የእስራኤልን ወደ ባቢሎን መማረክ፣ ፊት
ለፊት ከተናገሩት ነቢያት መካከል ቀዳሚው ነቢዩ ኤርምያስ ነው። ነቢዩ ዘመኑን በእንባና በልቅሶ ያሳለፈና አብዝቶ ከማልቀሱም
የተነሣ “አልቃሻው ነቢይ” የሚል ቅጽል ስም የተሰጠው ነው። የኤርምያስ ዘመኑ ብቻ ሳይኾን ሕይወቱም ጭምር አሳዛኝና በሕመም፤ በሰቆቃ
የተሞላ ነበር።
የእግዚአብሔርን ፍጹምና እውነተኛ ቃሎቹን
በግልጽ ማለትም፣ ኢየሩሳሌምና ሕዝቦችዋ እንደሚማረኩ (ኤር. 8፥18፤ 13፥17) በመናገሩና ለባቢሎን ንጉሥ እንዲገዙ፣ እጅ
እንዲሰጡ ከእግዚአብሔር የተላለፈውን ትእዛዛዊ ትንቢት በመተንበዩ ተጠላ፤ ብዙዎችም ሊገድሉት አሰቡ (ኤር. 11፥21፤
26፥11፤ 36፥26፤ 38፥6)። በዚህ ሳይበቃ በእግር ግንድ ተያዘ፤ በጭቃ ጕድጓድ ውስጥም ተጣለ፤ ተወረወረም፤
(20፥2፤37፥13፤38፥28)፤ እያበደ ትንቢት የሚናገር ሰው ተባለ (29፥26)። ከዚህ በዘለለ አስቀድሞ ሊመጣ ያለውን ጥፋት
ስላየለት፣ ከሚደርስበትም ጥልቅ የመንፈስ ስብራትና ሐዘን ሊጠብቀውም ስላሰበ ሚስት እንዳያገባ፣ ልጆችን እንዳይወልድ፣ ወደ
ግብዣና ልቅሶ ስፍራም እንዳይሄድ እግዚአብሔር አስቀድሞ ከለከለው (ኤር. 16)።
ይህ ኹሉ በኤርምያስ ሕይወት የኾነው፣
የእስራኤልን ኀጢአት በመግለጡና ይህን ተከትሎም የሚመጣውን አይቀሬውን ፍርድ በመናገሩ ምክንያት ነው። በተደጋጋሚ በብዙዎች ዘንድ
የመጠላቱና የመገፋቱም ምክንያት “ከዚህ ፍርድ ታመልጡ ዘንድ፣ ንስሐ ግቡ” ማለቱ እንጂ ሌላ አልነበረም። ነቢዩ በተለይም
እስራኤልንና ኢየሩሳሌምን ሕዝቦቿንም ጭምር እጅግ በመውደዱ ምክንያት (ኤር. 8፥18፤ 13፥17) የሚደርስባቸውን መከራና ሰቆቃ
በማስተዋል ፍጹም አዝኖአል፤ ተጨንቆአል፤ ተሰቃይቶአል። እስራኤልና ኢየሩሳሌም ግን ይህን ጥልቅ ሐዘኑንና ስብራቱን ፈጽሞ
አላስተዋሉለትም። የምርኮውን ፍጻሜ እንደምናስተውለውም ኤርምያስ በፍጻሜው ከሕዝቡ ጋር አብሮ የምርኮው ገፈት ቀማሽ ኾኖአል፤
አብሮ ሰቆቃውን ተሰቅቆአል።
ይህ ነቢይ በዚህ ጥልቅ መከራ ውስጥ
ቢያልፍም፣ ነገር ግን ስለ እስራኤል ተስፋና ተሐድሶ ከመናገር ከቶውንም ቸል አላለም። ራሱም ነቢዩ እንኳ፣
“ለዚህም ሕዝብ
የተመሸገ የናስ ቅጥር አደርግሃለሁ፤ ይዋጉሃል እኔ ግን ለማዳን ከአንተ ጋር ነኝና አያሸንፉህም።” (ኤር. 15፥20) የሚለውን
የአምላኩን ቃል በመታመን፣ እግዚአብሔርን እንደ ተስፋው እጅግ አድርጐ ይጠብቀው ነበር።
