትዮጵያ፤ የሰው ዘር የተገኘባት
የእምነትና የሥልጣኔ ምንጭ ናት፤ 2004፤ p. 56
[8] ብሩ
ጸጋዬ፤ የሥልጣኔ አፍሪካዊ ምንጭና በተረት መጋረጃዎች
የተደበቁ እውነቶች፤ 2008 ዓ.ም፤ ገጽ 132
[9] አማረ
ከፈለ ቢሻው፤ ኢትዮጵያ የሰው ዘር የተገኘባት! የእምነትና
የሥልጣኔ ምንጭ ናት፤ ገጽ 56-57
Greatest man in history, had no degree,yet they called him Teacher .
ReplyDelete