Monday, 10 February 2025

ከአንድ ዐይነትነት የመንፈስ አንድነት ይበልጣል።

 Please read in PDF

ዶግማና ቀኖና የማያሳስባቸውና የማያስጨንቃቸው፣ አንድ ላይ ያሉ አንድ ዐይነት “ኅብረቶች” ብዙ ናቸው። የሕይወት ልምምድና የኑሮ ዘይቤ ግድ የማይሰጣቸው፣ በጋራ ግን "መንፈሳዊ የሚመስል ኅብረት" ያላቸው ጀማዎች፣ በዘመናችን እንደ አሸን የፈሉ ናቸው። በአንድ ወቅት ፈሪሳውያንና ሰዱቃውያን ተስማምተው አንድ ኾነው ነበር፣ ቅዱስ ጳውሎስን ለመክሰስ፤ ነገር ግን አንድነታቸው የትንሣኤ ሙታን የዶግማ ጥያቄ ሲነሣ፣ ብትንትናቸው ወጣ፤ “... ይህንም ባለ ጊዜ በፈሪሳውያንና በሰዱቃውያን መካከል ጥል ሆነ ሸንጎውም ተለያየ።” (ሐ.ሥ. 23፥7) እንዲል።

በዘመናችን ካሉ አያሌ ግዳንግድ ዐንድ ዐይነት አንድነቶች መካከል፣ "አንድነታቸው የቆመው" የዶግማና የቀኖና መርኅ ተረግጦ ወይም ገለል ተደርጎ፤ የሕይወት ልምምድና የኑሮ ዘይቤ ተደፍጥጦ ወይም አይነኬ ርዕስ ኾኖ በተከድኖ ይብሰል ተለባብሶና ተድበስብሶ ነው። እንዲህ ባሉ ኅብረቶች መካከል፣ የኢየሱስ ሕይወት፣ ሥራና ትምህርት አይወሩም፤ አይሰበኩም፤ የውይይት ርዕስ አይደሉም። የመጽሐፍ ቅዱስ ሥልጣን የማይነካ ርዕስ ነው፤ ስለ ኀጢአት ማስተማርና መገሰጽ የማይደፈሩ ናቸው።

እንዲህ ባሉ "ኅብረቶች" ውስጥ ያሉ ሰዎች፣ ምልክቶቻቸው ግልጽና ተመሳሳይ ነው። “ለምን ፍቅር ብቻ አትሰብኩም?” [በሚያሳዝን መልኩ እንዲህ የሚል ሰበብ ያቀረበልኝ፣ በግብረ ሰዶማዊነት የታወቀ አንድ አገልጋይ ነበር] “ለምን ፍቅር ብቻ አትሰብኩም?” የሚሉ ኹሉ አመቻማች፣ አንድ አይነቶች ናቸው ማለት ይከብዳል፤ በብዛት ግን ይህን ሰበብ የሚያቀርቡ ሰዎች፣ ዶግማና ቀኖና የማይመቻቸው፣ ተመሳስለው ኗሪ፣ ፊሪሳዊ ግብዝነትን ገንዘብ ያደረጉ፣ ከማንም ጋር መቀያየም የማይሹ፣ እንደ ገበያ ለሻጭም ለገዢም የሚመቹ … ናቸው፡፡

እውነት ለመናገር፣ ደረት እስከ ቀላ ዶግማ መጣል፣ ሆድ እስከ ሞላ ቀኖና መግፋት፣ ኪስ እስከ ረጠበ ትውፊት መርገጥ፣ ኢየሱስንና ትምህርቱን፤ ሥራውንና ሕይወቱን ትቶ … መጐራበትና የአንድ ዐይነተኝነት ጽዋ መጫለጥ … ይዋል ይደር እንጂ እንክርዳድ ማጨድ፤ መምረርና መርከስ የማይቀር ፍሬ ነው፡፡

ቅዱስ ጳውሎስ፣ ክርስቶስን በማመን ስለሚከተሉን ነገሮች ሲናገር፣ “በሰላም ማሰሪያ የመንፈስን አንድነት ለመጠበቅ ትጉ።” (ኤፌ. 4፥3) ይላል፡፡ ማመን አኗኗርን መለወጥ አለበት፤ ወንጌል ተረድተናል ካልን የወንጌል ኑሮና ዘይቤው በሕይወታችን ሊንጸባረቅ ይገባል፡፡ የመንፈስ አንድነት መጠበቂያውና ማጥበቂያው ልጥ፣ በክርስቶስ ኢየሱስ ላይ ያለን ሕያው እምነት ነው፡፡ ክርስቶስን ገለል አድርገን፤ ትምህርቱንና ሥራውን ችላ ብለን የምናመጣው ኅብረትም ኾነ፤ የምናሳየው መንፈሳዊ ተጽዕኖ የለም፡፡

አንድ የኾንነው አንድ ጌታ፣ አንድ ሃይማኖት፣ አንዲት ጥምቀት፣ አንድ አምላክ ስላለንና አንድ አካል ውስጥ በመንፈሱ ስለ ኾንን ነው፡፡ በኒህ ነገሮች ከተከፋፈልን አንድ ላይ ብንኾንም፣ አንድ አይደለንም፡፡ በአገራችን ክርስትናን ካራከሱትን ካንኳሰሱት ነገሮች ቀዳሚው ተርታ ውስጥ የሚመደበው፣ አንድ ዓይነቶች መብዛታቸው ነው፡፡ ወዳጆች ሆይ፤ በክርስቶስ ኢየሱስ ያለውንና ለእኛም በመንፈስ ቅዱስ የተሰጠውን የመንፈስ አንድነት ጠብቁ፤ ለመጠበቅም ትጉ እንጂ አንድ ዐይነትነትን አትመኙ፤ አትጎምጁም!

No comments:

Post a Comment