እግዚአብሔር በኀጢአታችን ፈጽሞ
ቢቀጣንም፣ ርሱ ግን “ምሥራቅ ከምዕራብ እንደሚርቅ፥ እንዲሁ ኃጢአታችንን ከእኛ አራቀ።” (103፥12) እንዲል፣ በደላችንንና
ኀጢአታችንን ፈጽሞ ያርቃል፤ ይቅርም ይለናል። የፍጻሜ ተስፋውና ዕቅዱ እኛን ማዳንና መመለስ ነው። ዘወትር ግን መዘንጋት
የሌለብን እውነት አለ፤ እርሱም እግዚአብሔር ኀጢአትን ፈጽሞ ይጸየፋል፤ አይወድም፤ ርሱም እጅግ ከክፋት የራቀ አምላክ ነውና።
ዛሬ በምድራችን ላይ የምናየው ሰቆቃና
ዋይታ፤ ዕንባና ጥልቅ ሐዘን የእግዚአብሔር ልብ ላላቸው እውነተኛ አማኞች ፈጽሞ እፎይታ የሚሰጥ አይደለም። እንደ ኤርምያስ
አልቃሻና “ነጭናጫ” የሚያደርግ ነው። አገራችንን ጨምሮ በምድራችን ላይ አያሌ ስፍራዎች እጅግ አሰቃቂ ጦርነቶች እየተደረጉ
ነው፤ ሰዎች በብዙ ዓይነት ጎዳናዎች በሞትና በሰቀቀን መንገድ ሕይወታቸው እያለፈ ነው። በስደት፣ በርስ በርስ ጦርነቶች፣ በራብ፣ በቸነፈር … ወንጌል ሳይሰሙና
ሳይደርሳቸው የሚሞቱ ሰዎች እጅግ በርካቶች ናቸው።
ይህን ኹሉ በማየት ለመላለሙ ልትማልድ
የተጠራች ቤተ ክርስቲያን በዚህ ምድር ብትኖርም፣ እንደ ስሟ ተጽዕኖ ፈጣሪነቷ ደካማ ይመስላል። ከገዳዮች ጋር ትኹን ከሟቾች
ጋር፣ የቱ ጋር እንዳለች ሚናዋ ግራ ያጋባል፤ የራሽያና የዩክሬን ጦርነቶችን ባራኪዎቹ “ጳጳሳት” ነበሩ፤ በኛም ምድር ላይ
የተደረጉትን ጦርነቶች ባራኪዎቹ ጳጳሳትና ፓስተሮች ነበሩ፤ ይህ እጅግ በጣም ቅስም የሚሰብር፤ ጆሮ ጭው የሚያደርግ ነው።
እንደ ኤርምያስ፣ ከክፋቱ ጋር የማትተባበር፤
ዓመጻን የምትጠየፍና የምትጠላ፤ ከእግዚአብሔር የሚመጣውን የጽድቅ ፍርድ ሳታወላዳ የምትናገር፤ የኀጢአትን መራርነት በጽኑ የምትመሰክር፤
ደግሞም ተስፋንና ምሕረትን፤ ይቅርታንና ተሐድሶን ለሕዝቡ የምታሳይ ቤተ ክርስቲያን፤ እንዲኹም ጽኑ ዕንባ፤ ጠንካራ ሐዘኔታ ያላቸው
አገልጋዮችና አማኞች ያስፈልጉናል።
ነቢዩ ኤርምያስ እጅግ የምወደው ነቢይ ነው፤ ለኪዳኑ ሕዝብ እንዳለቀሰ፤ ከኪዳኑ ሕዝብ ጋር መከራ እንደ ተካፈለ በፍጻሜውም ከኪዳኑ ሕዝብ ጋር አለፈ፤ ቤተ ክርስቲያን እንደ ኤርምያስ በሚደነግጥና በሚራራ ልብ እንድትገለጥ ብርቱ መሻቴ ነው!
እግዚአበሔር ይመስገን!!!
ReplyDelete" ረድኤታችን ሰማይንና ምድርን በሠራ በእግዚአብሔር ስም ነው።"
ReplyDelete(መዝሙረ ዳዊት 124:8)